Thursday, September 5, 2013

ከጅቡቲ ድሬዳዋ ያለው የባቡር መስመር አገልግሎት መስጠት ጀመረ

 
 የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር አካል የሆነው ከጅቡቲ እስከ ድሬዳዋ ያለው የባቡር መስመር እድሳቱ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።  ከ1890 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ይኼው የባቡር መስመር በደረሰበት ብልሽት ምክንያት መቋረጡ በድሬዳዋ ከተማ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉን ነው የከተማዋ ነዋሪዎች የሚናገሩት።

    የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ አየለ ወንደወሰንም በነዋሪዎቹ ሀሳብ ይስማማሉ ። ይህ የሆነውም ባለ አንድ ሜትር የሀዲድ ስፋት እና ከድሬዳዋ ጅቡቲ ድረሰ የ308 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የባቡር መስመር በማርጀቱ ምክናይት ጥገና እንዲደረግለት መቋረጡን በማንሳት። እሳቸው እንደሚሉት በኢትዮጵያ በኩል ካለው 208 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ውስጥ ፥ ጥገና የሚያስፈልገውን 100 ኪሎ ሜትር ለመጠገን ስራውን የወሰደው የጣሊያን ድርጅት 23 ኪሎ ሜትሩን ብቻ ጠግኖ ስራውን አቁሞ ነበር ። ይህ ሁኔታም በሶስት አመት ውስጥ እንዲጠናቀቅ የታቀደውን እድሳት በስድስት አመት ውስጥ እንዲጠናቀቅ ማድረጉንም ያስረዳሉ።

     መንግስት ጉዳዩን እያጣራው ቢሆንም የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት ግን በራሱ አቅም ቀሪውን የባቡር ሀዲድ በመጠገን አሁን ላይ ስራውን እንዲጀምር ማድረጉንም ተናግረዋል።አገልግሎቱም ሀምሌ ወር አጋማሽ ላይ በሙከራ ከተጀመረ በኋላ ከሀምሌ 23 2005 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሙሉ ስራው በመግባት ከድሬዳዋ እስከ ጅቡቲ በሳምንት ሶስት ግዜ መንገደኞችን የማጓጓዝ ስራው እየተካሄደ ይገኛል ። በተለይ ወቅቱ የጅቡቲ ነዋሪዎች በሙቀት ምክንያት ወደ ድሬዳዋ የሚመጡበት በመሆኑ የአገልግሎቱ መጀመር ለከተማዋ እንቅስቃሴ መነቃቃት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ነው የሚሉት ሃላፊው ። እስከ አሁንም በኢትዮጵያ በኩል ከ4 ሺህ 800 በላይ መንገደኞች ማጓጓዝ የተቻለ ሲሆን ፥ የድሬዳዋ ነዋሪዎችም ከጆሯቸው ርቆ የነበረውን የባቡር ጡሩምባ በመስማታቸውና በአገልግሎቱ መጀመር መደሰታቸውን ተናግረዋል።


      አቶ አየለ እንደሚሉት ድርጅቱ በቅርቡም የጭነት ትራንስፖርት ለመጀመር አስፈላጊው ዝግጅት አድርጓል ። አሁን ያለው ባቡር አራት ተሳቢዎችን የሚይዝ ሲሆን በሂደት ይህን ከፍ በማድረግ የሎጂስቲክ አገልግሎትን ለመጀመር ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ስምምነት መፈጸማቸውንም ነው የተናገሩት። ቀሪው ከድሬዳዋ አእስከ አዲስ አበባ ያለው መስመር ፥ በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አማካኝነት እየተካሄደ ባለው የባቡር መስመር ዝርጋታ የሚገናኝ ይሆናል ።

No comments:

Post a Comment