Saturday, October 19, 2013

የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያን እድገት አደነቀ


የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ ባለፉት አስር አመታት ያሳየችው አስደናቂ እድገት ሀገሪቱ የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች ለማሳካት በሚያስችላት ደረጃ እንዳደረሳት ገለፀ፡፡


   የአፍሪካ ልማት ባንክ እና ኢትዮጵያ-ጥምረት ለሁሉን አቀፍ እድገት በሚል በቅርቡ ባወጣው ሪፖርቱ ባንኩ ሀገሪቱ የምታካሂደው ግዙፍ የመሰረተ ልማት ግንባታና የግብርናው ዘርፍ ገበያ ተኮር መሆን ለባለ 11 በመቶው እድገት ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ ጠቅሷል፡፡ ባንኩ የመንግስት ፖሊሲ ለሁሉን አቀፍ እድገት ትልቅ ሚና እንደነበረው አመልክቶ 69 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ በጀት  ደሀ ተኮር በሆኑ ስራዎች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
  የመንግስት ጥንቃቄ የተሞላበት የገንዘብ ፖሊሲ ከሁለት አመታት በፊት እስከ 40 በመቶ የነበረውን የዋጋ ግሽበት ምጣኔ ወደ 7.7 በመቶ እንዳወረደው ባንኩ በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ ባንኩ የሀገሪቱን የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድን ከግምት በማስገባት ትብብሩን እንደሚቀጥል ጠቁሟል፡፡ የሀገሪቱ ሁሉን አቀፍ እና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ መስራት አስተማማኝ ውጤት እንደሚያመጣ እምነት አለኝ ያለው ባንኩ ከሀገሪቱ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳውቋል፡፡

   ባንኩ በቅርቡ የኢትዮ ጂቡቲን የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ የኬንያ ኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታና የሞምባሳ ናይሮቢ አዲስ አበባን የመንገድ ስራ እና የገጠር ውሀ አቅርቦትና ንጽህና ፕሮግራም በፋይናንስ እየደገፈ ያለውም ከዚህ እምነቱ በመነሳት ስለመሆኑ ተናግሯል፡፡ ኢትዮጵያ ባንኩን የዛሬ 50 አመት ከተቀላቀለችበት ጊዜ ጀምሮ 3 ነጥብ 75 ቢሊየን ዶላር ብድርና እርዳታ ያገኘች ሲሆን ባንኩ ከፍተኛ ብድር ከሰጣቸው መካከል ስድስተኛዋ ሀገርም እንደሆነች ሪፖርቱ መጠቆሙን የኢሬቴድ ዘግቧል፡፡

No comments:

Post a Comment