Tuesday, March 24, 2015

“አዞ ያስለቅሳል እንጂ አያለቅስም....”


     አዞ ሲበላ ያለቅሳል ይባላል የሚበላ ከሆነ ለምን ያለቅሳል ፤ እውንስ አዞ ያለቅሳልን ? አዞ ቆዳው በጣም ጥቅጥቅ ነው፡፡ ስለዚህ በላብ መልክ በቆዳው የሚወጣለት ነገር የለም፡፡ በጥርሶቹ ደግሞ ቁርጥ እያደረገ ዋጥ ያደርጋል እንጂ አያኝክም ፣ አያላምጥም፡፡ ስለዚህ በቆረጠው ልኬት ወደ ውስጥ እንዲገባ ነው የሚያደርገው እና አንዳንድ ከፍ ያሉ ነገሮች ሲያጋጥሙት ጉሮሮው ይጨናነቃል፡፡ በዚህ ጊዜ ላቡ በአይኑ ዱብ ዱብ ይላል፡፡ ይህ ደግሞ ላብ እንጂ እምባ አይደለም፡፡ አዞ ያስለቅሳል እንጂ አያለቅስም ስትል የአርባ ምንጭ አዞ ማደለቢያ የጉብኝት ባለሙያ ወ/ሪት ህይወት አሰፋ አጫወተችኝ፡፡

     አስጎብኛችን ጨዋታ አዋቂ ናት ፡፡ እያዋዛች ቁም ነገር ማስኮምኮሟን ቀጥላለች…… በአለማችን ላይ 25 አይነት የአዞ ዝርያ አይነቶች አሉ፡፡ በአፍሪካ 4 ዓይነቱ ሲገኙ በኢትዮጵያ ደግሞየናይል አዞየተባለው ብቻ ነው የሚገኘው፡፡ 

  የናይል አዞ ካሉት ሁሉ ተፈላጊ ተመራጭ ተወዳጅ ሲሆን ግን ኃይለኛ ቢሆንም ካልነኩት አይነካም፤ ከነኩት ግን አይለቅም ፡፡ ልክ እንደ ኢትዮጵያዊ ነው ባህሪው ስትል አከለችልኝ፡፡   አዞዎች ከእንቁላል ሲፈለፈሉ መናከስ ይጀምራሉ፤ ምክንያቱም ከጥርስ ጋር ስለሚፈጠሩ፡፡ ተንቀሳቃሽ ምላስ የላቸውም፡፡ ጥርሳቸው ግን ከ62 - 66 ይደርሳል፡፡ አዞ አያኝክም ፣ አያላምጥም ፣ አያጣጥምም ስለዚህ ቁርጥም እያደረገ ዋጥ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ 



   የጉብኝት ባለሙያዋ ወ/ሪት ህይወት አንዳጫወተችኝ በማዕከሉ ያሉ አዞዎች ከ3 - 6 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ለእርድ የሚፈለጉበት /ቆዳቸው የሚፍለግበት/ ጊዜ ነው፡፡ ሲታረዱም የራሳቸው የሆነ መያዣ ዘዴ እና መምቻ ጥይት አለ፡፡ በዚህም ኢላማ የሚችል ሰው አናታቸው ላይ ይመታቸውና በማጅራታቸው/በጀርባቸው/ በኩል ይታረዳሉ፡፡


      አንድ አዞ ከ120 -150 አመት መኖር ይችላል፡፡ ከ7 - 8 ሜትር መርዘም ይችላል፡፡ ከ500 - 700 ኪ.ግ መመዘን ይችላል፡፡ ናይል ኮሮኮዳይል (ትልቁ አዞ ) ማለት ነው፡፡ አንድ የአዞ እንቁላል ከ40 - 140 ግራም ይመዝናል፡፡ አንድ አዞ በአንድ ጊዜ ከ30 - 70 እንቁላል ትጥላለች፡፡ 30ም ሆነ 70 በአመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው የምትጥለው፡፡  ከጣለችው እንቁላል ውስጥም 75 በመቶ የመፈልፈል እድል አላቸው፡፡ ለመፈልፈል ከእሷ የሚፈልጉት ነገር የለም፡፡ በአሸዋው ሙቀት ብቻ ነው የሚፈለፈሉት፡፡


     የፆታቸው ሁኔታም የሚወሰነው በአሸዋው ሙቀት እና ቅዝቃዜ ነው፡፡ ሙቀቱ ከፍተኛ ከሆነ ወንዶች ይሆናሉ፤ ቀዝቀዝ ያለ ከሆነ ደግሞ ሴቶች በማለት አስጎብኚዋ ወ/ሪት ህይወት መረጃውን በሳቅ እና በፈገግታ እያዋዛች ማስኮምኮሟን ቀጠለች፡፡ አዞ ለአቅመ አዞ የሚደርሰው ከ10 ዓመት በኋላ ነው፡፡ በማዕከሉ አንድ ሴት እና አንድ ወንድ አዞ ከእርድ ውጪ ሆነው በአንድ ገንዳ ውስጥ ለጎብኚዎች እይታ ተብለው ተቀምጠዋል፡፡ እነዚህ አዞዎች 26 ያህል አመታትን ስላስቆጠሩ የማዕከሉ ፈርጥ ናቸው፡፡ እንደ አስጎብኚያችን እከ እና ትርፌ የሚል ቅፅል ስምም ተሰጥቷቸዋል፡፡


     እኔም የዛሬ ጡመራዬን እዚህ ላይ ገታ ላድርግ፤ በሌላ ጊዜ ሌሎች መረጃዎች ይዤላችሁ ከች እላለሁ ፡፡ በተረፈ ግን እናንተ ጨምሩበት የምታውቁትንም መረጃ አካፍሉኝ…..

No comments:

Post a Comment