Monday, March 9, 2015

“ፈኢማ” …… ለአፋሮች ምንድን ነው !!!


   
   ከአፋር እሴቶች መካከልፈኢማአንዱ ነው፡፡ ከአፋር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ባገኘነው መረጃ መሠረት፣ፈኢማየብርቱ ወንዶች ስብስብ የቡድን ስም ሲሆን የፈኢማ አባላት ሰላምና ፀጥታን የማስከበር፣ ፍርድን የማስፈፀም፣ የታመመን የመረዳት፣ እንግዳን የማስተናገድ በሰርግና በመሰል በዓላት ሥራ የማገዝ፣ በቀብር ወቅት መቃብሩን የማዘጋጀትና ሥርዓቱን የማስፈፀም ወዘተ ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡ በእያንዳንዱ ጎሣ በብርታታቸውና ንቃታቸው የተመረጡ ወንድ ወጣቶችና ጎልማሶች ተውጣጥተውፈኢማይመሠርታሉ፡፡

 
ፈኢማበመባል የሚታወቀው የአፋር ብሔረሰብ ማኅበራዊ የቡድን አደረጃጀት በአንድ ሰው አቅም የማይከናወኑ ሥራዎችን ተጋግዞ ለማቃለል የብሔረሰቡ አባላት የሚጠቁሙበት ባህላዊ የማኅበራዊ ቡድን አደረጃጀት ነው፡፡ ለሥራ ተሳታፊዎች ከሥራ በኋላ ባንድ ላይ መብላትና መጠጣትም ያለ ባህል ነው፡፡ ከብሔረሰቡ ባህላዊ ማኅበራት መረዳዳት፣ በችግር ጊዜ የሚፈለገውን በማዋጣት የተለያዩ ችግሮችን ለማቃለል በገንዘብ፣ በጉልበትና በምክር ድጋፎች ማድረግን ያጠቃልላል፡፡
 

  ለመጥቀስ ያህልም ከብሔረሰቡ እጅግ ደሃ ወይም አቅመ ደካማ የሆነውን መልሶ ለማቋቋም በገንዘብና በዓይነት ድጎማ ማድረግን፣ በሰርግ ወቅትም ቢሆን ለጋብቻ የሚዘጋጀው ሰው ለሚገጥመው ችግር ቡድኑ ገንዘብ በማዋጣት ችግሩን ለመፍታት የሚያገለግል ነው፡፡ ሴቶችም በተመሳሳይ ፈኢማ ይመሰርታሉ፡፡ ይህ የሴቶች ፈኢማ ሴቶች ያለባቸውን የቤት ውስጥ ዕቃና የገንዘብ ችግር ለማቃለል አባላቱ ገንዘብ በማዋጣት እንደ ችግራቸው ቅድሚያ እየተሰጣጡ ሁሉንም በየተራ የሚረዳዱበት ዘዴ ነው፡፡


   “ፈኢማየዕድር መንፈስ ቢኖረውም የአፋር ብሔረሰብ የመረዳዳት ባህል ከሌሎቹ ብሔረሰቦች ለየት ይላል፡፡ የራሱ ባህልና ወግም አለው፡፡ በአፋር ብሔረሰብ ውስጥ ፈኢማ ሲባል ወንድና ሴት አይቀላቀልም፤ ወንዶች የራሳቸው ፈኢማ ሲኖራቸው ሴቶችም እንዲሁ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ የአፋር ብሔረሰብን ባህል ዕድሜ የሰጠው ከጥንት አያትና ቅድመ አያቶች ጀምሮ እየተወራረሰ የመጣው የፈኢማ ባህል እንደሆነ የብሔረሰቡ ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡

