Friday, March 24, 2017

አማርኛ ይሰማሉ ፣ ይናገራሉ ነገር ግን አያነቡም ፣ አይፅፉም…… ሀብተስላሴ ታፈሰ !!!


  ትውልዳቸው ኢትዮጵያ ቢሆንም ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ በራሽያ እና በግሪክ እንዲሁም በሌሎች ሀገራት ነው አብዛኛውን ህይወታቸውን ያሳለፉት፡፡ ከአምስት በላይ ቋንቋዎችን የሚችሉ ሲሆን ራሽያኛ ፣ ግሪክኛ ፣ ጣሊያንኛ ፣ እንግሊዘኛ ፣ ስፓኒሽ እና አማርኛ ይጠቀሳሉ፡፡ ቋንቋን ስናነሳ ገራሚ ታሪካቸው የአማሪኛው ነገር ነው፡፡ አማርኛ ይሰማሉ ፣ ይናገራሉ ነገር ግን አያነቡም ፣ አይፅፉም፡፡
   

  ሌላው ገራሚ ነገራቸው ደግሞ የኢትዮጵያን የባህል ምግብ እና መጠጥ አለመጠቀማቸው ነው፡፡ በውጪ ሀገር ብዙ ጊዜ መቆየታቸው ተፅዕኖ ቢያደርግባቸውም ሌላም ምክንያት እናዳላቸው ይገልፃሉ፡፡ ይኸውም ከውጪ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ሲመለሱ እናታቸው የፍቅራቸውን እና የእናትነታቸውን ልጃቸውን ሊያጎርሱ ይዘጋጃሉ፤ልጅ ለነገሩ እንግዳ ናቸው እና አሻፈረኝ ሲሉ እናት ቅስማቸው ይሰበራል፡፡ በዚህም እናቴ ረገመችኝ ከዚያ በኋላ ከአትክልት እና ፍራፍሬ ውጪ የባህል ምግቦች እና መጠጦችን እስካሁን ተጠቅሜ አላውቅም ሲሉም አጫውተውኛል፡፡ እኚህ ሰው የቱሪዝም አባት እየተባሉ የሚጠሩት ጋሽ ሀብተስላሴ ታፈሰ ናቸው፡፡
  
  ጋሽ ሀብተስላሴ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ላሳደግ ብዙ መስዕዋትነት ከፍለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት እንዲመሰረትም የበኩላቸውን ጥረት አድርገዋል፡፡ እሳቸው በጀመሩት ከቀረጥ ነፃ(ዲዩቲ ፍሪ) ግብይት ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በአለም ስሟ እንዲጠራ አስችለዋል፡፡ ባለፉት ረጅም አመታት ኢትዮጵያ በአለም ላይ ትተዋወቅበት የነበረው “የ13 ወር ፀጋ” መርህ አመንጪም ናቸው፡፡


  የቀድሞው ልዑል መኮንን መታሰቢያ ሆስፒታል(የአሁኑ ጥቁር አንበሳ) እና ሽራተን ሆቴል መዲናችን አዲስ አበባ እንዲቋቋሙ በማድረጉ በኩል ትልቅ ሚና ነበራቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ የህዝብ ለህዝብ ኪነት ቡድን ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ በመሄድ የኢትዮጵያን ባህል እና ቅርሶች እንዲያስተዋውቁ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ ለዚህም በካናዳ በ1960ዓ.ም የተካሄደውን “ኤክስፖ 67” መጥቀስ ይቻላል፡፡
  

     ጥሩ ፎቶግራፍ አንሽ የሆኑት ሀብተስላሴ ከመደበኛ ስራቸው በጡረታ ከተገለሉ በኋላም በግላቸው አሁንም በቱሪዝሙ ዘርፍ እየሰሩ ይገኛል፡፡ ሀገሪቱ በቱሪዝሙ ዘርፍ ማግኘት ያለባትን ባለማግኘቷ እና እሳቸውም የሚያስቡት ያህል ባለማድረጋቸው ይቆጫሉ፡፡ የ91 ዓመት የእድሜ ባለፀጋም ሆነው አሁንም ስለ ኢትዮጵያ ቱሪዝም ማበብ ያስባሉ ፣ ይጨነቃሉ፡፡ በርካታ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ እና በማማከርም ይሰራሉ፡፡ ከያዟቸው ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ እንደመሆኗ የሉሲን ፎቶ በአንድ ብር ወይም በአምስት ብር ኖት ላይ አሳትሞ በማሰራጨት በመላው አለም ማስተዋወቅ የሚለው ይገኝበታል፡፡   


    ኢትዮጵያ ለረጅም አመታት ትተዋወቅበት የነበረው “የ13 ወር ፀጋ” መርህ ምድረ ቀደምት በሚለው ተቀይሯል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ “የ13 ወር ፀጋ” መርህ አመንጪ እና የቱሪዝም አባት ተብለው የሚጠሩት ሀብተስላሴ ታፈሰ ብሄራዊ እውቅና ተስጥቷቸዋል፣ የወርቅ ኒሻን እና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሀገር ውስጥ እና በውጪ በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡  ክብር ለሀገር ባለውለታዎቻችን !!!

No comments:

Post a Comment