Thursday, May 5, 2022

ሁለገቡ የጥበብ ሰው እና የክብር ዘበኛ አባል የሆኑት አርቲስት 50 ዓለቃ ሸዋንዳኝ ወልደየስ አረፉ፡፡

አርቲስት 50 ዓለቃ ሸዋንዳኝ ወልደየስ ተወዛዋዥ ፣ የውዝዋዜ አሰልጣኝ ፣ ግጥም እና ዜማ ደራሲ ፣ ድምፃዊ እና የክብር ዘበኛ አባል ሲሆኑ በተለይ “ጃፓኗን ወድጄ” በተሰኘው የክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሰሰ ስራ ይታወቃሉ፡፡ አርቲስት 50 ዓለቃ ሸዋንዳኝ ወልደየስ ብሩ በሰሜን ሸዋ ቡልጋ አውራጃ 1926 ተወለዱ፡፡ ከዛም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት እድገታቸውና የልጅነት ጊዜያቸውን ላምበረት ሾላ አካባቢ አሳልፈዋል፡፡

1940 . የክብር ዘበኛ ሰራዊትን በመቀላቀል ከሁለት አመት ቆይታ በኋላ 1943 . የአንደኛው ቃኘው ሻለቃ እንዲሁም 1946 . ከአራተኛው ቃኘው ሻለቃ ጋር ወደ ኮሪያ ዘምተዋል፡፡ ከኮሪያ ዘመቻ መልስም ከክብር ዘበኛ ሙዚቃ ክፍል ጋር የተለያዩ የሙዚቃ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡ በ1949 ዓ.ም በርከት ያሉት ስራዎቻቸው በጠቅል ሬዲዮ ይደመጡላቸው እንደነበርም በአንድ ወቅት ባደረግነው ቃለ መጠይቅ ላይ ገልፀውልናል፡፡

ወደ
ሃገራቸው ከተመለሱ በኋላም ለፈጸሙት ወታደራዊ ግዳጅ የቀዳማዊ ይለስላሴ የጦር ሜዳ የወርቅና የብር ሜዳልያ፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኮሪያ ጦርነት መታሰቢያ፣ የዳግማዊ ሚኒሊክ የጦር ሜዳ የወርቅ ሜዳልያ፣ የቀዳማዊ ይለስላሴ የክብር ሜዳልያ፣ የክብር አምባሳደር የወርቅ ሜዳልያ እንዲሁም ከኮሪያ እና አሜሪካ መንግስታት የተመድ ሳኒቴሽን ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ከዚህ ባለፈም 25 አመት የረጅም አገልግሎት የወርቅ ሜዳልያ፣ 15 አመት አገልግሎት የብር ሜዳልያ እንዲሁም የተዋጊ ምልክት ያለበት የደረት አርማ ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል።

በራሳቸው ድምፅ ፣ ግጥም እና ዜማዎችን ደርሰው ከተጫወቷቸው ሙዚቃዎች ውስጥ ፡- ሰው መመልከትሽ ይቅር (እኔ እበቃሻለሁ) ፣ አዲስ አበባ የተዋብሽው ፣ ስራ አትፍቺ ፣ ፍቅርን አታውቂ እና ወይ አዲስ አበባ የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ “እንዋደድ ነበር” የሚል ሙዚቃን ከድምፃዊ ተዘራ ሀይለሚካኤል ጋር የተጫወቱ ሲሆን ለጥላሁን ገሰሰ - ስትሄድ ስከተላት  እና ጃፓኗን ወድጄ ፣ ለብዙነሽ በቀለ - እንዲህ ነው ጋብቻ (የማይሞት ጋብቻ) ፣ ለመሀሙድ አህመድ - ፍቅር በዘበዘኝ የሚሉ ስራዎችን ስጥተዋል፡፡ የራሳቸውም ሆነ ለሌሎች ድምፃውያን የሰጧቸው አብዛኞቹ ዘፈኖች እውነተኛ እና የራሳቸው ታሪኮች ናቸው፡፡ “ጃፓኗን ወድጄ”ም የ50 ዓለቃ ሸዋንዳኝ ወልደየስ እውነታኛ ታሪክ እና ዜማውም የራሳቸው ድርሰት ነው፡፡ የግጥሙ ደራሲ ደግሞ 50 አለቃ ገዛኸኝ ደስታ ናቸው፡፡


በክብር ዘበኛ ሙዚቃ ኦርኬስትራ ዉስጥ ተቀጥረዉ እያገለገሉ እያለ 1954 . ከወ/ የሺመቤት ወለደማሪያም ጋር ጋብቻ መስርተዉ 8 ወንዶችና 3 ሴቶች በድምሩ 11 ልጆችን አፍርተዋል፤14 የልጅ ልጆችን እና 2 የልጅ ልጅ ልጆችን አይተዋል፡፡ በክብር ዘበኛ ውስጥ ከ30 አመት በላይ ያገለገሉት አርቲስት 50 ዓለቃ ሸዋንዳኝ ከ60 አመታት በላይ የተሻገረው ታዳራቸው /ጋብቻቸው/ በክብር ዘበኛ ሙዚቃ ክፍል በእነ ጥላሁን ገሰሰ ፣ አበበ ተሰማ ፣ ብዙነሽ በቀለ ፣ ተዘራ ሃይለሚካኤል እና ሌሎች የክብር ዘበኛ አባላት ድምቆላቸዋል፡፡ ሚዜዎቻቸው እነ ኮለኔል ሳህሌ ደጋጎ ፣ ተካልኝ ፀጋ እና አሰፋ ሀይሌ የተባሉ የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ አባላት እንደነበሩም በህይወት በነበሩ ጊዜ አጫውተውናል፡፡

የባለብዙ ታሪክ ባለቤት እና ሁለገብ የጥበብ ሰው የሆኑት አርቲስት 50 ዓለቃ ሸዋንዳኝ ወልደየስ 1974 ከክብር ዘበኛ ሙዚቃ ኦርኬስትራ ጡረታ ከወጡ በኋላ በግላቸዉ የራሳቸዉን ስራ እየሰሩ ህይወታቸዉን ሲመሩ ቆይተዋል፡፡ አርቲስት 50 ዓለቃ ሸዋንዳኝ ወልደየስ በተወለዱ 88 ዓመታቸዉ ትናንት ሚያዝያ 26 ቀን 2014 . ምሽት 3 ሰዓት አካባቢ ህይወታቸዉ ማለፉንናቀብራቸዉ ስነ ስርዓትም በነገዉ እለት/28/8/2014ዓ.ም በአዲስ አበባ የካ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ከቀኑ 900 እንደሚፈፀም ልጃቸዉ እየሩሳሌም ሽዋንዳኝ ገልፀውልናል፡፡ ለእሳቸው እረፍተ ነፍስን ፤ ለቤተሰቦቻቸው ፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው እና አድናቂዎቻቸው ደግሞ መፅናናትን እንመኛለን፡፡

No comments:

Post a Comment