Wednesday, March 2, 2016

የአምባላጌው ጀግና የጦር አበጋዙ ፊታውራሪ ገበየሁ (አባ ጎራ)!!!


   የንጉሰ ነገስቱ የመሀል ጦር አዛዥ ፊታውራሪ ገበየሁ ከጣልያኖች ጋር በተደረገው በሁሉም ጦርነት የተመሰከረላቸው ጀግና ነበሩ፡፡ የአምባላጌውን ምሽግ በመስበር በጣሊያን ላይ የመጀመሪያውን የድል ደውል ያሰሙት እና ዋናው የድሉ ባለቤት እሳቸው ነበሩ፡፡በዚህም ምክንያት በወቅቱ የፈረንሳይ ጋዜጦች “የአምባላጌው የኢትዮጵያ ጀግና” በማለት እንዳወደሷቸው ተክለፃዲቅ መኩሪያ ፅፈዋል፡፡ የመቀሌውንም ጦርነት በደንብ ተካፍለው በጀግንነት ሲዋጉ እጃቸውን የቆሰሉ ሲሆን ፣ ከጦርነቱ በፊትም ራስ መኮንን ስለ እርቅ ጉዳይ በሚነጋገሩበት ጊዜ ገበየሁ እየተዋጉ ስላስቸገሩ እንደ አምባላጌው እንዳይዋጉ አስረዋቸው ሳለ በኋላ ግን ላይዋጉ አስምለው አስለቀቋቸው፡፡ በኋላም ጦርነቱ ሲጀመር የአምባላጌ የገፈቱ ድል ቀማሽ ፊታውራሪ ገበየሁ አባ ጎራ ነበር። በእለቱ ታሞ ስለነበር ዱላ እየተመረኮዘ ነበር ገደሉን የወጣው፤ ግና ይህ ሁኔታው ድልን ከመቀዳጀት አልከለከለውም። ስሙን ትንሹም ትልቁም ወዲያው አወቀው እና ገጣሚም እንዲህ ሲል አሞገሰው፦

የንጉሥ ፊታውራሪ ጎራው ገበየሁ
አላጌ በሩ ላይ ማልዶ ቢገጥማቸው
ለምሳም ሳይደርሱ ቁርሥ አደረጋቸው ተብሎ ተዜመለት፡፡

     በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ የአድዋ ድል ጉልህ ድርሻ አለው፡፡ በጦርነቱ ላይ የተሳተፉ ጀግኖች  ኢትዮጵያውያንም እንዲሁ፡፡ የአደዋ ጦርነት የተጀመረው በየካቲት 23 ቀን 1888ዓ.ም ከማለዳው ነበር፡፡ ውጊያው ከጠዋቱ 11፡30 ላይ በአራት ጄኔራሎች የሚመራው የጠላት ጦር በፊታውራሪ ገበየሁ ፣ በዋግሹም ጓንጉል ፣ በራስ ሚካኤል እና በራስ መንገሻ ጦር ላይ በሰነዘረው ጥቃት ተከፈተ፡፡ፊታውራሪ ገበየሁ በዚህ ጦርነት ፊት ለፊት የገጠሙት በእንዳ ኪዳነ ምህረት በኩል የመጣውን እና በጄኔራል አልበርቶኒ የሚመራውን የጠላት ጦር ነበር፡፡በጦርነቱ ፊታውራሪ ገበየሁ ከሰራዊቶቻቸው በመለየት ጎራዴያቸውን መዘው በዋናው የትግል አውድማ ፣ በተፋፋመ እና በቀለጠው ውጊያ ላይ ተወርውረው ገቡ፡፡ ዘለው እንደገቡም ከጀግናው ጓደኛቸው ከቀኝ አዝማች ታፈሰ ጋር እየፎከሩ የጠላትን አንገት በጎራዴ ሲቆርጡ እና ሲገነድሱ ቆይተው ከርቀት በተተኮሰ ጥይት ተመተው ወደቁ፡፡ ሌሎችም አዝማቾች እና መኮንኖች እንዲሁም ተራ ተዋጊዎች ሞተዋል፡፡ በጊዜውም እንዲህ ተገጠመ፡-

ያ ጎራው ገበየሁ ምን አሉ ምን አሉ
ያ ትንታግ ታፈሰ ምን አሉ ምን አሉ
እነ ደጃች ጫጫ ምን አሉ ምን አሉ
ተማምለው ነበር ከጦሩ ሲገቡ
አገሩን አቅንተው አደዋ ላይ ቀሩ፡፡

   ከዚህም በተጨማሪ ስለ ፊታውራሪ ገበየሁ አዲስ አበባ ድረስ ተማርኮ መጥቶ የነበረው የኢጣልያ መኰንን ፣ጆቫኒ ቴዶኒ የጻፈው ማስታወሻ እንዲህ ይላል…..  “በቢያን ኪኒና በማዘቶ ለሚመሩት መድፎች እየተመቱ አበሾች ወደ ኋላ ሲያፈገፍጉ አይቶፈሪ አንዴት ትሸሻላችሁ እኔ እንዴት እንደምሞት ለንጉሱ ሄዳችሁ ንገሩበማለት ፈረሱን በአለንጋ አስነስቶ በግልቢያ በሚዘንበው የመድፍ ጥይት መካከል ገባ፡፡እሱን ሲያይ ሁሉም እየሮጠ ተከታትሎ ገብቶ ከመድፈኞቹ ጋር ተጨፋጭፎና ገድሎ መድፈኞችን ማረከ፡፡ የገበየሁ ሬሳ ከወደቀበት ቦታ የእኛዎቹ ጀግኖች አብረው በመውደቅ የእርሱን ሬሳ አከበሩትበማለት ገልጾታል፡፡


   እነዚህ ጀግኖች አይረሴ የአድዋ ጌጥ እና የጥቁር ህዝቦች ሰማዕት ናቸው፡፡ ፊታውራሪ ገበየሁ ገና ወደ አድዋ ሲዘምቱ ተናዘውም ነበርስሸሽ ከኋላዬ ከተመታሁ አሞራ ይብላኝ፣ እኔ እንደ አባቶቼ አይደለሁምና ወግ አይገባኝም፤ ከፊት ለፊት ስፋለም ከወደቅሁ ግን እሬሳዬን /አፅሜን/ ትውልድ ቦታዬ ውሰዱልኝአሉ፡፡ እንደተባለውም ሆነ በፅኑ ሲፋለሙ ስለ ሀገራቸው ነፃነት አደዋ ላይ ወደቁ፡፡ በሕይወት እያሉ:-

የአድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው 
ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰውየተባለላቸው ገበየሁ(በአካባቢው አጠራር ጎራው ገበየሁ) አድዋ ሥላሴ ተቀብረው ከቆዩ በኋላ አፅማቸው ወደ አምባላጌ ጊዮርጊስ ተወሰደ፡፡ በቃል ኪዳናቸው መሠረት ከሰባት ዓመት በኋላም አፅሙ በትውልድ አካባቢያቸው በአንጎለላ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን አረፈ፡፡ ከአድዋ ድል በኋላ በጃንሜዳ የጦር አበጋዞች በፈረስ ሲያልፉ የፊታውራሪ ገበየሁ ፈረስ ብቻውን ከፊት ሲያልፍ ያዩት አፄ ምኒልክ ተንሰቅስቀው እንዳለቀሱም ይነገራል፡፡ ክብር ለአድዋ ጀግኖች ሰማዕታት ይሁን….. !!!
   
                           ምንጭ ፡- ተክለጻዲቅ መኩሪያ እና ሌሎችም


No comments:

Post a Comment