Saturday, April 16, 2016

“የመሰንቆው ሊቅ” ጌታመሳይ አበበ በተወለደ በ72 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ ፡፡


  የሙዚቃው ሊቅ  ጌታመሳይ አበበ በሙዚቃው ተለክፎ እጁን ለሙዚቃ የሰጠው ገና በልጅነቱ ነበር፡፡ በግል ጥረቱም ማሲንቆ የመጫወት ልምዱን አዳበረ፡፡ 1953 . ከሀገር ቤት ወዲህ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት ልምምድ ሲያደርግ ከቆየ በኋላ በአንዳንድ ተፅዕኖዎች ምክንያት ትያትር ቤቱን ተሰናብቷል፡፡ 1954. (በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የባህል ማዕከል የኢትዮጵያ ኦርኬስትራን ተቀላቅሎ  በድምጻዊነትና መሰንቆ ተጫዋችነት በርካታ ዘፈኖችን ተጫውቷል፡፡ የአገረሰብ የሙዚቃ ክፍል ኃላፊና አደራጅ በመሆንም አገልግለዋል።
 

   በ1960. ወደ ሀገር ፍቅር ትያትር ቤት ተዛወረ፡፡ በሀገር ፍቅር ትያትር ቤት ቆየታውም ከዘፋኝነት ባሻገር የትያትር ሙያን በመማር ከአስር በላይ በሚሆኑ ትያትሮች ከእውቅ አርቲስቶች ጋር በመሆን ተውኗል፡፡ ለአብነትም የአቤ ጉበኛየደካሞች ወጥመድ የብርሃኑ ዘሪሁንየለውጥ አርበኞችእና የጌታቸው አብዲስንት አየሁትያትሮች ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡የመሰንቆው ሊቅጌታመሳይ አበበ 200 በላይ ዜማዎችን ተጫውቷል፡፡ በዜማ ድርሰት፣ በድምጻዊነት፣ በኃላፊነት፣ በመምህርነት እንዲሁም የባህል ቡድኖችን በመምራት በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓና በአፍሪቃ በመዟዟር የኢትዮጵያን የባሕል ጨዋታ በተለያዩ አለም አቀፍ መድረኮች እንዲንፀባረቁ እና እንዲተዋወቁ የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል።

   አገራዊ እሴትን፣ የአገር ፍቅርንና ጀግንነትን የሚያንጸባርቁ ሥራዎችን በማቅረብ የሚታወቀው ጌታመሳይ አበበየሽምብራው ጥርጥርሆብዬ እመጣለሁየኔ አያልእናት ውብ አገሬወሸባዬዳይመኔየመኖሪያ ቤቴሰላሜ ሰላሜእና ሌሎችም አገራዊ ስሜትን ከፍ የሚያደርጉ ሥራዎቹ ተጠቃሽ ናቸው። 1996 . ባጋጠመው የጭንቅላት ዕጢ አማካኝነት ለ12 ዓመታት በህመም ላይ የቆየ ሲሆን መናገር እና መንቀሳቀስ በማይችልበት ደረጃ ይገኝ እንደነበርም ሚያዚያ 6/2008. በብሄራዊ ባህል ማዕከል ተዘክሯል፡፡ በባህል ማዕከሉ በተካሄደው የዝክር ዝግጅት ላይ በዊልቸር እገዛ ተገኝቶ የታደመው አንጋፋው ከያኒ የካባ ፣ የአገር ባህል ልብስ ፣ የዋንጫና የምስክር ወረቀት ሽልማቶችም ተበርክተውለት ነበር።


   የጠለቀ የመሰንቆ ዕውቀትና ችሎታውየመሰንቆው ሊቅየሚል መጠሪያ አጎናጽፏቸዋል። ጌታመሳይ አበበ በአሩሲ ክፍለ ሀገር ልዩ ስሙ አልባሶ በተባለ ቦታ 1935. እንደተወለደ መረጃዎች ይጠቁማሉ። አንጋፋው የጥበብ ሰው በነገው ዕለት ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት ጀምሮ አድናቂዎቹ ፣ ከያኒያን እና ቤተሰቦቹ በተገኙበት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል የቀብር ስነ ስርዓቱ ይፈፀማል፡፡ ለቤተሰቦቹ ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ እና አድናቂዎቹ መፅናናትን እንመኛለን፡፡

No comments:

Post a Comment