Wednesday, July 23, 2014

ለቢል ጌትስ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተሰጠ


   የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለማይክሮሶፍት መስራችና የኩባንያው ባለቤት ቢል ጌትስ የክብር ዶክትሬት ሰጠ።የዩኒቨርስቲው የውጭ ግንኙነት፣ ትብብርና ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ባልደረባ አቶ ተሾመ ጌታሁን እንደገለጹት ለቢል ጌትስና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ሊቀመንበር የዶክትሬት ማዕረጉ የሚሰጠው በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ፈጠራ ዓለም እርስ በእርሱ እንዲገናኝ አስተዋጾኦ በማበርከታቸው ነው፡፡  

   ባለሃብቱ ቢል ጌትስ 17-11-06 /ሀሙስ/ አዲስ አበባ በመገኘት ከዩኒቨርሲቲው ልዩ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል። 

  ዩኒቨርስቲው  "የፈጠራ ባለሙያና በጎ አድራጊው ሚስትር ቢል ጌትስ የቴክኖሎጂ ውጤታቸው ሕዝብን ከሕዝብ በማግናኘት ረገድ ካበረከተው አስተዋጽኦ ባሻገር በአፍሪካ ባከናወኗቸው በጎ ተግባራትም ሽልማቱ ይገባቸዋል" ብሏል፡፡

 ዊሊያም ሄኒሪ ጌትስ ሶስተኛ /ቢል ጌትስ/ እ.አ.አ. ጥቅምት 28 ቀን 1955 በዋሽንግተን ሲያትል ተወለዱ። በሐርቫርድ ኮሌጅ ሌክሳይድ የተማሩት ባለሃብቱ ለኮምፒዩተር ፕሮግራም ዝንባሌ ያደረባቸው ገና የ13 ዓመት ልጅ እያሉ ነበር፡፡ በቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራ ፍቅር አድሮባቸው ፖል አለን ከተባለ አጋራቸው ጋር ማይክሮ ሶፍትን መሰረቱ፡፡

 ሚስተር ጌትስ ከትዳር አጋራቸው ሚሊንዳ ጌትስ ጋር እ.አ.አ በ1994 ዊሊያም ኤች ጌትስ ፋውንዴሽንን በማቋቋምና 28 ቢሊዮን ዶላር በመመደብ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ላይ የጤናና የትምህርት ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። የዓለማችን ባለ ሃብት የሆኑት ቢል ጌትስ ባለፈው የካቲት የማይክሮሶፍት ኩባንያ ሊቀመንበርነታቸውን ማስረከባቸው ይታወሳል፡፡
                                                ምንጭ ፡- ኢዜአ

No comments:

Post a Comment