|
ምስጋና ለአፍሪካ ቫኬሽን ክለብ |
ከዚህ ቀጥዬ ስለ እኛ እናገራለሁ፡፡ እኛ ማነን? ……ተከተሉኝማ…!
ዕለተ ቅዳሜ መጋቢት ዘጠኝ 2009 ዓ.ም እኔና ባልደረቦቼ ለጉዞ ተነስተናል፡፡ ጉዞ ወደ አፍሪካ ቫኬሽን - ላንጋኖ፡፡ ይህ ጉዟችን የተለመደው ዓይነት - የሥራ ጉዞ አይደለም፡፡ ይልቁንም በህግና ደምብ ፣ በአለቃና ምንዝር ፣ የታጠረ አብርሆትን (formal communication) ሰብረን ሰብአዊ ቤተሰብን የምንፈጥርበት እንጂ፡፡ ማህበራዊ ቁርኝታችንን ወደ ላቀ ከፍታ የምናሳድግበት ፤ እንደ ሰራተኛና አለቃ ብቻ ሳይሆን እንደ እህት እንደ ወንድም፣ እንደ ታናሽ እንደ ታላቅ እኔ ላንተ አንተ ለኔ የምንባባልበት ልዩ የፍቅር ጉዞ ነው፡፡ ዓመት ሙሉ በሥራ የተወጠረ አዕምሮ ዘና የሚልበት ወይም ራሳችንን (Refresh)የምናረግበት ነው - ዓመታዊው የጉዞና የመዘናኛ ዝግጅታችን፡፡
እናማ በዚህ መሰረት ነው የዘንድሮው ጉዟችን ፡፡ ለዚህ ጉዞ ከ 20 የምንበልጥ ጋዜጠኞች በማለዳው ተገኝተናል፡፡ ጉዞ የሚጠይቀውን ጓዝም ሸክፈናል፡፡ የአንዳንዱ ሻንጣ አያይዝ ግን ላንጋኖ ሊዝናና ነው ብሎ ከማሰብ ይልቅ ላንጋኖ ቤት ሊቀይር ነው ብሎ ማሰብ የሚቀል ይመስለኛል፡፡ (ያዝ እንግዲህ)፡፡
አሁን ደግሞ ጥቂት ስለ መኪና ውስጥ አቀማመጣችን “ከፊል እውነት” የተቀላቀለበት መረጃ እሰጣለሁ፡፡
ፊት ወንበር - - - -ከፍተኛ አመራር
መሀል ወንበር - - -መካከለኛ አመራር
ኋላ ወንበር - - - ሪፖርተር
ከመጨረሻ መጨረሻ - - - ተሰናባች ጋዜጠኛ
እንግዲህ በስልጣን ተዋረዴ መሰረት ከኋላ ወንበሬ ላይ ተሰይሜያለሁ፡፡ ልብ በል በተሰናባቹ ጋዜጠኛ ቦታ አላልኩም፡፡ ሪፖርተር በሚለው ቦታ ማለቴ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ ተሰናባቹ ጋዜጠኛ ያለኩት አንድ በቅርቡ ከኛ ጋ የለቀቀ - በፍቅር ብዛት ከኛ ጋር እንዲጓዝ ተጋብዞ የመጣ አንድ ጋዜጠኛ ስላለ ነው፡፡)
ከጋዜጠኛ ጋር ስትጓዝ ሁለት ነገሮች የተከለከሉ መሆናቸውን ባታምንም ታምናለህ፡፡ አቀርቅሮ ማሰብና ማንቀላፋት፡፡ በምትኩ - ከየማዕዘኑ በሚወረወሩ የቀልድ ጠጠሮች አናትህ እየተወቀረ ፈንዲሻ መስለህ መጓዝን አምነህ ትቀበላለህ፡፡ የሳቅ ነገር ከተነሳ የገረሙኝን ሁለት ነገሮች ልናገር፡፡
አንድ - ያንዳንዱ ሳቅ ከሰማይ መብረቅ የሚያወርድ ይመስል የሆነ ግግግገግግ የሚል ማስገምገም ያለው መሆኑ (ያዝ - እዚህ ውስጥ የምትካተት ራስህን ቁጠር)
