Monday, December 14, 2015

ፊቼ - ጫምባላላ በዓለም ቅርስ ነት ተመዘገበ


  የሲዳማ ሕዝብ የዘመን መለወጫ በዓል ‹‹ፊቼ - ጫምባላላ›› የሰው ልጆች ወካይ ቅርስ (Representative List of Intangible Cultural Heritage of Humanity) ሆኖ መመዝገቡን ዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት) አስታወቀ፡፡
ፊቼ፣ ኢትዮጵያ ከመስቀል በዓል ቀጥሎ ያስመዘገበችው ሁለተኛው ወካይ ቅርስ እንዲሆን የተወሰነው የዩኔስኮው በይነ መንግሥታዊ ኮሚቴ 10ኛውን ጉባኤ በናሚቢያ መዲና ዊንድሆክ ኅዳር 22 ቀን 2008 .. ባካሄደበት ጊዜ ነው፡፡ 

  ዩኔስኮ በድረ ገጹ እንዳስታወቀው፣ ... 2003 የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ዓለም አቀፍ ስምምነት መስፈርትን ያሟሉና ከተለያዩ አገሮች የተወከሉ ተጨማሪ 19 ወካይ ቅርሶችም ተመዝግበዋል፡፡ ከአፍሪካ ቅርሷን ያስመዘገበችው ሁለተኛዋ አገር ጉባኤውን ያስተናገደችው ናሚቢያ ስትሆን የፍራፍሬ ፌስቲቫልዋ ይሁንታን አግኝቷል፡፡ 
በወርሀ ክረምት የሚውለው የፊቼ በዓል ታሪካዊ አመጣጥ በአፈ ታሪክ እንደሚወሳው ከጥንት ጀምሮ ሲሆን፣ የበዓሉ ስያሜ መነሻ ፊቾ ከምትባል ሴት ነው፡፡ ይህች ሴት በየዓመቱ ለወላጆቿና ወንድሞቿ ቡርሳሜ (የተነኮረ እና በቅቤ የተለወሰ ቆጮ) እና ወተት በቃዋዶ ዕለት ይዛ መጥታ እንደምትጠይቃቸውና የተዘጋጀውንም ቡርሳሜ ጎረቤት ተሰብስቦ ይጋበዝ እንደነበር ይነገራል፡፡ በአፈ ታሪኩ መሠረት ምግቡ ይበላ የነበረው ማታ ነው፡፡ ፊቼ ይህንን በተደጋጋሚ ስትፈጽም ቆይታ ትሞታለች፡፡ ቀደም ሲል የግብዣው ታዳሚ የነበሩ ሰዎች እርሷ የምትመጣበትን ጊዜ ጠብቀው በራሳቸው ለመደገስ ይስማማሉ፡፡ የግብዣውን ስያሜም በስሟ ፊቼ ብለው ጠሩት፡፡ በዚህ መሠረት የበዓሉ አከባበር በሁሉም ሲዳማ አካባቢ ፊቼ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት እየተከበረ መምጣቱ እንደሚነገር፣ በዓሉን አስመልክቶ ኢትዮጵያ ለዩኔስኮ የላከችው መረጃ ያመለክታል፡፡


  የፊቼ - ጫምባላላ በዓል በርካታ ባህላዊና ማኅበራዊ ፋይዳዎች ያሉት፣ አገር በቀል የሆነ የዘመን አቆጣጠር ዕውቀትን አካቶ የያዘ ዓመታዊ የዘመን መለወጫ ክብረ በዓል ከመሆኑም በላይ፣ የሲዳማ ብሔር አንኳር የሆኑ ባህላዊ ገጽታዎች የሚንጸባረቁበት የማይዳሰስ (ኢንታንጀብል) ቅርስ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ በሲዳማ ባህል ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየው ‹‹ፊቼ›› የዘመን መለወጫ በዓል ከሁለት ሳምንት ላላነሰ ጊዜ በድምቀት የሚከበር ሲሆን፣ አከባበሩም ቅደም ተከተላዊ ሒደትና በደረጃ እየሰፋ የሚሄድ የጋራ የአከባበር አንድምታ ያለው ነው፡፡ በዓሉ በቤተሰብ ወይም በጎረቤት ደረጃ ተሰባስቦ በማክበር የሚያበቃ ሳይሆን፣ ሰፋ ባለ መልኩም በባህላዊ አደባባዩ ጉዱማሌ፣ በጋራና በድምቀት የማክበር ሒደትን የሚያካትት ነው፡፡
 
