የአማራን ባህል በጥቅል የመንዝን ባህል ደግሞ በዝርዝር ያጠኑትና በዚህ ስራቸውም “አሜሪካዊው መንዜ'' የሚል ቅጽል ስም ያተረፉት አሜሪካዊው የማህበረሰብ ጥናት ተመራማሪ /Sociologist/ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን በመንዝና በአካባቢው ባና በሰፊው እንደሚለበስ የመንዞችም ብርድልብስ እንደሆነ ጽፈዋል፡፡ ይሄ ብርድ ልብስም ከመንዝ አልፎ ወደሌሎች ቦታዎችም በሰፊው ይሸጥ ነበር፡፡ በወቅቱ የሚከፈቱ አዳሪ ትምህርት ቤቶችም ለተማሪዎቻቸው የሚያለብሱትም ይሄንኑ ባና ነበር፡፡ የአሁኑ አቤቶ ነጋሲ ወረደቃል ትምህርት ቤት የመጀመሪያ አዳሪ ተማሪዎችም ባናን ለሌሊት ልብስነት ይለብሱ እንደነበር የቀድሞ ተማሪዎች ያስታውሳሉ፡፡ በመንዝ ባላባቶች እና ትላልቅ ሰዎች ዘንድ የሚለበሰው በርኖስም ከክብር ልብስነቱ ባለፈ ለብርድ መከላከያነትም ያገለግላል፡፡ ሴቶችም ከበግ ፀጉር የተሰራ መላወሻ የተባለ በጉርድ ቀሚስ አይነት የተሰራ ልብስ ይለብሱ ነበር፡፡
ባና ወይም ዝተት እና በርኖስ የመንዞች ጥንታዊና ባህላዊ ልብስ ነው። በአሁኑ ጊዜ የመንዝ ማማ ፣ የመንዝ ላሎ ፣ የመንዝ ቀያ ፣ የመንዝ ጌራ ምድር ወረዳ እና የግሼ ወረዳ ያሉበት አካባቢ መንዝ በሚለው ጥቅል ስም ይጠራሉ፡፡ መንዞችም የበጎቻቸውን ጸጉር በመቁረጥ ወይም በመሸለት የሚወጣውን ጸጉር በመፍተል«ባና» ወይም«ዝተት» እና በርኖስ በመስፋት ለተለያዩ አገልግሎቶች ማለትም ለብርድ መከላከያ፣ በበዓላት ቦታ፣ በሀዘንና በአደባባይ ቦታ ይለብሱታል፡፡ ወንዶች«ዝተት» ወይም«ባና» እንዲሁም በርኖስ ሲለብሱ ሴቶች ደግሞ ዝተቱን ወይም ባናውን በመሸንሸን ከወገብ በታች እንደ ቀሚስ ይለብሱታል፡፡ ይህም«መላወሻ» ይባላል፡፡
አካባቢው ቀዝቀዝ ስለሚል አብዛኛው ህዝብ ይህን ቅዝቃዜ ለመቋቋም ሲል «ባና» ወይም «ዝተት» የሚባለውን ከበጎች ፀጉር በማሰራት ይለብሳል፡፡ በተመሳሳይ ደግሞ በርኖስ የጥንት አባቶች እና መኳንቶች የክብር እና የሀዘን ልብስ በመሆኑ በበዓላት ፣ በሰርግ እና ለየት ባሉ ስነ-ስርዓት ላይም ይለበሳል፡፡
እነዚህ የመንዝ ጥንታዊና ባህላዊ ልብሶች እንዴት ይዘጋጃሉ?
