Thursday, February 28, 2013

የኢትዮጵ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛውን ፓትርያርክ መረጠች

  ዛሬ ከጧት ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛውን ፓትርያርክ ለመምረጥ በተደረገው ሂደት መሠረት 806 መራጮች ድምጽ የሰጡ ሲሆን ከሰዓት በኋላ በተደረገው ድምጽ ቆጠራ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ በ500 ድምጽ በመመረጥ የመጀመሪያውን ድምጽ በማግኘት 6ኛው ፓትርያርክ ሆነዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ 39 ድምጽ፤ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ 98 ድምጽ፤ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ 98 ድምጽ፤ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል 70 ድምጽ በማምጣት ምርጫው ተጠናቋል፡፡ አንድ የድምፅ መስጫ ፎርም ምልክት ሳይደረግበት በመገኘቱ  ውድቅ ሆኗል፡፡


   ፓትርያርክ ሆነው የተመረጡት ብፁዕ አቡነ ማትያስ በመጨረሻ ባስተላለፉት መልእክት “ከእግዚአብሔርና ከሕዝበ ክርስቲያኑ የተሰጠኝን አደራ ለመወጣት ከብፁዓን አባቶች፣ ካህናትና ከምእመናን ጋር አብረን ስለምንሠራ ሥራው የቀለለ ይሁናል ብዬ አምናለሁ” ብለዋል፡፡ የብፁዕ አቡነ ማትያስ በዓለ ሹመት የፊታችን እሑድ የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም. በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የሚፈጸም ሲሆን፣ ሥነ ሥርዓቱም ከተለያዩ አገሮች የሚመጡ ሊቃነ ጳጳሳት በሚገኙበት ይካሄዳል፡፡ በዓለ ሹመቱ በኮፕቲክ ቴሌቪዥን በቀጥታ ሥርጭት እንደሚተላለፍ ለማወቅ ተችሏል፡፡ እሑድ በዓለ ሹመቱ ከተፈጸመ በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ ተመልክቷል፡፡ ለምርጫው በአጠቃላይ ብር 3,650,000 ወጪ መደረጉን የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ተናግረዋል፡፡

   አስመራጭ ኮሚቴው አራት ንኡሳን ክፍሎች ነበሩት፡ – የመራጮች ምዝገባና ቁጥጥር፤ የሕዝብ ግንኙነት ንኡስ ክፍል፤ የሎጅስትክ ንኡስ ክፍል፤ የሒሳብና በጀት ንኡስ ክፍል ናቸው፡፡ ከግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተሳተፉት መራጮች፡- ብፁዕ አቡነ ጳኩሚስ፣ ብፁዕ አቡነ ራፋኤል፣ ብፁዕ አቡነ ቢነም፣ ብፁዕ አቡነ ቢሾይ፣ ብፁዕ አቡነ ሂድራ ሲሆኑ በታዛቢነት የተወከሉት ካሚል ሚሸል ናቸው፡፡ የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቪዥን ጣቢያ(ሲቲቪ) የምርጫ ውሎውን በቀጥታ ሥርጭት አስተላልፏል፤ ለበዓለ ሹመቱም ተመሳሳይ ሽፋን እንደሚሰጥ ተገልጧል፡፡ ራሳቸውን ሸሽገው የቆዩት ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በምርጫው የቀትር በኋላ ውሎ ተገኝተዋል፡፡


No comments:

Post a Comment