‹‹ፊቼ ፋሎ›› የሚባለው በጋራ በባህላዊ አደባባይ በድምቀት የማክበር ሥነ ሥርዓት ሲሆን፣ ኅብረተሰቡም በዓሉን የሚያከብረው በጎሳ በጎሳ በመሆን በተለያየ ባህላዊ ጭፈራና ባህላዊ አልባሳት ተጊጦ ነው፡፡ በክብረ በዓሉ የባህላዊው ሃይማኖት አባቶችና የጎሳ መሪዎች እንደ ማኅበራዊ ደረጃቸው በየተራ ንግግር ያደርጋሉ፣ ይመርቃሉ፣ ባሮጌው ዘመንና በአዲሱ ዘመን ላይ ያተኮሩ መልዕክቶች ያስተላልፋሉ፡፡ በጎው እንዲጎለብት አስከፊው እንዳይደገም ምክር አዘል መልዕክት ያስተላልፋሉ፤ ዘመኑ የሰላም፣ የብልጽግና የልማት ይሆን ዘንድ ቃለ ቡራኬ ያደርሳሉ፡፡
የሲዳማ ባህላዊ የዘመን መለወጫ በዓል ፊቼ - ጫምባላላ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ውክልና ጊዜያዊ መዝገብ ውስጥ የገባው በሐምሌ 2006 .. እንደነበር ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ ሐቻምና /2006ዓ.ም/ የመጀመሪያውን መንፈሳዊ ባህላዊ ቅርስ የመስቀል ክብረ በዓልን ማስመዝገቧም ይታወቃል፡፡ 
                                                                     ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ

Saturday, November 28, 2015

ከሜጋ ትያትር እስከ ኮራ እና አፍሪማ ተሸላሚነት …….. አርቲስት ፀደንያ ገብረማርቆስ


   “ገዴ” እና “ቢሰጠኝ” የተሰኙ ሁለት አልበሞች አሏት፡፡ እ.ኤ.አ በ2004 “እወድሃለሁ” በሚለው ስራዋ የኮራ ሙዚክ አዋርድ ተሸላሚ ናት፡፡ በቅርቡ ደግሞ በናይጄሪያ ሎጎስ በተካሄደው ኦል አፍሪካ ሙዚክ አዋርድስ /አፍሪማ/ በምስራቅ አፍሪካ ምርጥ የሴት ድምፃውያን ምድብ አሸናፊ ሆናለች፡፡ ለተለያዩ ፊልም እና ድራማዎች ሳውንድ ትራክ /ማጀቢያ ሙዚቃ/ ሰርታለች፡፡ ቀደም ሲል በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 በሚቀርበው የ “አይሬ” ፕሮግራም ትሰራ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 “ዜማ ፍቅር” የተሰኘ ፕሮግራምን ታቀርባለች፡፡ ሶስተኛ አልበሟንም ሰርታ አጠናቃለች፤ አርቲስት ፀደንያ ገብረማርቆስ፡፡
   አርቲስት ፀደንያ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ልዩ ልዩ ሽልማቶችን አግኝታለች፡፡ በኮራ እና በአፍሪማ አራት ጊዜ ተወዳድራ ፣ ሶስት ጊዜ ለእጩነት ቀርባ በሁለቱ አሸንፋለች፡፡ እ.ኤ.አ በ2004 ከኬንያዊቷ አቺንግ አቦራ ጋር “እወድሃለሁ” በተሰኘው ስራዋ በምስራቅ አፍሪካ ምርጥ የሴት ድምፃዊት ተብላ የሽልማቱ ተጋሪ ሆናለች፡፡ ዘንድሮ ደግሞ በ2015 ለሀርየት ፊልም ማጀቢያ በሰራችው “የት ብዬ” ዘፈን  በ24 ካራት ወርቅ የተለበጠ የአፍሪማን የዋንጫ ሽልማት አግኝታለች፡፡ በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 የለዛ ፕሮግራም የአመቱ የአድማጮች ምርጥ የፊልም ማጀቢያ በሚል “የት ብዬ” በተሰኘው ዘፈን አሸናፊ ሆናለች፡፡


