አዲስ አበባ በዋና ከተማነት ከተቆረቆረችበት ከ1879ዓ.ም በተለይም ከ1880ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ማዕከል በመሆን በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡ ከተማዋ የምዕተ አመቱን ጉዞ የሚዘክሩ፣ ለተፈፀሙት ታሪካዊ ክንዋኔዎች ገላጭ እና አስረጂ የሆኑ ቅርሶችንም በውስጣ ይዛለች፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ በየጊዜው የተከናወኑ ታሪካዊ ድርጊቶችን እንዲሁም በታሪኩ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያላቸውን ግለሰቦች ለማስታወስ የቆሙ ሀውልቶችም አሉ፡፡ ለመታሰቢያነት ከቆሙት ሀውልቶች አንዱ የሆነውን ለዛሬ በአጭሩ ለማየት እንሞክራለን፡፡
በመዲናችን አዲስ አበባ ስላሉት ሀውልቶች ሲነሳ በቅድሚያ የሚጠቀሰው የቀድሞው አራዳ የአሁኑ ፒያሳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ከአራዳ ጊዮርጊስ ፊት ለፊት የቆመው የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሀውልት ነው፡፡ በፀረ ኮሎኒያሊዝም ትግላቸው እና የዘመናዊ ስልጣኔን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት ለሚታወቁት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ማስታወሻ እንዲሆንላቸው ልጃቸው ንግስተ ነገስት ዘውዲቱ ያሰሩት ሀውልት ነው፡፡ የሀውልቱን ንድፍ ያዘጋጀው ጀርመናዊው አርክቴክት ሀርቴል/ሀርሴል/ ስፔንግለር ሲሆን የተሰራበት ቁሳቁስም ከነሀስ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
አፄ ምኒልክ የፊት ሁለት እግሮቹን ወደ ላይ አንስቶ የሚጋልብ ግዙፍ ፈረስ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ በእጃቸው ጣምራ ጦር ይዘው ከራሳቸው ላይ ደግሞ ዘውድ ደፍተዋል፡፡ በጥሩ ሁኔታ እየተቀለበ እንደኖረ የሚያስታውቀው ፈረሳቸው ከእነ ሙሉ ጌጡ ይታያል፡፡ አባ ዳኛው እየተባለ የሚጠራው የአፄ ምኒልክ ፈረስ ፊቱን ወደ ሰሜን አድርጓል፡፡ ይህም ለመላው ጥቁር ህዝብ ኩራት የሆነውን ታሪክ ወደ አስመዘገበበት አድዋ ለማመላከት ነው፡፡ንግስት ዘውዲቱ ጀርመን ሀገር ድረስ ልከው በልዩ ትዕዛዝ የአባታቸው ማስታወሻ እንዲሆን ያሰሩትን ይህን ሀውልት በሀገራቸው ቆሞ ሳያዩት ነው በድንገት የሞቱት፡፡ ይሁንና የሀውልቱ ስራ ተጠናቆ ጥቅምት 22 /1923ዓ.ም ተመርቋል፡፡ በጣሊያን ወረራ ጊዜ አንዳንድ መረጃዎች ሙሉ በሙሉ ተነቅሎ እነዲቀበር ተደረጓል ሲሉ ሌሎች ደግሞ ተነቅሎ ተወስዷል ይላሉ፡፡ ያም ሆን ይህ በአርበኞች ተጋድሎ ጣሊያን ሀገሪቷን ከለቀቀ እና ነፃ ከወጣች በኋላ እንደገና ተጠግኖ እና ታድሶ መጀመሪያ በነበረበት ቦታ ላይ ሚያዚያ 27 /1934ዓ.ም ዳግም ተተክሏል፡፡ ከዚያም የአድዋ 100ኛ አመት ሲከበር እድሳት ተደርጎለታል፡፡ ይህ ሀውልት ዛሬ ድረስ የኢትዮጵያን ህዝብ ታሪክ እና ጀግንነት የሚያስመሰክር ህያው ቅርስ ሆኖ ይገኛል፡፡