Thursday, November 6, 2014

ተንቀሳቃሹ ቤተ- መዘክር ……. አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ


     በብዙዎች ዘንድ ተንቀሳቃሽ ቤተ መዘክር ተብለው ይታወቃሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ትያትር ህንፃው ታንፆ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ስማቸው አብሮ ይጠራል፡፡ አንዳንድ ጓደኞቻቸውም ሆኑ በቅርብ የሚያውቋቸው ስለ ብሄራዊ ትያትር መረጃ ሲፈልጉ ወደ እሳቸው መሄድን ይመርጣሉ፡፡ እኚህ ሰው ደራሲ ብቻ ሳይሆኑ የመድረክ ተዋናይ እና የትያትር አዘጋጅም ናቸው፡፡ አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ፡፡
 
  አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ ከአዲስ አበባ 50 ያህል ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው አዲስ አለም ሚያዚያ 20/1928 ዓ.ም ነው የተወለዱት፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ ከተማቸው በአዲስ አለም እስከ 6ኛ ከተማሩ በኋላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተልም ወደ አዲስ አበባ መጡ፡፡

  በአዲስ አበባም ልባቸው ወደ ሙዚቃው እና ትያትሩ በመሳቡ ትምህርታቸውን ብዙም ሳይገፉ አቋረጡ፡፡ በተስፋ ኮኮብ ት/ቤትም ከአንድ ሴሚስተር በላይ እንዳልገፉም ይነገራል፡፡


 ገና በወጣትነት እድሜያቸው በ1944ዓ.ም በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የትያትር እና ሙዚቃ ማስፋፊያ ክፍል ውስጥ በመግባት ስራን አሀዱ አሉ፡፡ከዚያም ከተወሰኑ አመታት በኋላ ከማዘጋጃ ቤት ወደ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ትያትር በመዛወር የህይወታቸውን ብዙውን ምዕራፍ በትያትር እና በሙዚቃው ዘርፍ አሳልፈዋል፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ የትያትር ተመልካቹ ቁጥር በጣም ትንሽ ነበር፡፡ እነዚህን ተመልካቾች ለመሳብም መንገድ ዳር በመውጣት ዘፈን በመዝፈን እና ትያትሩን በማስተዋወቅ ሰው ሲገባ ልብሳቸውን ቀይረው ይሰሩ እንደነበርም ያወሳሉ፡፡


   በ1946ዓ.ም ጀምሮ ነው የራሳቸውን የትያትር ድርሰት መፃፍ የጀመሩት፡፡ አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ በትያትሩ ዘርፍ ባሳለፏቸው 50 ዓመታት 52 ትያትሮችን ተጫውተዋል፤ 15 ያህል ተውኔቶችን አዘጋጅተዋል፤ 10 ያህል ድርሰቶችን ደግሞ ራሳቸው ደርሰው ለመድረክ አብቅተዋል፡፡ ከተወኑባቸው ትያትሮች መካከል ለአብነት ጥቂቶቹን አናንሳ ፡-

“ዳዊት እና ኦሪዮን፣ ጎንደሬው ገብረማሪያም፣ የሺ /የፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ ድርሰት ነው/ ፣ የፌዝ ዶክተር /ዶክተር ሆነው የተወኑበት/ ፣ አወናባጅ ደብተራ / ደብተራ ሆነው የተጫወቱበት/ ፣ በልግ / ወፈፌው ሰዓሊ/ ፣ የከርሞ ሰው / 3 ሆነው የተወኑበት ሲሆን ፡- አውላቸው ደጀኔ፣ ተስፋዬ ሳህሉ እና ጌታቸው ደባቄ ተሳትፈውበታል/ ፣ ዋናው ተቆጣጣሪ / ከንቲባ ሆነው/ ፣ ሀሁ በ6ወር ፣ ቴዎድሮስ ፣ ስነ - ስቅለት፣ ኦቴሎ ፣ አምሌት ፣ የአዛውንቶች ክበብ ፣ አፅም በየገፁ ፣ ሀኒባል ፣ ተሀድሶ ፣ ሻጥር በየፈርጁ ፣ በቀይ ካባ ስውር ደባ ፣ የአመፃ ልጆች እና እርጉም ሀዋሪያ” ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡


     አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ ከ 1944 - 1946 ዓ.ም ድረስ በማዘጋጃ ቤት በነበራቸው ቆይታ “ድንገተኛ ጥሪ ፣ እድሜ ልክ እስራት እና የፍቅር ጮራ” ትያትሮች ላይ ተውነዋል፡፡ ከላይ ለመጥቀስ የተሞከሩትን ብዙዎቹን በብሄራዊ ትያትር እያሉ የሰሩባቸው ናቸው፡፡ ጡረታ ከወጡ በኋላም “በንጉስ አርማህ” ትያትር ላይ ተውነዋል፡፡እሳቸው ከደረሷቸው ትያትሮች መካከል “በድሉ ዘለቀ” የመጀመሪያ ስራቸው ሲሆን በመዘጋጃ ቤት ነው የታየው፡፡ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ትያትር ቤት ከታዩት መካከል ደግሞ “የፍቅር ሰንሰለት ፣ ያስቀመጡት ወንደ ላጤ ፣ ደህና ሁኚ አራዳ  እና የሮምነሽ” የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ 


   በሙዚቃው ረገድም በርከት ያሉ ግጥም እና ዜማዎችን ደርሰው ለተለያዩ ድምፃውያን ሰጥተዋል ፡፡ የተወሰኑትን ለማየት እንሞክር፡-
1.  ለ ግርማ ነጋሽ  - / የኔ ሀሳብ ፣ ምነው ተለየሽኝ ፣ እንገናኛለን እና አልበቃኝም ገና/
2.  ለ አባባ ተስፋዬ /ተስፋዬ ሳህሉ/ -  አለም እንዴት ሰነበተች
3.  ለ አስናቀች ወርቁ - / በል ተነሳ ልቤን ጨምሮ 9 ያህል ስራዎችን /
4.  ለ ምኒሊክ ወስናቸው - / አደረች አራዳ ፣ አልማዝዬ አሰብኩሽ /
5.  ለ መኮንን  በቀለ - / ፍቅርን እውር ነው አትበሉ / እንዲሁም
6.  ለ ጠለላ ከበደ - / ሎሚ ተራ ተራ እና ሌሎችንም ደርሰዋል፡፡
  
    ሎሚ ተራ ተራ በሚለው የግጥም ስራቸውም በደርግ ዘመነ መንግስት ለ 4 ዓመት ያህል ታስረዋል፡፡ በእስር ቤት ቆይታቸውም “ደንቆሮ በር” የሚል መፅሀፍ አሳትመዋል፡፡ መፅሀፉ የእስር ቤት ቆይታቸውን የሚያወሳ ሲሆን በጊዜው ያዩትን፣ የታዘቡትን እና አጠቃላይ የእስር ቤቱን ሁኔታ የሚያሳይ ነው፡፡ የደንቆሮ በር መፅሀፍ ከ 60 - 70 ገፆች እንዳሉትም ይናገራሉ፡፡

   በጳጉሜ 5,1953/54ዓ.ም የዘፈን ግጥም ውድድር ነበር፡፡ በዚህ ወቅት አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ የኔሀሳብ የሚለውን የዘፈን ግጥም በማቅረብ ይወዳደራሉ፡፡ ተወዳድረውም አንደኛ በመውጣት 25 ብር ተሸልመዋል፡፡ በወቅቱ ለኦርኬስትራው ፣ ለድምፃዊው እንዲሁም ለግጥም እና ዜማ ደራሲው አጠቃላይ የተሰጠው ሽልማት 250 ብር ነበር፡፡ ይህ ሲከፋፈል ነው ለእያንዳንዳቸው 25 ብር የደረሳቸው፡፡

  የአርቲስት አስናቀች ወርቁ እና የ (አባባ) ተስፋዬ ሳህሉ የህይወት ታሪክን የተመለከተ መፅሀፍም ፅፈዋል፡፡ በተጨማሪም የብሄራዊ ትያትርን ታሪክ በተመለከተ እና የዘፈን ግጥሞቻቸውን እየፃፉም እንደሆነ አጫውተውኛል፡፡በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በአሁኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ትያትር እስከ 1966ዓ.ም ድረስ በህዝብ ግንኙነት እና የትያትር ክፍል ሀላፊ እንዲሁም ፕሮግራም እና ፕሮዳክሽንን በተጠባባቂነት በመምራት በልዩ ልዩ ሀላፊነት አገልግለዋል፡፡


   በ1994ዓ.ም የኢትዮጵያ ስነ ጥበባት እና መገናኛ ብዙሃን ሽልማት ድርጅት በተውኔት ዘርፍ “የህይወት ዘመን” ተሸላሚ ናቸው፡፡ በዚህም የወርቅ ሜዳሊያ ፣ የክብር ዲፕሎማ እና የ 20,000 ብር ሽልማትን አግኝተዋል፡፡ አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ የሁለት ሴቶች እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ናቸው፡፡

No comments:

Post a Comment