  በቀድሞው ደብረ ያሬድ (ሜጋ ትያትርም) ለተወሰኑ አመታት ሰርታለች፡፡ በእንግሊዘኛ ዘፈኖች ሙዚቃን አሀዱ ያለችው አርቲስት ፀደንያ ገብረማርቆስ ቀስ በቀስ ወደ አማርኛ ስራዎች በማምራት ሁለት ያህል አልበሞችን እና በርከት ያሉ ነጠላ ዜማዎችን ለአድናቂዎቿ አድርሳለች፡፡ “ገዴ” የተሰኘው የመጀመሪያ አልበሟ በኬንያዊው አቀናባሪ ዴቪድ ኦቴኖ የተሰራ ሲሆን አምባሰል ሙዚቃ ቤት ነው የታተመው፡፡ “ቢሰጠኝ” የተሰኘው አልበሟ ደግሞ ጥበቡ ወርቅዬ ኢንተርቴይመንት የታተመ ሲሆን ቅንብሩን ዳግማዊ አሊ ሰርቶታል፡፡


   አሁን ደግሞ ሶስተኛ አልበሟን አጠናቃ ለአድናቂዎቿ ለማድረስ ጉድ ጉድ እያለች ትገኛለች፡፡ የዚህ አልበም በዛ ያሉት ግጥሞች የይልማ ገብረአብ ሲሆኑ ጌትነት እንየው፣ አብዲራዋ (የህመሜ ደራሲ) እና ፋሲል ከበደ ተሳትፈዋል፡፡ አብዛኛዎቹን ዜማዎች እሷ እራሷ ናት የሰራቻቸው፡፡ ቅንብሩን ደግሞ አቤል ጳውሎስ፡፡ ሙዚቃ ስትጀምር አማርኛ እንዳትዘፍን የተባለችው ይህቺ ድምፃዊት የሀገሯን ሙዚቃ በአለም መድረክ እያስተዋወቀች ትገኛለች፡፡ በዚህም በርካታ ሽልማቶችን ተጎናፅፋለች፡፡


  እ.ኤ.አ በ2003 ከግርማ ይፍራሸዋ ጋር የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትን በመዘዋወር ስራዎቿን አቅርባለች፡፡ በ2009ም በወርልድ ሙዚክ ከእነ ፈለቀ ሀይሉ (ሳክስፎን) ፣ ሳሙኤል ይርጋ (ፒያኒስት) ፣ ተራማጅ ወረታው (ማሲንቆ) እንዲሁም ስንታየሁ ዘነበ እና እሷ ሆነው ሁለት አልበሞችን ሰርተው በአለም አቀፍ ፌስቲቫሎች ላይ ተሳትፈዋል፡፡
   

  ከኤዘር ኦርኬስትራ ጋርም አልያንስ - ኢትዮ ፍራንሲስ ከውጪ በመጡ የሙዚቃ ባለሙያዎች ታጅባ “ባቲ” የተሰኘ ስራዋን አቅርባለች፡፡ ከዚያም በኋላ ከጋሽ መሀሙድ አህመድ ጋር በፈረንሳይ ሀገር ዝግጅቶቿን አሳይታለች፡፡ ድምፃዊት ፀደንያ ገብረማርቆስ ከድምፃዊነት፣ ዜማ ደራሲነት እና ፕሮግራም አቅራቢነት ባሻገር ቀደም ብላ ማስታወቂያዎችንም ትሰራ ነበር፡፡ ለአብነትም አብወለድ ፣ ገርልጊ ፣ ካዲስኮ እና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡

