Monday, April 10, 2017

“የበጋው መብረቅ” ---- ሌፍተናት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ


  “ጃጋማየሚለው የኦሮምኛ ቃል የአባታቸው የፈረስ ስም ሲሆን፤ የአማርኛ ፍቺው ሀይለኛ ማለት ነው። ሌፍተናት ጄኔራል ጃጋማ እሲኪወለዱ ድረስ የፈረሳቸውን ስም የሚሰጡት ሁነኛ ልጅ ያላገኙት አባታቸው፤ በልጃቸው በጃገማ ይኮሩ ነበር። ለዚያም ነው ይህን ስያሜ ለልጃቸው መጠሪያ ያደረጉት ይባላል፡፡


  አገራቸውን ከልጅነታቸው ጀምሮ በውትድርና ያገለገሉት ጄነራል ጃጋማ ኬሎ ከኢጣሊያ ጋር የነበረው ጦርነት በድል ከተጠናቀቀ በኋላም አገራቸውን በሻለቅነት፣ በብርጌድ መሪነትና በብሔራዊ ጦር አዛዥነት በማገልገል የሌፍተናንት ጄኔራልነት ማዕረግ አግኝተዋል።
  
   በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ጦርነት ወቅት ወራሪውን የጣሊያን ጦር በዱር በገደሉ በጀግንነት በመዋጋት በተቀድጇቸው ድሎች ሳቢያየበጋው መብረቅየሚል ቅጽል ስም ይጠሩ እንደነበር ታሪክ ያወሳል። በዚህ ስያሜም(ርዕስ) የሕይወት ታሪካቸውን የሚተርክ መጽሐፍ ታትሞላቸዋል።
  አርበኛው ሌፍተናት ጄኔራል ኬሎ ከአውሮፕላን ሳይቀር ወድቀው ከሞት ተርፈዋል፡፡የመኪና አደጋም እንዲሁ ደርሶባቸው ነበር፡፡ በቀድሞው  ሆለታ የጦር ትምህርት ቤትና አሜሪካን አገር ድረስ ተጉዘውም ዘመናዊ የጦር ትምህርት በመማር በሺዎች የሚቆጠሩ ያገራቸውን ልጆች ያስተማሩ አገር ወዳጅ ጀግና ናቸው።
  ሌፍተናንት ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ በህይወት ዘመናቸው በርካታ የክብር ሽልማቶችንም ተቀብለዋል። የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ፣ የዳግማዊ ምኒልክ፣ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ኒሻኖች እንዲሁም የቀድሞው የቀዳዋዊ አጼ ኃይለስላሴ የጦርና የአርበኝነት ሜዳሊያዎች ጥቂቶቹ ናቸው።

    በኢትዮጵያ ታሪክ ታላቅ ስፍራ ያላቸው ሌተናል ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ባደረባቸው ህመም ሳቢያ በጦር ሃይሎች ሆስፒታል ህክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው 96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ሌፍተናል ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ የአንድ ወንድና አምስት ሴቶች ልጆች አባት ነበሩ። ለቤተሰቦቻቸው እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን እንመኛለን ፡፡

No comments:

Post a Comment