Sunday, January 4, 2015

ሶስተኛው ተንጠልጣይ ድልድይ በአባይ ወንዝ ላይ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።


   በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ዳስራ ማርያም በተሰኘ የገጠር ቀበሌ የተሰራዉ ድልድይ 108 ሜትር ርዝመት እና 1ነጥብ 6 ሜትር ስፋት አለዉ፡፡ ተንጠልጣይ ድልድዩ በአንድ ጊዜ 400 ኪሎ ግራም ክብደት የመሸከም አቅም አለዉ፡፡

   በሃገሪቱ ብቸኛዉ የተንጠልጣይ ድልድይ በመስራት በሚታወቀው ሄልቬታስ ሲዊዝ ኢንተርኮኦፕሬሽን በተሰኘ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት የተሰራም ነው፡፡ በድርጅቱ የተንጠልጣይ ድልድዮች ፕሮግራም ሃላፊ አቶ አለም ሹምዬ፥ ግንባታዉ ሰባት ወራት መፍጀቱንና ሶስት ሚሊየን ብር የሚጠጋ ወጭ እንደወጣበት ተናግረዋል፡፡

  የግንባታ ወጭዉንም 40 በመቶ ሄልቬታስ 60 በመቶዉን ደግሞ ከዓለም ባንክ የግብርና እድገት ፕሮግራም በተገኘ ገንዘብ ተሸፍኗል፡፡ ታንኳ በር ተንጠልጣይ ድልድይ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የዳስራ ማርያም እና የጭስ አባይ እንዲሁም በደቡብ ጎንደር ዞን ደግሞ የደራ ወረዳ የተወሰኑ የገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደሮችን የዘመናት ጥያቄን ፈቷል፡፡
  
  ቀደም ሲል በጠባብ ታንኳ ሰዉ፣ እንስሳትና ቁሳቁስ በአንድ ላይ 100 ሜትር የሚረዝመዉን የአባይን ወንዝ መሻገር ይጠበቅባቸዉ ነበር፡፡ ታንኳ እየተገለበጠ የሰዉና የእንስሳት ህይወት ሲያልፍ ቆይቶል፡፡ ድልድዩ ሰዉ እና እንስሳትን ባንዴ እያሻገረ በአግባቡና በጥንቃቄ ከተያዘ 40 እስከ 50 አመት አገልግሎት መስጠት እንደሚችል ባለሙያዎች ገልፀዋል፡፡

  የአካባቢዉ አርሶ አደሮችም የዘመናት ጥያቄያቸው በመመለሱ ደስተኞች ሆነዋል፡፡ አቶ አለም ሹምዬ እንደገለፁት የተንጠልጣይ ድልድዮች ስራ ወደ ሃገሪቱ ከገባ ስምንት አመታትን ማስቆጠሩንና እስካ አሁንም በአምስት ክልሎች 60 በላይ ተንጠልጣይ ድልድዩች ተሰርተዉ ለአገልግሎት በቅተዋል፡፡
                                ምንጭ፦ የአማራ መገናኛ ብዙሃን    

No comments:

Post a Comment