Thursday, February 19, 2015

የሰማዕታት ሀውልት /የካቲት 12/


    ሀውልቱ የወራሪው የጣሊያን ወታደሮች በግፍ የጨፈጨፏቸውን 30ሺ ያህል ሰዎች ለመዘከር የቆመ ነው፡፡ ግራዚያኒ ሰራዊቱን እና መኳንንቱን ጠርቶ ፣ ህዝቡን ሰብስቦ የአሁኑ አዲሰ አበባ ዩኒቨርስቲ ቀደም ሲል ገነተ ልዑል በሚል ይታወቅ በነበረው በአፄ ኃይለስላሴ ቤተ መንግስት ውስጥ የተለመደ የእብሪት ንግግሩን በማሰማት ላይ ነበር፡፡ ግራዚያኒን ለመግደል አመቺ ቦታ እና ጊዜ ሲጠባበቁ የነበሩት አብርሐም ደቦጭ እና ሞገስ አሰግዶም የያዙትን ቦምብ አከታትለው ወረወሩበት፤ ግራዚያኒም ቆሰለ፡፡ ከዚያች ቅፅበት በኋላ በማንኛውም ሁኔታ የተገኘ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በግፍ ተጨፈጨፈ፡፡ አዲሰ አበባም በንፁሀን የደም ጎርፍ ተጥለቀለቀች፡፡ በህፃናት ለቅሶ በእናቶች ዋይታ ተዋጠች፡፡ በወቅቱ የተፈጠረው ሁኔታም ኢትዮጵያውያን በድፍረት እና በወኔ ጠላትን እንዲፋለሙ ብርታት ሆናቸው፡፡ እነዚህን ያለርህራሄ የተጨፈጨፉ ንፁሀን ዜጎች ለማሰታወስም ዛሬ በየካቲት 12 ሆስፒታል ፣ በአዲሰ አበባ ዩኒቨርስቲ እና በአንበሳ ግቢ መካከል 6ኪሎ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ የሰማዕታቱ ሃውልት ቆሟል፡፡


         በዚህ ሀውልት ቀረፃ ላይ ኢትዮጳያውያን ባለሙያዎችም ተሳትፈዋል፡፡ ሀውልቱ 28 ሜትር ቁመት ያለው ሲሆን ባለ ሶስት ማዕዘንም ነው፡፡ ሀውልቱ የተሰራው በሁለት የዩጎዝላቪያ ዜግነት ያላቸው ባለሙያተኞች ሲሆን በሀውልቱ ላይ ኢትዮጵያውያን በጣሊያን ወታደሮች በግፍ ሲገደሉ የሚያሳዩ ቅርፃ ቅርፆችም ይስተዋላሉ፡፡ ሀውልቱ ከቅርፃ ቅርፆቹ ባሻገር የተለያዩ ፅሁፎችም አሉት፡፡
                                                                   ክብር ለተሰውት ሰማዕታት……..!!!

No comments:

Post a Comment