  ትውልዷ እና እድገቷ እዚሁ መዲናችን አዲስ አበባ የሆነው ፀደንያ የመንታ ወንድ ልጆች እናት ናት ፡፡ ቀሪ ዘመኗም የስኬት እና ብልፅግና እንዲሆን በመመኘት እኔ ፅሁፌን በዚሁ ላብቃ ሌላውን እናንተ ጨምሩበት ……

Wednesday, November 4, 2015

በስለት ተወልዶ በስስት ያደገው …… ድምፃዊ ኪሮስ አለማየሁ


  በስለት ተወልዶ በስስት እንዳደገ ይነገርለታል፡፡ 1944. ትግራይ ክልል ፀአዳ አምባ ወረዳ ሰንደዳ ቀበሌ ነው የተወለደው ድምፃዊ ኪሮስ አለማየሁ፡፡ የቤተ ክህነት እውቀትን የቀሰመው ኪሮስ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በፍሬወይኒ ውቅሮ እና አፄ ዮሀንስ /ቤቶች ተከታትሏል፡፡ በመምህርነት እና በሀላፊነትም ሰርቷል፡፡ ከዚያም ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በራስ ትያትር ለአምስት አመታት ያህል የትግርኛ ሙዚቃዎችን ተጫውቷል፡፡ የመጀመሪያ አልበሙንም ራስ ትያትር እያለ ከሸበሌ ባንድ ጋር በመሆን ለአድናቂዎቹ አድርሷል፡፡
   

   1970ዎቹ አጋማሽ  በአዲስ  አበባ  ማዕከላዊ  እስር  ቤት  ታስሮ  የነበረው  ኪሮስ  አለማየሁ  በኪነቱ  ውስጥ  በነበረው  ቆይታ  በርከት  ያሉ  አስደሳች  አሳዛኝ እና አስቂኝ  ነገሮችን አሳልፏል፡፡ በስራዎቹም  ለትግሪኛ  ሙዚቃ  እድገት  ከፍተኛ  አስተዋፅኦ  አድርጓል፡፡ በተለያዩ   ርዕሰ  ጉዳዮች  ላይ  ያቀነቀነው  አንጋፋው  ድምፃዊ  ግጥም እና ዜማ  ይደርሳል፤ ዋሽንት  እና ክራር  የመሳሰሉትን  የሙዚቃ  መሳሪያዎችም  ይጫወታል፡፡

  
ድምፃዊ ኪሮስ አለማየሁ ነገሮችን እና ሁኔታዎችን አይቶ የመድረስ እና ከዜማ ጋር አዋህዶ የመጫወት ተሰጥኦው ላቅ ያለ ነው ይባልለታል፡፡ በአንድ ወቅትም ባለቤቱ አዲስ ሙሽራ ሆና ስትስቅ ስትጫወት እሷን በማየትአይቁንጅናየተሰኘውን ስራ እንደሰራው እና ከዚያም 1983. በካሴት እንዳሳተመው ይነገራል፡፡


ድምፃዊ ኪሮስ አለማየሁ በግሉ አምስት ከሌሎች ድምፃውያን ጋር ደግሞ ሁለት ያህል አልበሞችን ሰርቷል፡፡ ድምፃዊው በጥቅምት ወር 1986. ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል፡፡ በስሙ ቤተ መፅሃፍት የተቋቋመለት ሲሆን ከመቀሌ ዩኒቨርስቲም የክብር ዶክትሬትን አግኝቷል፡፡ በቅርቡም የህይወት ታሪኩን በተመለከተ መፅሃፍ ተፅፎለታል፡፡ እሱ በህይወት ባይኖርም ስራዎቹ ህያው ናቸው እና ሁሌም ሲታወስ ይኖራል፡፡