በሙዚቃው አለም ከ3ዐ አመት በላይ አሣልፏል፡፡ በአንድ ወቅት ለአንድ ሠው ደብዳቤ ለማድረስ ሀረር ይሄዳል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በሀረር ፖሊስ ምስራቅ ሰጎን ኦርኬስትራ ዳንስና ሙዚቃ ተፈትኖ ገና በ13 አመቱ አካባቢ የኪነ ጥበቡን አለም ተቀላቀለ፡፡ በሀረር ፖሊስ ለ3 ዓመታት ያህል ከሠራ በኋላም አዲስ አበባ ተመልሶ የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ /የአሁኑ ብሄራዊ ትያትር/ ቤት ሰው ሊጠይቅ ይሄዳል ፡፡ እዚያም በዚሁ አጋጣሚ በትያትር ቤቱ “ዳዊት ባንድ” ውስጥ ተቀጥሮ ለትንሽ ጊዜ አገልግሏል፡፡ በዚህ ያላቆመው ይህ ሰው ፖሊስ ፣ ምድር ጦር እና ሀገር ፍቅር ኦርኬስትራዎች ውስጥም በተለያዩ ጊዜያት ገብቶ ሠርቷል፡፡ ድምፃዊ ፣ግጥም እና ዜማ ደራሲ ቶማስ አበበ፡፡
በተፈጥሮው የዘፋኝነት ተሰጥኦ ያለው ቶማስ አበበ በልጅነቱ የጥላሁን ገሰሰ፣ በተለይም የመስፍን ሀይሌ እና ሌሎች ድምፃውያን ስራዎችን ይጫወት ነበር፡፡ ረዘም ያለውን ጊዜ በምድር ጦር ያሳለፈው ቶማስ አበበ ለራሱ ከደረሣቸው ግጥምና ዜማዎች ባሻገር ለአባይ በለጠ "ሙናዬ" እና ለታምራት ሞላ "ሙዚቃ " የተሰኙትን ድርሰቶች አዘጋጅቷል፡፡ በምድር ጦር እስከ1969ዓ.ም ድረስ በድምፃዊነት እና በግጥም እና ዜማ ደራሲነት ቆይቷል፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበርን በስራ አስፈፃሚነት እና በዋና ፀሃፊነት፤ ሀገር ፍቅርን ደግሞ በህዝብ ግንኙነት ባለሙያነት አገልግሏል፡፡
ድምፃዊ ፣ግጥምና ዜማ ደራሲ ቶማስ አበበ በደርግ ዘመነ መንግስት የሳንሱር ቀንጥጫን ቀመሷል፡፡ ቤተ መንግስት ቀርቦ ፣ ማዕከላዊን ጎብኝቶ በውህኒ ቤት ለሁለት አመት ከግማሽ በእስር ቆይቷል፡፡ እዚሁ መዲናችን አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገው ቶማስ አበበ በግጥም እና ዜማ ደርሰቱ ፤ ራሱም ሆነ ሌሎች በተጫወቱት ስራዎቹ ማህበራዊ ሂሶችን እና ትችቶችን በመስጠት፣ ስለፍቅርም ሆነ ስለ ፖለቲካ እና ስለ ሀገር ጉዳዮች አንስቷል፡፡ እሱ ከተጫወታቸው ስራዎች መካከል “አበቦች ሲያብቡ” ፣ “የጋራ ኑሮ ነው” ፣ “ጊዜው ለጨነቀው” ፣ “ቃልሽ ይገባኛል” ፣ “መስለው እየታዪት” ፣ “ያለምንም ደም እንከኗ ይውደም” እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