ሁለት - አንዳንዱ ደሞ ሳቁ በአዋጅ የተከለከለ ይመስል ከንፈሩን ገጥሞ ሆዱን እንደ ፎጣ የሚጨምቅ ነው፡፡ (እዝችጋ እኔን አንድ በል)
ከመኪናችን የኋላ ጥግ (corner) ተቀምጫለሁ፡፡ አቀማመጤ ለሌሎችና ለካሜራ እንዳልታይ ቢያረገኝም ሁሉንም አጮልቄ እንድሾፍ ግን ጠቅሞኛል፡፡ የሰርግ አስፈፃሚ ከመሰለው እስከ ባለሻንጣው - - - ለቀልዶች ሁሉ ሀሀሀሀ የሚል ሳቅ ከሚያዋጣው እስከ ሳትናገር ሄዳ ሳትናገር እስከተመለሰችው፡፡ ሁሉንም አያለሁ፡፡ (እነዚህ እነማናቸው እንደማትሉኝ ተስፋ አለኝ)፡፡
ጉዟችን ሞቅ ያለ ነበር፡፡ የሙቀቱ ምክንያት ግን ፀሐይዋ ብቻ አትመስለኝም፡፡ እንደኔ እንደኔ የስንታሁ እጅም ነበረበት፡፡ ምክንያቱም ያን ሁሉ የሳቅ ናዳ እያንከባለለ ባይጭንብን በሳቅ ሙቀት ተንጣጥተን መች ፈንዲሻ እንሆን ነበር፡፡ እንደውም አንዳዶች ለብዙ ሀይላንድ ውሃ መጠጣት አደጋ አጋልጦናል ብለዋል አሉ፡፡ ( ያዝ - ስንትሽ ቺርስ )
አሁን ደግሞ ከሳቅ ምንጮች ጥቂቶቹን እጠቅሳለሁ - - -ግን እኛ ብቻ እንዲገባን አድርጌ ነው ( ምን ታረጉታላችሁ)
ወርደን እንነጋገር - - - - - - (ስንቴ)
ጨምላቃ - - - - - - - - - (ስንቴ Vs ታዴ)
እምቡጥ - - - - - - - - -- -(ታዴ)
Yahoo.com - - - - - - - - - (አቤል)
ከፀሐይ ላይ ተነስ - - - - - - - (ሚሊ)
ፐብሊክ ባስ እየመጣ ነው - - - -(ጀሙ)
ሌሎችም - - - -
አፍሪካ ቫኬሽን - ላንጋኖ ስንደርስ ጊዜው ወደ መምሸቱ ነበር፡፡ ቢሆንም ግቢውን ዞረን ለማድነቅ ፣ ኳስ ለመጫወት ፣ የላንጋኖን ሐይቅ በምትጠልቀዋ ጀምበር ለማየት የሚያስችል ሰዓት አላጣንም፡፡
ከምሽቱ ዝግጅታችን እስከ እሁድ ረፋድ የነበረን ቆይታ በርግጥም አስደሳች ነበር ብል አልተጋነነም፡፡ የጀልባው ሽር ሽር ፣ ፈረስ መቀመጡ ፣ ዋናው - - - - በሥራ የታጨቀ መንፈሳችንን ማደስ ብቻ ሳይሆን - - - የማንረሳው ትዝታም የጣለብን ይመስለኛል፡፡
ከሳቅ ከጨዋታው ደምቆ የሚነበብ - መተሳሰብን ፣ ይበልጥ መቀራረብን ፣ እንደዋዛ የተነገሩ ነገር ግን የህይወት ስንቅ የሆኑ ልምዶችን ተለዋውጠናል፡፡ በኔ ዐይን ይህ ጉዞ ገንዘብ የማይገዛውን ውድ የመንፈስ ሀብት የሸመትንበት ነው እላለሁ፡፡ እናንተስ - - - -???