Monday, April 14, 2014

ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በተለያዩ ከተሞች በተካሄዱ የማራቶን ውድድሮች ባለድል ሆኑ

 ጥሩነሽ የማራቶን ሩጫ ህይወትን በጥሩ ውጤት ጀመረች

2014 ለንደን ማራቶን ባለድሎች — (ከግራ ወደ ቀኝ) — ፍሎረንስ፣ ኤድና እና ጥሩነሽ

   10 ሺህ እና 5 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድሮች በተደጋጋሚ የአለም ሻምፒዮን እና የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያዎች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ የረጅም ርቀት ሩጫ ንግስት ጥሩነሽ ዲባባ በጉዳት ምክንያት ለአንድ አመት ያህል ባዘገየችው የመጀመሪያዋ በሆነው የለንደን ማራቶን ርቀቱን 2 ሰአት 20 ደቂቃ 35 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ ሶስተኛ ደረጃን አግኝታ የማራቶን ሩጫ ህይወትን ጀምራለች። ጥሩነሽ ርቀቱን ሮጣ የጨረሰችበት ሰአት (2:20:35) ማራቶንን ለመጀመሪያ ጊዜ በሮጡ ሴት አትሌቶች ታሪክ ሶስተኛው ፈጣን ሰአት ሆኖ ተመዝግቧል። 

    ጥሩነሽ ዲባባ  ከኬኒያዎቹ ኤድና ኪፕላጋት እና ፍሎረንስ ኪፕላጋት ጋር እስከ 30ኛው ኪሎሜትር ድረስ አብራ በተረጋጋ ሁኔታ ብትሮጥም ጥቂት ከተጓዙ በኋላ ውሀ ለመጠጣት በሚል ወደጎን የወጣችው ጥሩነሽ የውሀ ላስቲኩ ከእጇ ላይ ድንገት በመውደቁ እና ያንን ከመሬት ለማንሳት በመቆሟ ኤድና እና ፍሎረንስ አጋጣሚውን ተጠቅመው በማፈትለካቸው ከጥሩነሽ ጋር የነበራቸው ልዩነት ሊሰፋ ችሏል። 

ጥሩነሽ በመሪዎቹ ሁለት ኬኒያዊያን እና በሷ መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለማጥበብ ብትሞክርም በማራቶን ከሷ የተሻለ ልምድ ያላቸው ኤድና እና ፍሎረንስ ላይ ለመድረስ ባለመቻሏ ሶስተኛ ደረጃን አግኝታ ውድድሯን ለማጠናቀቅ ተገዳለች።


  ከጥሩነሽ ጋር በሴቶቹ የለንደን ማራቶን ከተሳተፉት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች መካከል ከሁለት አመት በፊት በተካሄደው የለንደን ኦሎምፒክ በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፈችው ቲኪ ገላና ዘጠነኛ ደረጃን አግኝታ ውድድሯን ስታጠናቅቅ፣ ፈይሴ ታደሰ አራተኛ፣ አበሩ ከበደ አምስተኛ በመሆን ውድድራቸውን ጨርሰዋል። ኬኒያዊቷ ኤድና ኪፕላጋት ርቀቱን 220:21 በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ የዘንድሮው የለንደን ማራቶን አሸናፊ ስትሆን፣ የሀገሯ ልጅ ፍሎረንስ ኪፕላጋት በሶስት ሰከንዶች ዘግይታ ሁለተኛ ደረጃን አግኝታ አጠናቃለች።

    በወንዶቹ የለንደን ማራቶን ውድድር የአምናው ሻምፒዮን ኢትዮጵያዊው ጸጋዬ ከበደ ርቀቱን 206:30 በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ ሶስተኛ ደረጃን አግኝቶ ጨርሷል። ጸጋዬ ከውድድሩ በኋላ በሰጠው አስተያየት -
ምንም እንኳን ማሸነፍን አላማዬ አድርጌ ለውድድሩ ብገባም የርቀቱን ግማሽ ያህል ከሮጥን በኋላ ሰውነቴ አቅሙን ሲያጣ ስለተሰማኝ መሪዎቹ ላይ እንደማልደርስባቸው በማረጋገጤ ቢያንስ ሶስተኛ ደረጃን አግኝቼ ለማጠናቀቅ በሚል ያደረኩት ጥረት ስለተሳካልኝ ተደስቻለሁብሏል።

