Thursday, October 9, 2014

ጥቂት ስለ ፖስታ ቴምብር …….


   መስከረም 29 የአለም የፖሰት ቀን በተለያዩ ሀገራት ይከበራል፡፡ ይኸው ቀን በእኛም ሀገር ታስቦ ይውላል፡፡ ይህ በመሆኑም ስለ ፖስታ ካነበብኩት መረጃ ላካፍላችሁ……

  በሌላ ቦታ ከሚኖር ዘመድ ወይም ወዳጅ በፖስታ ቤት በኩል ደብዳቤ ተልኮልዎት እንደሆነ ከኤንቨሎፕ ፊት ለፊት እና ከበስተጀርባው ከሰፈሩት የተቀባይ እና የላኪ አድራሻዎች ሌላ አብዛኛውን ጊዜ ቅርፁ አራት ማዕዘን የሆነ አንድ አነስተኛ ወረቀት ተለጥፎ ይመለከታሉ፡፡ ይህ ወረቀት በልዩ ልዩ ቀለማት ያሸበረቀ ከመሆኑም በላይ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማህበራዊ፣ ወዘተ ጉዳዮችን ያካተቱ ስዕሎች የተሳሉበት ስለሆነ ጎላ ብሎ ይታያል፡፡ ይህ ነው እንግዲህ የፖስታ ቴምብር የሚባለው፡፡

   የፖስታ ቴምብር በቀላሉ ዓይንን ስለሚማርክ ቀረብ ብለው ሲያጤኑት ከስዕሉ መልዕክት ሌላ ብዙ ነገሮችን ይመለከታሉ፡፡ እነርሱም ቴምብሩን ያሳተመው አገር ስም፣ የቴምብሩ ዋጋ፣ በቴምብሩ ላይ የተሳለው ስዕል መጠሪያ፣ በመጨረሻም ስዕሉን የሳለው ሰዓሊ ስም እና ቴምብሩ የታተመበት ዓመተ ምህረት ሰፍሮበት ይመለከታሉ፡፡ በአንዳንድ  ቴምብሮች ላይ የአታሚውን ድርጅት ስምም ያገኛሉ፡፡


 በፖስታ ላይ የተለጠፈው ቴምብር የፖስታ ቴምብርን ምንነት ላላወቁ ሰዎች ለጌጥ የተቀመጠ ይመስላቸው ይሆናል፤ ነገር ግን ለጌጥ አይደለም፡፡ ይህ ቴምብር በደብዳቤው ላይ ባይለጠፍ ኖሮ ደብዳቤው ከላኪው ወደ ተቀባዩ ሊደርስ አይችልም ነበር፡፡ ይህንን የፖስታ ቴምብር የማሳተም እና የመሸጥ ስልጣን ያለው የፖሰታ አገልግሎት ድርጅት ብቻ ነው፡፡

  ደብዳቤውን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ስፍራ ተቀብሎ የማስተላለፍ መብት የተሰጠውም ይኸው ድርጅት ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ መልኩ ለሚያከናውነው ተግባር የአገልግሎት ክፍያ ተቀብሎ በምትኩ የፖስታ ቴምብር ለላኪው ይሰጣል፡፡ ይህም የሚተላለፈውን የፖስታ መልዕክት አይነት፣ ክብደት፣ መጠንና የቦታውን ርቀት መሰረት በማድረግ ይሆናል፡፡ 

  ይህ ቴምብር እንደ ክፍያ ማረጋገጫ የሚያገለግል ስለሆነ በሚላከው ደብዳቤ ወይም በሌላ የፖስታ መልዕክት ላይ በመለጠፍ በቀጥታ ለባለአድራሻው እንዲደርስ ያደርጋል፡፡ስለዚህ የፖስታ ቴምብር በላኪውና መልዕክቱን ለሚያደርሰው ክፍል ለአገልግሎቱ የሚሰጠው የክፍያ ማረጋገጫ ነው ለማለት ይቻላል፡፡

  ማንናውም ሰው ሊገነዘበው የሚገባ ነገር ቢኖር የፖስታ ቴምብር ከቀረጥ ቴምብር የተለየ መሆኑን ነው፡፡ የፖስታ ቴምብር ደብዳቤ ወይም ሌላ የፖስታ መልዕክት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመላክ የሚያገለግል ሲሆን የቀረጥ ቴምብር ግን በውሎች፣ በውክልናዎች፣ በንግድ ፍቃድ ማሰረጃዎች ላይ ወዘተ የሚለጠፍ ነው፡፡ የፖስታ ቴምብር በፖስታ አገልግሎት ድርጅት ታትሞ የሚወጣ ሲሆን የቀረጥ ቴምብር ደግሞ የሚታተመው በገንዘብ ሚኒስቴር አማካኝነት ነው፡፡ 

No comments:

Post a Comment