Tuesday, November 25, 2014

“አንተ ጎዳና” እና የድምፃዊ ሚካኤል በላይነህ የህይወት ጉዞ …

   
  ድምፃዊ እና የዜማ ደራሲ ነው፡፡ ወደ ሙዚቃው ከገባባት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ርዕሰ - ጉዳዮች ዙሪያ በርከት ያሉ ስራዎችን ሰርቷል፡፡ ሁለት ያህል አልበሞችም አሉት በግሉ ማለት ነው፡፡ ከግርማ ይፍራሸዋ ጋር የሰሩትም “መለያ ቀለሜ” የተሰኘ አልበም አለው፡፡ ሙዚቃን የጀመረው በእንግሊዘኛ ዘፈኖች ነው፡፡ “ሳይሽ እሳሳለሁ” ፣ “ውበትን ፍለጋ” ፣ ከዘሪቱ ከበደ ጋር የተጫወተው “ታምሪያለሽ” እና “ትዝታ” ከሰራቸው ነጠላ ዜማዎች  መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ አርቲስት ሚካኤል በላይነህ፡፡ 

   ለቤተሰቦቹ 4ኛ እና የመጨረሻ ልጅ የሆነው ድምፃዊ ሚካኤል በላይነህ ትውልዱ አራት ኪሎ ሲሆን እድገቱ ደግሞ ኮተቤ አካባቢ ነው፡፡ በደጃዝማች ወንድራድ ፣ በገዳመ -ሴታውያን እና በጥቁር አንበሳ ት/ቤቶች ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ተምሯል፡፡ ከባህር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ዩኒቨርስቲ በኢንዱስትሪያል ኤለክትሪክሲቲ በአድቫንስ ዲፕሎማ ተመርቋል፡፡ ከዚያም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፖለቲካል ሳይንስ እና አለም አቅፍ ግንኙነት ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ በያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ፒያኖ ተምሯል፡፡ ከዚህም ባሻገር ኦን ላይን የተለያዩ ስልጠናዎችን በመውሰድ የሙዚቃ ክህሎቱን እያዳበረ ይገኛል፡፡

በኢንዱስትሪያል ኤሌክትሪክሲቲ ከተመረቀ በኋላም በከተማ ፕላን ለአራት አመት ያህል አገልግሏል፡፡ በወቅቱ ይከፈለው የነበረው 420 ብር ስላላረካው ወደ ሌሎች ሙያዎች እና ሙዚቃ ተሸጋገረ፡፡ ከዚያም ቦሌ መንገድ “ፐርፕል” የሚባል ካፌ ከሌሎች ሰዎች ጋር ከፍቶ ይሰራም ነበር፡፡ ካፌው ተወዳጅ በመሆኑ በርካታ ሰዎች ይስተናገዱበት ነበር አርቲስቶችን ጨምሮ፡፡ ለአብነትም ላፎንቴኖች ፣ ጆኒ ራጋ ፣ ኤልያስ መልካ እና ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ ይጠቀሳሉ፡፡

     አርቲስት ሚካኤል በላይነህ የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮችን በማንሳት በዛ ያሉ ስራዎችን ሰርቷል፡፡ ለአፍሪካ ህብረት በተሰራ ዘፈን ላይ በድምፅ ተሳትፏል፡፡ በተለይ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ  ዙሪያ የተሰሩ ስራዎች ላይ በርከት ያሉ ዜማዎችን ደርሷል፡፡ በድምፅም ተሳትፏል፡፡ የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፡- “ማለባበስ ይቅር - ማወቅ ነው መሰልጠን” ፣ “መላ መላ” ፣ “መታመን ማመን ነው ” ፣ “ኦሮሚኛ - መሌ ሀራ” እና ሌሎች አራት ያህል ዜማዎችን ሰርቷል፡፡
   
  በቅርቡም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ /አባይ/ “ከፍ እንበል” የተሰኘውን ዘፈን ዜማ ደርሷል፡፡ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘም ከዘሪቱ ከበደ ጋር በመሆን “ኢትዮጵያ አረንጓዴ” የሚል ስራም ሰርቷል፡፡ በተጨማሪም ለስኳር ህሙማን የተሰራ “ስኳርን አየሁት” የሚል ዜማም አለው፡፡ ይህንን ዘፈን አብነት አጎናፍር ፣ ግርማ ተፈራ ፣ ሀይልዬ ታደሰ እና ጥላሁን ገሰሰ ተጫውተውታል፡፡


     በአንድ ወቅት በሽራተን አዲስ በተደረገ ዝግጅት ላይ ከእነ ጥላሁን ገሰሰ ፣ መሀሙድ አህመድ ፣ ምኒሊክ ወስናቸው እና ሀመልማል አባተ ጋር ስራውን አቅርቧል፡፡ በጊዜው ከመዲና ባንድ ጋር ከጥላሁን ገሰሰ ቀጥሎ በሁለተኛነት ስራዎቹን ተጫውቷል፡፡ ድምፃዊ ሚካኤል በላይነህ ለራሱም ሆነ ለሌሎች አርቲስቶች በርከት ያሉ የዜማ ድርሰቶችን ሰርቷል፡፡ “አንተ ጎዳና” ከተሰኘው አልበሙ ከ11 ስራዎቹ 9ኙ የእሱ የዜማ ድርሰቶች ናቸው፡፡ “ናፍቆት እና ፍቅር” ከሚለው አዲሱ አልበም ደግሞ ከ13ቱ 11 ያህሉን ዜማ የሰራው እራሱ ነው፡፡ በቀጣይም ለሌላ አልበም ስራ እየተዘጋጀ ነው፡፡ ተጨማሪ መረጃዎችን እናንተ አክሉበት…….!!!




No comments:

Post a Comment