ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ (ዶክተር ቻርለስ ማርቲን) ከአባታቸው አዛዥ እሸቴ ወ/ማርያም እና ከእናታቸው ወ/ሮ ደስታ በ1857 ዓ.ም. በጎንደር አካባቢ ተወለዱ፡፡ ሐኪም ወርቅነህ የ3 ዓመት ህፃን ሳሉ ቤተሰባቸው አፄ ቴዎድሮስን ተከትሎ ወደ
መቅደላ አምባ ሄዶ ነበር፡፡ ከጦርነቱ ፍፃሜ በኋላ የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ አለማየሁ ቴዎድሮስ እና ወርቅነህ እሸቴ ተማርከው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ከኮሎኔልቻርለስ ቻምበርሊን ጋር በመሆን በወቅቱ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ወደ ነበረችው ህንድ ወሰዷቸው፡፡ ሕፃን ወርቅነህ በሕንድ አገር ለአራት ዓመት እንደተቀመጡ አሰዳጊያቸው ቻርለስ በሞት ስለተለዩ ኮለኔል ማርቲን የተባለው ሰው ተቀብሎ ከአንድ የሚሽን ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርት እንዲቀጥሉ አደረገ፡፡
የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ፑጃብ በምትባለው ከተማ ተከታትለው ሲጨርሱ ለዩኒቨርሲቲ የሚያበቃ ውጤት ስለበራቸው በፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ተከታተሉ፡፡ በዚያም በህክምና ሙያ ተመርቀው በረዳት ሐኪምነት ሰርተዋል፡፡ ከሁለት ዓመት አገልግሎት በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ እንግሊዝ ሄደው በግላስኮ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በቀዶ ጥገና ሙያ በታላቅ ክብር ተመርቀዋል፡፡
በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው ባስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤት የሀኪሞች ማሕበር “የበቃ ጥቁር ሀኪም”
የሚል ሽልማት ተበረከተላቸው፡፡ ሀኪም ወርቅነህ እንደተመረቁም የእንግሊዝ መንግስት ራሳቸውን ችለው ቀዶ ጥገና ስራቸውን እንዲያከናውኑ ያኔ በእንግሊዝ ስር ወደነበረችው በርማ ላካቸው፡፡ በወቅቱ ለአጼ ምኒልክ ቅርበት ከነበራቸው ምሁራን መካከል አለቃ አጽሜና አለቃ ታዬ የሚባሉት ስለሃኪም ወርቅነህ ዝና አውሮፓ ሳሉ የሰሙትን አንድ በአንድ ነገራችው፡፡ አጼ ምኒልክም ሐኪም ወርቅነህ ወደ
ኢትዮጵያ መጥተው የህክምና ሥራ እንዲሰሩ እንዲፈቅዱላቸው ለእንግሊዝ መንግሥት ደብዳቤ ጻፉ:: የእንግሊዝ መንግሥት “በሁለታችን መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማጥበቅ ቻርልስ ማርቲንን ስንልከው ለእርስዎም ያለንን አክብሮት ለመግለጥ ነው” በማለት መፍቀዳቸውን በመግለፅ ሐኪም ወርቅነህን ላኳቸው፡፡ ሐኪም ወርቅነህ ያኔ የ36 ዓመት ጎልማሣ ነበሩ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው ጥቂት ዓመታት ያህል እንዳገለገሉ በ1894 ዓ.ም ኦጋዴን ውስጥ በኢትዮጵያና በሶማሊያ ድንበር በተደረገ ጦርነት፤ በጦርነቱ ቁስለኞችን ከቦታው ድረስ ሄደው ያከሙት ሐኪም ወርቅነህ ናቸው፡፡ በ1895 ዓ.ም እንደ ገና ወደ እንግሊዝና በርማ ሄዱ፡፡ በዚያም አምስት ዓመት ሲቀመጡ ከእንግሊዛዊትና ከበርማ ሴቶች ልጆችን አፍርተዋል። ከዛን ወዲህ በተለያዩ ጊዜያት ወደ አገራቸው በመምጣት የተለያዩ ተግባራትን ያከናወኑ ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜ በ1903 ዓ.ም በመጡበት ወቅት ከወ/ሮ ቀፀላ ወርቅ ቱሉ ጋር ትዳር የመሠረቱ ሲሆን ትዳራቸው ሰምሮ አምስት ወንዶችና ስምንት ሴት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ሐኪም ወርቅነህ በድጋሚ በመጡ ጊዜ አጼ ምኒልክ የአውሮፓን ስልጣኔ ወደ
