Saturday, October 4, 2014

በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሊጠገን ነው


  የዓለም ቅርስ የሆነው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን በ670 ሺህ ዶላር በሚቀጥለው ወር እንደሚታደስ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።በአማራ ክልል ከሚገኙት 11 የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን መካከል ቤተ ገብርዔልና ቤተ ሩፋኤል በተፈጥሮ አደጋና የጎብኚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ለከፍተኛ ጉዳት መጋለጡን በባለሥልጣኑ የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች ልማት ዳይሬክተር ወይዘሮ ፀሐይ እሸቱ ገልጸዋል።
 

  በልደት (የገና) በዓል ብቻ  ላሊበላ በየዓመቱ ከ 80 ሺህ እስከ 100 ሺህ የሚደርሱ ጎብኚዎች የምታስተናግድ ሲሆን በርካታ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በዓሉን ለማክበር በሥፍራው ይታደማሉ። እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ በርካታ ቁጥር ያላቸው አማኞችና ጎብኚዎች ወደ ሥፍራው መጓዛቸው ለዐብያተ ቤተ ክርስቲያኑ መጎዳት እንደ አንድ ምክንያት ሆኗል። 
 

  ይህን ጥንታዊና ታሪካዊ የሆነ ቅርስ መቀመጫው ኒው ዮርክ የሆነውና ለትርፍ ያልተቋቋመው የዓለም አቀፉ ‘የሞኑመንት ፈንድ’ ድርጅት ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ጋር በመተባበር ይታደሳል። በቀጣዩ ጥቅምት ወር እድሳቱ የሚጀመር ሲሆን በዚህ አመት ውስጥም ይጠናቀቃል ተብሎ ይገመታል፡፡

No comments:

Post a Comment