Sunday, October 19, 2014

አርቲስት ፍቅርተ ደሳለኝ ማናት……. ?


   አርቲስት ፍቅርተ ደሳለኝ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ቀበና አካባቢ ነው ተወልዳ ያደገችው፡፡ ወደ ሙዚቃው አለም ስትገባም የብዙነሽ እና የሂሩት በቀለ ስራዎችን በማንጎራጎር ነበር፡፡ ይህ ግንኙነትም ተጠናክሮ በናይጄሪያ ሎጎስ እና በሱዳንም ስራዎቻቸውን አብረው አቅርበዋል፡፡ በ1958ዓ.ም የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ (የአሁኑ ብሄራዊ ቲያትር) በድምፃዊነት ከመቀጠሯ አስቀድሞ በምሽት ክበብ ውስጥ ትሰራ ነበር፡፡ብሄራዊ ቲያትር የገባችውም በቴሌቭዥን ስትዘፍን የተመለከቷት የዛን ጊዜው የብሄራዊ ቲያትር ስራ አስኪያጅ ችሎታዋን አድንቀው ወደ ቲያትር ቤቱ እንድትመጣ በመጠየቃቸው ነበር፡፡በወቅቱ የተሰጣትን ፈተና በአጥጋቢ ሁኔታ በማለፏ በ100 ብር ደምወዝ ተቀጠረች፡፡
 
   በአንድ ወቅት ስራዋን በቀጥታ ስርጭት ስታቀርብ የዘፋኝ ስም ሲፃፍ የአባቷን ስም ቀይራ ነበር፡፡ ከቤተሰቦቿ ለመደበቅ እና በወቅቱ በድምፃውያን ላይ ይሰነዘር ከነበረው ትችት ለመሸሽ ስትል እንደሆነም ትናገራለች፡፡ እናም በጊዜው ፍቅርተ ደሳለኝ የነበረ ስሟ ፍቅርተ ግርማ ተብሎ በቴሌቭዥን በመታየቱ በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆና ነበር፡፡ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ቲያትር ቤትን በተቀላቀለችበት ጊዜ ቲያትር ቤቱ በስሩ 3 ኦርኬስትራዎች ነበሩት (ያሬድ፣ ዳዊት፣ እዝራ) ፡፡ አርቲስት ፍቅርተ ደሳለኝም በያሬድ ኦርኬስትራ ስር ሆና የተለያዩ የሀገራችን ክፍል ተዘዋውራ ሰርታለች፡፡

    ከሰራቻቸው ዘፈኖቿ መካከል ጥቂቶቹን እናንሳ፡-የሻለቃ ግርማ ሀድጎ ግጥም እና ዜማ የሆነው የመጀመሪያ ስራዋ “የፍቅር ምድጃ”፣ “ሰው በናፍቆት አይሞትም”፣ “ኮተት” የተሰኘው የሲራክ ታደሰ ድርሰት፣ “ቤትም እኮ ነበር”፣ “የመኖሬ ተስፋ”፣ “የኔ አለኝታ”፣ በ1963ዓ.ም የተቀረፀው “ባሌ ነው ህይወቴ”፣ በጎዳና ተዳደሪ ልጆች ላይ የሚያተኩረው እና ከታምራት አበበ ጋር የተጫወተችው “ጠውላጋዋ አበባ”፣ እንዲሁም ከጌጡ አየለ ጋር በርካታ አስቂኝ የኮሜዲ ሙዚቃዎችን ተጫውታለች፡፡ ፍቅርተ ደሳለኝ እና ጌጡ አየለ በሚሰሯቸው የኮሜዲ ሙዚቃዎች አቀራረባቸው ከስሜት ጋር ነበር፡፡ በጊዜውም ባልናሚስት፣ እጮኛሞች፣ ፍቅረኛሞች እና መሰል ገፀ ባህሪያትን ወክለው ስለሚጫወቱ በተመልካች ዘንድ ባልና ሚስት ተደርገው ይቆጠሩ ነበር፡፡ እንደ አርቲስቷ ገለፃ “አርቲስት ጌጡ አየለ የወንድ ጓደኛ እንኳን አልነበረውም፡፡ ሰርጉንም እኔ ነኝ ደግሼ የዳርኩት” በማለት በሁለቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ታስረዳለች፡፡
  

