ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ በሸዋ ጠቅላይ ግዛት ጅሩ ቆላ ውስጥ እምባጮ መግደላዊት በሚባል ሥፍራ በ1891ዓ.ም ተወለዱ። በቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያ ትምህርታቸውን እስከ ዳዊት ድረስ ካጠናቀቁ በኋላ የዜማ ትምህርት ተከታትለው ጾመ ድጓ እና ድጓን ዘልቀዋል። ቀጥሎም የቅኔ ትምህርታችውን አጠናቀው በአሥራ አራት ዓመት ዕድሜያቸው በወንበር ፀሐፊነት የመጀመሪያ ሥራቸውን ጀመሩ። የመፅሕፍተ ሐዲሳትን ትርጓሜ፤ የዮሐንስ አፈወርቅን ትርጓሜ፤ እንዲሁም የመቅድመ ወንጌልን ትርጓሜ ትምህርት ያጠናቀቁት እኝህ ታላቅ ሰው ብርሃንና ሰላም (ጋዜጣ) የተሰኘው ጋዜጣ ሲመሠረት የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ በመሆን፣ ቀጥለውም በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የግዕዝና የአማርኛ አስተማሪ በመሆን አገልግለዋል። ከፋሺስት ወረራ በኋላ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በኃላፊነትና በዳይሬክተርነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በአጠቃላይ ከ50 ዓመታት በላይ በመንግስት ስራ አገልግሎት ተሳትፈዋል፡፡
ሥነ ጽሑፍንና ታሪክን በተመለከተ፣ አሥራ ሦስት መፃህፍትን የደረሱ ሲሆን፣ ሰባት መጻሕፍት ደግሞ ተርጉመው አቅርበዋል። እንዲሁም የተለያዩ ጽሑፎችን አሰባስበው ከማዘጋጀታቸው ባሻገር፣ የቅዱሳት መፃህፍት ሥራዎችም ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጋር በትብብር አዘጋጅተዋል። ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ አንዱ የአማርኛ ቋንቋ አባት ተብለው ቢወደሱ ማጋነን አይሆንም። ይህም የተባለበት ምክንያት የአማርኛ ሰዋሰውን አስመልክቶ ባደረጉት ጥልቅ ምርምሮች እና በተቀናጀ መልክ የተዘጋጁ የአማርኛ ሰዋሰው መማርያ መጸሐፍትን በመጻፋቸው ነው።
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት ተቀጥረው በተርጓሚነት፣ በአዘጋጅነት እና በደራሲነት ባገለገሉበት ጊዜ ከ35 በላይ የሚሆኑ መፀሀፍት ለህትመት እንዲበቁ አድርገዋል። በዚህም መሰረት የአማርኛን ቋንቋ ከዘመናዊ እና ከኪነታዊ አነጋገር በማስማማት ላደረጉት የላቀ አገልግሎት ድርጅቱ በ 1964 ዓ.ም. የአማርኛ ስነ ጽሁፍ ሽልማትን ሰጥቷቸዋል ። በወቅቱም 10,000 ብር፣ የወርቅ ኒሻን እና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በብሪታንያ ሶማሌላንድ እና በፈረንሳይ ሶማሌንድ መካከል የተፈጠረውን የድንበር ግጭት ለመፍታት ለሶስት አመታት (1924-1927) ያገለገለው ኮሚሽን አባል እና ዋና ፀሀፊ በመሆን አገልግለዋል።
የደራሲው ሥራዎች
1. የአማርኛ ሰዋሰው(ቋንቋ)
2. የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ(ታሪክ)
3. ትምህርተ ሕፃናት(ትምህርት)
4. ዐውደ መዋእል(ታሪክ)
5. የመ.ኀ.ወ.ቂ. የአማርኛ ስዋስው መክፈቻ(ትምህርት)
6. የትእምርተ መንግሥት ታሪክ በመዋዕሊሁ ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ(ታሪክ)
7. የአማርኛ ስዋስው ለጀማሪዎች፣ መጀመሪያ እርምጃ ስም፣ተውላጠ ስም፣ ቅጽል፣መስተዋድድ (ትምህርት)
8. የኢትዮጵያ መዝገበ ቃላት(ቋንቋ)
9. የጥንት ታሪክ ሔሮዶቱስ እንደጻፈው ትርጉም( ትርጉም)
10. ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጎንደርን የመጎብኘታቸው ታሪክ ፲፱፻፴፱ መስከረም ፳፫ – ጥቅምት ፯።(ታሪክ)
11. ጥበብን መፈለግ፤ቅን ጥበብ በቅን አማርኛ፤ (ፍልስፍና) እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡
2. የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ(ታሪክ)
3. ትምህርተ ሕፃናት(ትምህርት)
4. ዐውደ መዋእል(ታሪክ)
5. የመ.ኀ.ወ.ቂ. የአማርኛ ስዋስው መክፈቻ(ትምህርት)
6. የትእምርተ መንግሥት ታሪክ በመዋዕሊሁ ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ(ታሪክ)
7. የአማርኛ ስዋስው ለጀማሪዎች፣ መጀመሪያ እርምጃ ስም፣ተውላጠ ስም፣ ቅጽል፣መስተዋድድ (ትምህርት)
8. የኢትዮጵያ መዝገበ ቃላት(ቋንቋ)
9. የጥንት ታሪክ ሔሮዶቱስ እንደጻፈው ትርጉም( ትርጉም)
10. ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጎንደርን የመጎብኘታቸው ታሪክ ፲፱፻፴፱ መስከረም ፳፫ – ጥቅምት ፯።(ታሪክ)
11. ጥበብን መፈለግ፤ቅን ጥበብ በቅን አማርኛ፤ (ፍልስፍና) እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡
No comments:
Post a Comment