ባና ወይም ዝተት ለማዘጋጀት በመጀመሪያ በጉ ይታጠባል፡፡ አንድ ቀን ከዋለ በኋላ በማግስቱ ይሸለ ታል/ ይቆረጣል፡፡ ከዚያም ፀጉሩ በግልም ሆነ በቡድን በመሆን በእጅ ይፋታል፡፡ የተፋታውም ፀጉር በደጋን፣ በቅል አንገትና መታፈሪያ ይነደፋል/ይባዘታል/፡፡ ደጋንና ቅል አንገት ስንል ምን ማለት እንደሆነ ግራ አንዳይገባዎት የበግ አንጀት ታልቦ ለሁለት ታጥፎ ይከረራል፡፡ ከዚያም ተወጥሮ ከታሰረ በኋላ እንዲደርቅ ይደረጋል፡፡ ይህ በሶስት ወይም በሁለት ይደረባል፡፡ ከዚህ በኋላ ጅማት ይባላል፡፡ ይህ ጅማት በቆላፋ እንጨት ላይ ተወጥሮ ደጋን የሚባለውን ስም ያገኛል፡፡ከቅል ተክል ከጫፍ ያለው እንቡቶ አይነት ቅርፅ ተቀርፍፎ ይወጣና «ቅል አንገት» የሚል ስያሜ ያገኛል፡፡ «መታረሪያ» የምንለው ደግሞ ቀጭንና ጠንካራ ከወይራ ወይም ከቀጨሞ እንጨት ግማሽ ሜትር ርዝመት ያለው ከእስክርቢቶ ትንሽ ወፈር ያለ ሲሆን አገልግሎቱም ጅማቱን እና ደጋኑን በማያያዝ በቅል አንገቱ በሚወጣው ንዝረት አማካኝነት የሚነደፈውን ፀጉር በአግባቡ እንዲበተንና እንዲለሰልስ ማድረጊያ ነው፡፡ በዚህ መንገድ የተፋታው ፀጉር ይነደፋል፡፡ የተነደፈው ፀጉር በአመልማሎ መልክ እየተጠቀለለ በእንዝርት ይከረራል። ከዚያም ለዚህ በተዘጋጀው ከበድ ያለ እንዝርት አማካኝነት በወፍራሙ ይፈተልና ልቃቂት ይለቀቃል፡፡
በዚህ ሁኔታ ልቃቂቶች ከተጠራቀሙ በኋላ ሁለቱ በአንድ ላይ ይኮባሉ/ይጠቀለላሉ/፡፡ በተዘጋጀዉ እንዝርት አማካኝነት ወደ ቀኝ ተፈትሎ የነበረዉን በተቃራኒዉ ወደ ግራ ይከረራል፡፡ እንደዚህ ከተከረረ በኋላ ልቃቂት ይሆናል፤ የተከረረዉም ልቃቂት ይኮባል/ይጠቀለላል፡፡ በዚህ መንገድ የተደራዉ /የተኮበው ለሸማኔ ይሰጣል፡፡ የተዘጋጀዉ ፈትል በሸማኔ ከተሸመነ በኋላ ሲያልቅ ሽክሽክ የሚባል ስያሜ ያገኛል፡፡ ሸማኔዉም ሲሸምን የተለያዩ ቀለማትን እንዲይዝ ያደርገዋል፡፡
በርኖስ የሚሰራው መጀመሪያ ከጥቁር ሪዝ በግ ፀጉር ብቻ ተመርጦ ልክ እንደ ዝተት ወይም ባና አሰራር ከተዘጋጀ በኋላ ለበርኖስነት በሚያመች መንገድ ተቆርጦ በባህር ፣ አርብና የተለያዩ ቀለማት ባሉት ሀር ለአንገት ማስገቢያ በሚያመች መልኩ ተሰፍቶ ለአደባባይ፣ ለሀዘን ፣ ለደስታ እና ሙግት ጊዜ ይለበሳል፡፡ በሀዘን ጊዜ ባህር አርቡ ወደ ላይ ተገልብጦ ሲለበስ በግራ ትክሻ ላይ እንደሻኛ ቆሞ የሚታየው ቅርፅ ወደ ፊት እንዲተኛ ይደረጋል፡፡ በደስታ፣ በአደባባይና በሙግት የአለባበስ ጊዜ ወደ ፊት ተኝቶ የነበረው የበርኖስ ሾጣጣ ክፍል በትክሻ ቅርፅ እንዲቆም ይደረጋል፡፡ አንዳንዴም ከነጭ አቡጀዴ እጅ ጠባብ ፣ ጠባብ ሱሪ እና ጭራ ጋር አብሮ የሚለበስበት ስርዓት አለው፡፡
(ዘሪሁን ተፈራ ከሰሜን ሸዋ ዞን - መሃል ሜዳ ከተማ ኮሙኒኬሽን ፅህፈት ቤት)