Thursday, April 21, 2022

የኢትዮጵያ ጥንታዊ የባህል የዜማ መሳሪያ …. በገና !!!

 በገና ፡- ነዘረ ፣ መታ ፣ ደረደረ ማለት ሲሆን በገነኛ የሚለው ደግሞ በገናን የሚመታ ፣ በገናን የሚያውቅ ደርዳሪ ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም በገና ማለት ድርደራ ፣ ምስጋና ፣ መዝሙር በሚል ይተረጎማል፡፡ በበገና የህይወት ከንቱነት ፣ የሞት አይቀሬነት ይሰበክበታል፤ ቅዱሳን ይመሰገኑበታል፤ ሞራል እና ስነ ምግባር ይነገርበታል፤ ፀሎት እና ምስጋናም ይቀርብበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እንደ አስፈላጊነቱ ለማህበራዊ እሴት ፣ ለሀገር ክብር ፣ ለሉዓላዊነት ፣ ወ.ዘ.ተ በገና ይደረደራል፡፡ በአጠቃላይ እድሜ ጠገብ የሆነው በገና ለአርምሞ/ተመስጥኦ/ ተመራጭ ነው ፡፡ ለአርምሞ ማን እንደበገናም ተብሎለታል፡፡ 

የበገና አመጣጥ ረዘም ያለ ታሪክ ያለው ቢሆንም አነሳሱ ግን ከእምነት በተለይም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ይህ የዜማ መሳሪያ በሀገራችን እንዴት ተፈጠረ እና መቼ ተጀመረ የሚለውን በግልፅ የሚያስረዱ መረጃዎች ባይኖሩም ሁለት መላ ምቶች ተቀምጠዋል፡፡ 1ኛው በገና ቀድሞም በኢትዮጵያ ውስጥ ነበረ የሚል ሲሆን 2ኛው ደግሞ ንግስት ሳባ የሰለሞንን ጥበብ ለማየት ወደ እየሩሳሌም በሄደችበት ጊዜ ከንጉስ ሰለሞን የተወለደው ቀዳማዊ ምኒልክ ታቦተ - ፅዮንን ፣ በርከት ካሉ ነዋየተ - ቅዱሳን ጋር ከእስራኤል ወደ ኢትዮጵያ ይዞ ሲገባ በገናም አብሮ ገብቷል የሚሉ እስቤዎች ናቸው፡፡ ይሁንና የበገና አጠቃላይ ማህበራዊም ሆነ መንፈሳዊ አገልግሎቱ ይበልጥ ጎልቶ የታወቀው ግን በመዝሙረኛው /በገነኛው/ ቅዱስ ዳዊት እንደሆነ በስፋት ይነገራል፡፡


በገና ቁመቱ ረዘምገበታው ሰፋ ያለ 90 ሳንቲ ሜትር እስከ 140 ሳንቲ ሜትር ርዝመት ያለውና 10 ጅማቶች (አውታሮች) ያሉት ጥንታዊ የኢትዮጵያ የዜማ መሳርያ ነው። በገና ሲደረደር የሚወጣው ድምፅ ወፍራም እና ቀልብን የሚስብ በመሆኑ ሀዘን እና ትካዜን ለመግለፅ ፣ ፀሎት ለማድረስ እንዲሁም የውስጥ ስሜትን ለማድመጥ ተመራጭ የዜማ መሳሪያ ነው፡፡ ይህንን ተወዳጅ የሙዚቃ መሳሪያ ለመስራት የተለያዩ ግብአቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ግራ እና ቀኝ የሚቆሙት ሁለት ምሰሶዎች እና አግዳሚ እንጨት/ቀንበር/ ፣ 10 የሚወጠሩ ክሮች/ጅማቶች/ ፣ ገበቴ ፣ መቃኛ ፣ ብርኩማ ፣ እንዚራ ፣ መወጠሪያ እና ድህንፃ /መደርደሪያ/ ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ የበገና አካሎች/ክፍሎች ሁሉም ትርጓሜ ያላቸው ሲሆን ትርጓሜያቸውም ሀይማኖታዊ ይዘት አለው፡፡ 

በገና በእጅ እና በድህንፃ ይደረደራል(ድህንፃ- መግረፊያ ሆኖ እጅግ መሳጭና የበለጠ በሚመስጥ መልኩ በገናውን የሚያስጮኽ ጥንታዊ የዜማ መሣርያ ወይም የበገና ማጫወቻ ነው)፡፡ በገና ለዓለማዊ ፍላጐት ማስፈፀሚያ ማለትም ለዳንስና ለዳንኪራ ፣ ለዘፈንና ለጭፈራ ፣ ለዝናና ለጉራ፣ ለቀልድና ለፉከራ ወ.ዘ.ተ አገልግሎት አይሰጥም(አገልግሎት ላይ አይውልም)፡፡

በገና ለፈጣሪ ምስጋና ማቅረቢያ ብቻ ሳይሆን ቀደም ያሉት ነገስታት በፍርድ ፣ በሸንጎ ፣ በአስተዳደር ውሎ ህዝብን እንዳይበድሉ ፣ ለስጋዊ ነገር አድልተው ከፈጣሪ መንገድ እንዳይወጡ ፤ ሚስቶቻቸው ፣ መኳንንቱ ፣ እና መሳፍንቱ መካሪ እና ገሳጭ እንዲሁም አርቆ አመላካች የሆኑ ግጥሞችን በበገና እየደረደሩ ለነገስታቱ ያስደምጡ ነበር፡፡ እናም ነገስታቱ በዘዴ ፣ በጥበብ እና በማስተዋል ህዝብን እንዲያስተዳደሩ ምክሩ በበገና ይሰጥ እንደነበርም ይወሳል፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ፣ አፄ ዮሀንስ ፣ አፄ ምኒሊክ ፣ እቴጌ ጣይቱ ፣ ምንትዋብ  እና ራስ መኮንን በገና ከሚደረድሩ ነገስታት እና መኳንንት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡


በገና ጥንታዊ የዜማ መሳሪያ ይሁን እንጂ እንደ አንጋፋነቱ ብዙ ያልታወቀ እና በጥቂት ባለሙያዎች እጅ የቀረ እና እየተረሳ የመጣ የዜማ/ሙዚቃ መሳሪያ/ ነበር፡፡ ይሁንና ከጥቂት አመታት ወዲህ ግን ይህ የዜማ መሳሪያ እንዳይጠፋ እና ጥንታዊነቱ ተጠብቆ እንዲቆይ ብሎም ለትውልድ እንዲተላለፍ የተለያዩ ተቋማት ተከፍተው ስልጠና እየሰጡ ይገኛል፡፡

No comments:

Post a Comment