ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እና ከግርማዊት እቴጌ መነን ልጅ ከልዕልት ተናኘ ወርቅ እና ከጀግናው ክቡር ራስ ደስታ ዳምጠው መጋቢት 3ዐ ቀን 1919 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የተወለዱት ልዕልት አይዳ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዋ የዩኒቨርሲቲ የሴት ተማሪ በመሆን በእንግሊዝ ሀገር ስመጥር በሆነው ኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ትምህርት በዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ ልዕልቷ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኛ ኮሚሽነር ተወካይ ሆነው አገልግለዋል፡፡
በ1941 ዓ.ም. ከልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ጋር ጋብቻቸውን ፈጽመው ፣ በ64 ዓመት የትዳር ሕይወታቸው ስድስት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን የ11 ልጆች አያትና የሦስት ልጆች ቅድመ አያት ነበሩ፡፡ በደርግ ዘመነ መንግስት ከታሰሩት የንጉሳውያን ቤተሰብ ውስጥ አንዷ
ልዕልት አይዳ ደስታ ናቸው፡፡ በዚህም ለ14ዓመታት በእስር ቆይተዋል፡፡
ልዕልት አይዳ ከእስር ከወጡ በኋላ ከባላቸው እና ከልጆቻቸው በስደት ቆይተዋል፡፡ የደርግ ስርዓት ከተገረሰሰ በኋላም በዋሽንግተን ዲሲ እና በአዲስ አበባ አሳልፈዋል፡፡ በመጨረሻም ጥር 16 ቀን 2005 ዓ.ም በ85 ዓመታቸው በአሌክዛንደሪያ ቨርጂኒያ ህይወታቸው አልፎ በአዲስ አበባ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የቀብር ስነ - ስርዓታቸው ተፈፅሟል፡፡
በቀብራቸው ላይም ባለቤታቸው ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም፣ ልጆቻቸውና ልዑላንና ልዑላት
፣ በሺሕ የሚቆጠሩ ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዓቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጸሎተ ፍትሐቱን የመሩ ሲሆን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትም ተገኝተዋል፡፡
No comments:
Post a Comment