“ገዴ” እና “ቢሰጠኝ” የተሰኙ
ሁለት አልበሞች አሏት፡፡ እ.ኤ.አ በ2004 “እወድሃለሁ” በሚለው ስራዋ የኮራ ሙዚክ አዋርድ ተሸላሚ ናት፡፡ በቅርቡ ደግሞ በናይጄሪያ
ሎጎስ በተካሄደው ኦል አፍሪካ ሙዚክ አዋርድስ /አፍሪማ/ በምስራቅ አፍሪካ ምርጥ የሴት ድምፃውያን ምድብ አሸናፊ ሆናለች፡፡ ለተለያዩ
ፊልም እና ድራማዎች ሳውንድ ትራክ /ማጀቢያ ሙዚቃ/ ሰርታለች፡፡ ቀደም ሲል በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 በሚቀርበው የ “አይሬ” ፕሮግራም
ትሰራ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 “ዜማ ፍቅር” የተሰኘ ፕሮግራምን ታቀርባለች፡፡ ሶስተኛ አልበሟንም
ሰርታ አጠናቃለች፤ አርቲስት ፀደንያ ገብረማርቆስ፡፡
በቀድሞው ደብረ ያሬድ (ሜጋ ትያትርም) ለተወሰኑ
አመታት ሰርታለች፡፡ በእንግሊዘኛ ዘፈኖች ሙዚቃን አሀዱ ያለችው አርቲስት ፀደንያ ገብረማርቆስ ቀስ በቀስ ወደ አማርኛ ስራዎች በማምራት
ሁለት ያህል አልበሞችን እና በርከት ያሉ ነጠላ ዜማዎችን ለአድናቂዎቿ አድርሳለች፡፡ “ገዴ” የተሰኘው የመጀመሪያ አልበሟ በኬንያዊው
አቀናባሪ ዴቪድ ኦቴኖ የተሰራ ሲሆን አምባሰል ሙዚቃ ቤት ነው የታተመው፡፡ “ቢሰጠኝ” የተሰኘው አልበሟ ደግሞ ጥበቡ ወርቅዬ ኢንተርቴይመንት
የታተመ ሲሆን ቅንብሩን ዳግማዊ አሊ ሰርቶታል፡፡
ከኤዘር ኦርኬስትራ ጋርም አልያንስ - ኢትዮ ፍራንሲስ ከውጪ በመጡ የሙዚቃ ባለሙያዎች ታጅባ “ባቲ” የተሰኘ ስራዋን አቅርባለች፡፡ ከዚያም በኋላ ከጋሽ መሀሙድ አህመድ ጋር በፈረንሳይ ሀገር ዝግጅቶቿን አሳይታለች፡፡ ድምፃዊት ፀደንያ ገብረማርቆስ ከድምፃዊነት፣ ዜማ ደራሲነት እና ፕሮግራም አቅራቢነት ባሻገር ቀደም ብላ ማስታወቂያዎችንም ትሰራ ነበር፡፡ ለአብነትም አብወለድ ፣ ገርልጊ ፣ ካዲስኮ እና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡
ትውልዷ እና እድገቷ እዚሁ መዲናችን አዲስ አበባ
የሆነው ፀደንያ የመንታ ወንድ ልጆች እናት ናት ፡፡ ቀሪ ዘመኗም የስኬት እና ብልፅግና እንዲሆን በመመኘት እኔ ፅሁፌን በዚሁ ላብቃ
ሌላውን እናንተ ጨምሩበት ……