 
ፈኢማበአጠቃላይ ጽንሰ ሀሳቡ በመረዳዳት ላይ በመመርኮዝ ችግሮች ሲከሰቱ የሚከናወን ነው፡፡ ፈኢማ በአባላቱ ዕውቅና የተሰጠው አለቃ/ሰብሳቢ/ ይኖረዋል፡፡ በሰብሳቢው አማካይነት ሥርዓቱን ያልተከተለ አባል ይቀጣል፡፡ ስለዚህ አባላት ለሥርዓቱ ተገዥ ይሆናሉ፡፡ በአፋር ብሔረሰብ ብዛት ያላቸው ፈኢማዎች ሲኖሩ ማንኛውም የብሔረሰቡ አባል በመረጠው ፈኢማ የመግባት መብት አለው፡፡ ነገር ግን ከነበረበት ፈኢማ ወጥቶ ወደ ሌላ ፈኢማ ለመግባት ከመጀመሪያው ፈኢማ ለምን እንደወጣ በቂ ምክንያት ካላቀረበ ሌላኛው ፈኢማ ለአባልነት አይቀበለውም፡፡ ቀደም ሲል እንደተገለፀው ፈኢማዎች የወንድና የሴት ከመሆናቸውም ሌላ አንዱን ፈኢማ ከሌላው የሚለይበት ሁኔታ የለም፡፡ ሴቶች የራሳቸው ደንብ አላቸው ወንዶችም በተመሳሳይ፡፡


  የሴቶች ፈኢማ በሰርግና በለቅሶ ጊዜ ምን መልክ እንዳለው ስንመለከት ሰው በሚሞትበት ጊዜ ‹‹ፈኢማ›› ይጠራል፡፡ በዚህም ጊዜ የተለየ የአለባበስ ባህል አለ፤ ወደ ለቅሶ የሚመጡ ሴቶች ሁሉ ፀጉራቸው ላይ ሻሽ ያስራሉ፣ ባዶ እጃቸውን አይመጡም፡፡ ይህም የሚደረገው ሀዘንተኛውም ሆነ ዘመዶቹ ምንም ዓይነት ወጭ እንዳያወጡና ፈኢማው ከጎናቸው መሆኑን ለማሳወቅ ነው፡፡ ሰርግንም በተመለከተ በፈኢማዎች በኩል ጥሪ ይደረጋል፡፡ በሰርግ ጊዜ ብቻ የሚዘፈን ባህላዊ ጨዋታ ይጫወታሉ፡፡ በጭፈራውም ወቅት ፈኢማው ቀድሞ ሳይጫወት ሌላ ሰው መጫወት አይችልም፡፡ ቀድሞ የሚጫወት ካለ ይቀጣል፡፡ ጨፍረው ከዘመድ አዝማድ የሚገኘውን ሽልማት ከፊሉን ለሙሽራው ወይም ለሙሽራዋ እናት ይሰጣሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ‹‹ፈኢማ›› ከፍተኛ ክብር ስላለው በድግሱ ወቅት ለአባላት የሚዘጋጅላቸው ምግብ የተለየ ነው፡፡


   የሴቶች ፈኢማ ባህልን ከማስጠበቅ አኳያ ከፍተኛ ድርሻ ስላለው ማንኛውም የአፋር ብሔረሰብ እናት ይቀርበኛል ወይም ይስማማኛል በሚሉት ፈኢማ ይደራጃሉ፡፡ ፈኢማ የአፋር ብሔረሰብን ያስተሳሰረና የማንነቱ መግለጫ ስለመሆኑ አብዛኛው የብሔረሰቡ አባላት አጽንኦት ሰጥተው ነው የሚነጋገሩት፡፡ ታዲያ ይህ አኩሪ የሆነው ባህላቸው በዕድሜ የገፉ ሰዎች ባለፉ ቁጥር ለተተኪው ትውልድ ይህ ባህል ሳይጓደል እንዴት ነው የሚተላለለፈው የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህበቃል ያለ ይረሳል በጽሑፍ ያለ ይወረሳል” ነውና የሚመለከታቸው አካላት ሊያስቡበት ይገባል፡፡

No comments:

Post a Comment