አገራቸው እያስገቡ ነበር፡፡ ሐኪም ወርቅነህ በማስተማርና በህክምና የቻሉትን ያህል አጼ ምኒልክን ደግፈዋል፡፡
አጼ ምኒልክ በታመሙ ጊዜ በመጀመሪያ ሙሴ ሃርማኒየር ሲያክሙ ቆይተው በኋላ ሐኪም ወርቅነህ በቦታው ተተክተው ማከም ቀጠሉ፡፡ በ1906 ዓ ም (ከአጼ ምኒሊክ እረፍት በኋላ ሐኪም ወርቅነህ ወደ በርማ ተመለሱ:: በአጠቃላይ
በሕንድና በበርማ ለ32 ዓመታት አገልግሎት ከሰጡ በኋላ ጠቅልለው ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ፋሺስት ኢትዮጵያን እስከ ወረረበት ድረስ በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በአዲስ አበባ የሚገኘውን የፍልውሀ ድርጅት አቋቁመዋል፤ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሆነው ሰርተዋል፤ የየካቲት 12 ሆስፒታል(የቀድሞው ቤተ - ሳይዳ)፣ የጅማ መንገድ እና የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሲቋቋሙ የበላይ ተቆጣጣሪ ሆነው ሰርተዋል፡፡
በ1927 ዓ.ም በአባይ ወንዝ ላይ ለሚገነባው ግድብ እርዳታ ለማሰባሰብ ወደ አሜሪካ የተጓዘውን ቡድን መርተዋል ፣ በ1920 ዓ.ም ለቆመው ዘመናዊ ፍርድ ቤት አዛዥ ተብለው በተሰጣቸው ሹመት በቅንነት አገልግለዋል፣ የጨርጨር አውራጃ ገዢ በመሆን የሰሩ ሲሆን ኢትዮጵያ በነበረባት የተማረ የሰው ኃይል እጥረት የተለያዩ ሙያ ያላቸው 21 ህንዳውያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሰሩ የግል ድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነውም ሰርተዋል፡፡ በ1927 በጄኒቫ የመንግስታቱ ማሕበር የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው የተላኩት ሀኪም ወርቅነህ በዛው እያሉ ኢትዮጵያ በፋሺስት እጅ በመውደቋ ወደ እንግሊዝ በማቅናት
ከንጉሱ ጋር በመሆን የተለያዩ የዲፐሎማሳዊ ሥራዎችን በማከናወን እና አገራቸውን ለመርዳት የሚያስችሉ ዝግጅቶችን በማደራጃት በወቅቱ ከኢትዮጵያውያንና ከኢትዮጵያ ወዳጆች ከፍተኛ እርዳታ እንዲገኝ የላቀ ሚና ተጫውተዋል፡፡
ሐኪም ወርቅህ የሚያደርጉትን የተቃውሞ ትግል ለመበቀል ይመስላል ጣሊያኖች ዮሴፍ ወርቅነህና ቢንያም ወርቅህ የተባሉ ልጆቻቸውን በ1929 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ገድለውባቸዋል:: ከሐኪም ወርቅነህ ታዋቂ ልጆች መካከል ዶ/ር ዮሃንስ ወርቅነህ፣ አስቴር ወርቅነህና ኤልሳቤጥ ወርቅነሀ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከነጻነት መልስ ለተወሰነ ጊዜ ወደ ህንድ ሄደው የቆዩ ሲሆን በመጨረሻ ከቤተሰባቸው ጋር ወደ
አገራቸው ለመመለስ በቅተዋል፡፡ በ1952 ዓ.ም ማለትም በተወለዱ በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው በየካ ሚካኤል ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡
No comments:
Post a Comment