Monday, April 7, 2014

ሁጅዋን በ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የጫማ ኢንዱስትሪ ከተማ ሊገነባ ነው


 
    የቻይናው ሁጅዋን ጫማ ፋብሪካ በአዲስ አበባ ከተማ የኢንዱስትሪ ዞን ሊያቋቁም ነው። የፋብሪካው  ፕሬዝዳንት ዥያንግ ሁሮንግ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሐኖምጋር አዲስ አበባ ውስጥ መክረዋል።
  ዥያንግ ሁሮንግ እንደተናገሩት በአዲስ አበባ ከተማ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለቡ አካባቢ የሚገነባው የኢንዱስትሪ መንደር በዱከም ከተማ በቻይናውያን ከተገነባው ከኢስተርን የኢንዱስትሪ ዞን የገዘፈ ይሆናል። በአሁኑ ወቅት ኩባንያው ከአዲስ አበባ አስተዳደር መሬት ተረክቦ ሌሎች አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያካሄደ ነው፡፡ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ግንባታ ይጀመራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ኢዜአ ዘግቧል።
  ኩባንያው ከዚህ ቀደም በዱከም ከተማ በኢስተርን የኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ባቋቋመው ፋብሪካ 3ሺህ 500 ሰራኞችን ቀጥሮ እንደ ጓንትና ጫማ ያሉ የቆዳ ውጤቶችን ለውጭ ገበያ እያቀረበ ነው ፡፡ አዲሱ የኢንዱስትሪ መንደር ከ30 እስከ 50 ሺ ለሚደርሱ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ከኩባንያው ፕሬዝዳንት ጋር ባደረጉት ውይይት ወደ ስራ ለሚገቡ የውጭ ባለሃብቶች መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። ኩባንያው ለአንቨስትመንቱ 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በጅቷል፡

No comments:

Post a Comment