   ከጸጋዬ ከበደ ጋር በወንዶቹ ውድድር የተሳተፉት ኢትዮጵያዊያኖቹ አየለ አብሸሮ አራተኛ፣ ጸጋዬ መኮንን አምስተኛ፣ ፈይሴ ሊሌሳ ዘጠነኛ ደረጃን አግኝተው አጠናቀዋል።
ኬኒያዊው የአለም የማራቶን ክብረውሰን ባለቤት ዊልሰን ኪፕሳንግ የስፍራውን ክብረወሰን በማሻሻል ርቀቱን 20429 በሆነ ጊዜ አጠናቆ ለሁለተኛ ጊዜ የለንደን ማራቶን ሻምፒዮን ሲሆን፣ የሀገሩ ልጅ ስታንሊ ቢዎት 204:55 ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን ጨርሷል።

  ኦስትሪያ ውስጥ በተካሄደው አመታዊው የቪዬና ከተማ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊው ጌቱ ፈለቀ የስፍራውን ክብረወሰን በመስበር አሸንፏል። ርቀቱን 205:41 በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ ድልን የተጎናጸፈው ጌቱ ፈለቀ ከድሉ በኋላ በሰጠው አስተያየት -
ውድድሩ ሊያበቃ ሁለት ኪሎ ሜትሮች ያህል ሲቀሩት ሆዴ አካባቢ ህመም ባይሰማኝ ኖሮ ከዚህ የበለጠ ፈጣን በሆነ ሰአት ማጠናቀቅ እችል ነበር። ያም ቢሆን ግን ከንፋሱ በስተቀር ውድድሩ ጥሩ ሆኖ አግኝቼዋለሁብሏል።

 ጌቱ ፈለቀ ከአምስት አመት በፊት በሩጫ ህይወቱ የመጀመሪያው የሆነውን የማራቶን ውድድር ያደረገው ቪዬና ውስጥ ሲሆን የእሁድ እለት ድሉ .. 1998 . የሀገሩ ልጅ ሞገስ ታዬ ድል ካረገ በኋላ የቪዬና ማራቶንን ያሸነፈ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አትሌት እንዲሆን አብቅቶታል።
ኬኒያዊያኖቹ አልፍሬድ ኬሪንግ እና ፊሊፕ ኪሙታይ ጌቱ ፈለቀን ተከትለው እንደቅደም ተከተላቸው ሁለተኛ እና ሶስተኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

   በሴቶቹ የቪዬና ከተማ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ማርታ ለማ ርቀቱን 2:3110 በማጠናቀቅ ሶስተኛ ሆና ጨርሳለች። ጀርመናዊቷ አና ሀነር ውድድሩን ስታሸንፍ፣ ኬኒያዊቷ ካሮላይን ቼፕኩዌኒ ሁለተኛ ደረጃን በማግኘት አጠናቃለች።

  ሆላንድ ሮተርዳም ከተማ ውስጥ በተካሄደው አመታዊው የሮተርዳም ማራቶን ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አበበች አፎወርቅ ርቀቱን 227:50 በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ ባለድል ስትሆን፣ የሀገሯ ልጅ ጉተኒ ሾኔ 2:3023 በሆነ ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን አግኝታ አጠናቃለች።

   ባለድሏ አበበች የውድድሩ መጀመሪያ አካባቢ ውሀ ለመጠጣት በሚል ያነሳችው ላስቲክ ወድቆባት እሱን ለማንሳት በመቆሟ ምክንያት ተፎካካሪዎቿ አጋጣሚውን ተጠቅመው ቀድመዋት ቢሄዱም ውድድሩ ሊጠናቀቅ ሁለት ኪሎ ሜትሮች ያህል ሲቀሩት ተፎካካሪዎቿ ላይ ከመድረሷ በተጨማሪ ቀድማቸው በመሄድ ማሸነፏ አድናቆትን አስገኝቶላታል።
                                ምንጭ ፡- ቶታል 433

No comments:

Post a Comment