   ቀደም ሲል ትምህርት ሳትማር የትራንፔት ተጫዋች የሆነው የመጀመሪያ ባለቤቷ አቶ ግርማ ገብረአብ እያስጠናት በግሩም ሁኔታ ዘፈኖቿን ታቀርብ ነበር፡፡ ባለመማሯ የተቆጨችው ፍቅርተ ደሳለኝ በየነ መርዕድ የማታ ትምህርቷን ጀምራ ፍሬህይወት 1ኛ ደረጃ ት/ቤት እስከ 8ኛ ክፍል ተማረች፡፡ ከዚያም በሌላ ት/ቤት እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርቷን አጠናቃቀች፡፡ አርቲስት ፍቅርተ ደሳለኝ ከሙዚቃዎቿ ባሻገር በርካታ ትያትሮችና እና ፊልሞችን ሰርታለች፡፡ ከሰራቻቸው ትያትሮች ውስጥ የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን የትርጉም ስራ የሆነው “የፌዝ ዶክተር ” የተሰኘው ትያትር የመጀመሪያ ስራዋ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ “ጥላ”፣ “የባላገር ፍቅር”፣ የዶ/ር አርቲስት ተስፋዬ አበበ ድርሰት የሆነው “አምታታው በከተማ” ላይም የገጠር ሴትን ወክላ ተጫውታለች፡፡ በ1992ዓ.ም ጡረታ ከወጣች በኋላ የአዜብ ወርቁ የትርጉም ስራ የሆነው “8ቱ ሴቶች” እንዲሁም “ፍቅር የተራበ” ትያትር ላይ ተውናለች፡፡
   
 

   ከትያትሩ ወደ ፊልም ኢንዱስትሪው ተቀላቅላ በዛ ያሉ ፊልሞች ላይም ሰርታለች፡፡ ለአብነትም ፡- “ማራ፣ ማንነት፣ ታስራለች፣ ዱካ፣ የህሊና ዳኛ/ የመጀመሪያ የፊልም ስራዋ ነው/፣ ቫኬሽን ፍሮም አሜሪካ፣ ሰርፕራይዝ፣ ጥቁር ነጥብ፣ የልደቴ ቀን፣ ያ ልጅ፣ የትውልድ እንባ፣ ስሌት፣ ጓንታናሞ፣ ልዩነት፣ 400 ፍቅር፣ አይራቅ፣ ጉደኛ ነች የመሳሰሉትን በጥቂቱ መጥቀስ ይቻላል፡፡ አርቲስት ፍቅርተ ደሳለኝ በትያትርም ሆነ በፊልሞቹ ላይ ብዙውን ጊዜ የእናት ገፀ ባህሪን ተላብሳ ነው የምትቻወተው፡፡


    ለመድረክ ከፍተኛ ክብር የምትሰጠው አርቲስት ፍቅርተ ደሳለኝ ሽቅር ቅር እና ሳቂታ ናት፡፡ ፈገግታ ከፊቷ የማይለያት አርቲስቷ እንባዋም ቅርብ ነው ይላሉ በቅርብ የሚያውቋት ጓደኞቿ፡፡ ጡረታ በ1992ዓ.ም ከወጣች በኋላ የፍቅር ዘፈን አልሰራም፤ ከሰራሁም ጠንከር ያሉና አስተማሪ ስራዎችን ነው የምሰራው የሚል አቋም አላት፡፡ አርቲስት ፍቅርተ ደሳለኝ ከትራንፔት ተጫዋች ባለቤቷ ከአቶ ግርማ አንድ ልጅ ወልዳለች፡፡ ይህ ትዳር ባይዘልቅም አሁን ሌላ ትዳር መስርታ እና ልጆች ወልዳ እየኖረች ነው፡፡ የልጅ ልጅ ያየችው እና የአራት ልጆች እናት የሆነችው ፍቅርተ ደሳለኝ በቅርቡ ሊወጡ የሚችሉ 6 ያህል ፊልሞችም አሏት፡፡ለአንጋፋ ድምፃዊት እና ተዋናይት እድሜ እና ጤና በመመኘት ከእሷ ስራ ተከታዩን ጋበዝኳችሁ…………
   
     
                   

No comments:

Post a Comment