Tuesday, July 5, 2016

“የጦር ሜዳው ቀሲስ” ….. መምህር ፣ ደራሲ እና ጋዜጠኛ አበራ ለማ !!!


 አበራ ለማ  የተወለደው 1943 .. ፍቼ ሰላሌ ውስጥ ነው። እድገቱ ወሊሶንና አዲስ አበባ ያካትታል። ከኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅም በዲፕሎማ መርሃ ግብር ከፍተኛ ውጤት በማግኘቱ “የአመቱ ታላቅ ተማሪ” የሚል ሽልማትንም አግኝቷል፡፡  በዲግሪ ፕሮግራምም ኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ጥናት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማዕርግ ተመራቂ ነው። ጋዜጠኝነት ሙያ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ፕሬስ መምሪያዎች ሠርቷል። ከጦር ግምባር ጋዜጠኝነት እስከ ኪነጥበባት ዘርፎች ሃያሲነት ዘልቋል።በጦር ሜዳ ዘገባውም “የጦር ሜዳው ቀሲስ” የሚል ቅፅል ስም ተሰጥቶት ነበር ፡፡


   እስከ 1980ዎቹ አጋማሽ ድረስ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ዋና ጸሃፊ ሁኖ አገልግሏል። ዛሬ ኖርዌይ ነዋሪ ነው። በኖርዌይ ደራስያን ማኅበር ብቸኛውና የመጀመሪያው ጥቁርና በአፍ መፍቻ ቋንቋው የሚፅፍ አባል ደራሲ ነው። በዚህ ማኅበር ውስጥ የዓለም አቀፍ ኮሚቴው የረዥም ዘመን አባል በመሆንም ይታወቃል። ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህንንና (1997) ስዊድናዊ/ኤርትራ የሆነውን አስመራውን እስረኛ፣ ደራሲና ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሐቅን (2009 ...) ሃሳብን በነጻ የመግለፅ ሽልማት እንዲሸለሙ በእጩነት አቅርቦ ማሸለሙም ይታወሳል።


ከአበራ ለማ የታተሙ ሥራዎች መካከል፡-
·         1967 ኩል ወይስ ጥላሸት እና አውጫጭኝ የግጥም መድብል፣
·         1974 ሽበት፣ የግጥም መድብል፣
·         1975 ሕይወትና ሞት፣ የአጫጭር ልብ ወለዶች መድብል፣
·         1976 ሞገደኛው ነውጤ፣ ኖቭሌት፣
·         1978 አባደፋር፣ ከሌሎች ደራስያን ጋርስብስብ፣
·         1978 ጽጌረዳ ብእር፣ ከሌሎች ገጣሚያን ጋርስብስብ፣
·         1980 የማለዳ ስንቅ፣ ያጫጭር ልቦለዶችና ግጥሞች መድብል፣
·         1980 መቆያ፣ ያጫጭር ልቦለዶችና ግጥሞች መድብል፣
·         1981 ትዝታን በጸጸት፣ ያጫጭር ልቦለዶች ትርጉም….በጋራ፣
·         1994 አውጫጭኝ፣ የግጥም መድብል፣
·       1994 ሙያዊ ሙዳዬ ቃላት፣ ኢልቦለድየቋንቋ ጉዳይ፣
·         1998 የእውቀት ማኅደር፣ ኢልቦለድጠቅላላ እውቀት፣
·         2003 E.C. ULIKE HORIZON Norsk Saksprosa samling med andre forfatterer
·         እውነትም እኛ... የግጥሞች ስብስብ ቪዲዮ በዲቪዲ፣ ታህሳስ 2003 ..
·         ጥሎ ማለፍ.....ታሪካዊ ልቦለድ፣ ጥር 2003 ..
·         ሽፈራው... ሞሪንጋ   - 2006ዓ.ም
·          “ቅንጣት - የኔዎቹ ኖቭሌቶች” - 2007ዓ.ም የሚሉት ከስራዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ጥቂት ድርሰቶቹም በሬዲዮ ተተርከዋል ፡፡ በተደጋጋሚ የተደመጠው እና በኢትዮጵያ ሬዲዮ በአርቲስት ፍቃዱ ተክለማሪያም አማካኝነት የተተረከው “ሞገደኛው ነውጤ” በቀዳሚነት ይቀመጣል፡፡
  

   ደራሲ ፣ ገጣሚ እና ጋዜጠኝ አበራ ለማ ከድርሰት ስራው ባሻገርም በመምህርነት ፣ በህዝብ ግንኙነት ባለሙያ እና በጋዜጠኝነት ሙያዎች በተለያዩ ተቋማት አገልግሏል፡፡ የተወሰኑ የግጥም ስራዎቹንም የተለያዩ ድምፃውያን ተጫውተውለታል፡፡ ለአብነትም ፀሀይ እንዳለ (ያሉትን ይበሉ እና ስውሩ መውደዴ) ፣ ጌታቸው ካሳ (ሀገሬን አትንኳት እና አደሴዋ) ፣ አበበች ደራራ ፣ ትዕግስት እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ አማርኛ ፣ ኦሮምኛ ፣ እንግሊዘኛ ፣ ኖሪጃን(የኖርዌ ቋንቋ) እና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎችን ይናገራል፡፡

  ኑሮውን በኖርዌ ያደረገው አበራ ለማ ሰሞኑን ወደ ትውልድ ሀገሩ መጥቶ ስለ ስራዎቹ እና የህይወት ልምዱ ተጨዋወተን ነበር ፤ከዚህም በጥቂቱ አካፈልኳችሁ፡፡ ለጋሽ አበራ ለማ እድሜ እና ጤና ፣ በቀሪ ስራዎቹም ስኬትን ተመኘሁ፡፡ የቀረውን እናንተ ጨምሩበት …..

No comments:

Post a Comment