“ሀገርን
መውደድ የሚገለፀው በመስራት ነው፡፡ ቀደም ሲል የነበሩት በአብዛኞቹ ውጭ ሀገር ተምረው ወደ ሀገራቸው የመመለሱ ሁኔታ ሰፊ ነው፡፡
ውጭ የመቅረት ሀሳብም አልነበረንም፡፡ ይህ ለሀገራችን የነበረንን አክብሮት እና ፍቅር የሚያሳይ ነው፡፡ እናም ወጣቱን ትውልድ ይህንኑ
ነው የምለው፤ በዚች ምስኪን (ድሃ) ሀገር ውጭ ተምሮ በቂ ደምወዝ ፣ ምቹ የስራ ሁኔታ የለም ብሎ መቅረት የታሪክ እና የትውልድ
ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡” ክብር ዶ.ር ተፈራ ደግፌ
ስራ የጀመሩት
በኢትዮጵያ መንግስት ባንክ ሲሆን ፣ ባንኩ በተቋቋመ በዓመቱ ነው፡፡ አቶ ተፈራ ባንኩ የውጭ ትምህርት እድል (ስኮላርሺፕ) ሰጥቷቸው
ከተማሩት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ናቸው፡፡ በወቅቱ
በእርሳቸውና በጓደኞቻቸው ጥረት የተቋቋመው የውጭ ሃገር ተማሪዎች ህብረት የመጀመሪያው ሰብሳቢ የነበሩ ሲሆን በቀጣይም ግርማሜ ንዋይ ስልጣኑን እንደተረከቡም ይነገራል።
አቶ ተፈራ በ1950ዎቹና 60ዎቹ ውስጥ የኢትዮጵያ የባንክ ስራ ስርአትን ከዘረጉት ሰዎች መካከል አንዱ ነበሩ። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የመንግስት ባንክ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ስራቸውን ከጀመሩ በኋላ በሀገሪቱ የባንክ ዘርፍ
እንዲያድግ፤ በርካታ ቅርንጫፎች እንዲከፈቱ እንዲሁም የባንክ ሙያ ማሰልጠኛ እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡
በኢትዮጵያ መንግስት ባንክ፤ በሱዳን የኢትዮጵያ ባንክ፤ በመድህን ድርጅት፣ በሲቪል አቬሽን ዳይሬክተርነት፤ በመጨረሻም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዢ ሆነው ሰርተዋል፡፡ በአብዮቱ ዘመንም ታስረው እንደነበር ይነገራል። ከእስር ከተፈቱ በኋላ፤ አቶ ተፈራ ደግፌ በቫንኩቨር በሚገኘው የብሪቲሽ ኮሉምቢያ ዩኒቨርስቲ ህግ ፋክልቲ የክብር ዶክትሬት የተሰጣቸው ሲሆን፤ ጡረታ ከወጡ በኋላ ረጅም ጊዜያቸውን የኖሩት በቫንኩቨር ካናዳ ነበር።
ክብር ዶክተር ተፈራ ደገፌ በቶሮንቶ የሚገኘው ቢቂላ የሽልማት ድርጅት ባዘጋጀው የመጀመሪያ ሽልማት ላይ በህይወት ዘመን አስተዋጽኦ ተሸልመዋል፡፡ ATripping
Stone, and Minutes of an Ethiopian Century የተሰኙ ሁለት መጻህፍትም ጽፈዋል።
የሩሲያ፣ ጣሊያን ፣ ፈረንሳይ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎችን የሚናገሩት ዶ.ር ተፈራ ደገፌ በ2007ዓ.ም በ89 ዓመታቸው
ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡ የሁለት ልጆች አባት ሲሆኑ በኑዛዜያቸው ላይ በኢትዮጵያ ያላቸው ንብረት ለፌስቱላ ሆስፒታል እንዲሰጥላቸው
መናዘዛቸውም ተሰምቷል፡፡ በተገኘው አጋጣሚ የሀገር ባለውለታዎችን ማስታወስ ተገቢ
ነው፡፡
ክብር እና ምስጋና ለባለውለታዎቻችን!!!