በኢትዮጵያ አመታትን ጠብቀው
የሚከበሩ ሀይማኖታዊ በዓላት ከእምነት ፋይዳቸው ባለፈ በውስጣቸው በያዙት መስህባዊ ተፈጥሮ ምክንያት በርካት የውጪ እና የሀገር
ውስጥ ጎብኚዎችን ይስባሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ደግሞ የጥምቀት በዓል ነው፡፡ የስነ መለኮት ምሁራን ጥምቀት ለሚለው ቃል መነከር
፣ መታጠብ ፣ መረጨት እና እና የመሳሰሉትን ትርጓሜዎች ይሰጡታል፡፡የጥምቀት ዋዜማ ከተራ ይባላል፡፡
የከተራ እለት/ ጥር 10 ማለት ነው/ ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ በሚሰማው የደውል ጥሪ ታቦታቱ ፤ የተለያዩ ህብረ ቀለማት ያላቸው አልባሳት
በለበሱ ህዝበ ክርስቲያን ታጅበው ጉዞአቸውን ወደ ጥምቀተ ባህር ያደርጋሉ፡፡
በሀገራችን ታቦት ተሸክሞ ፣ ወንዝ ወርዶ የክርስቶስን
በዓለ ጥምቀት ማክበር የተጀመረው በአፄ ገብረመስቀል ዘመነ መንግስት እንደሆነ ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ ይህንን ታሪክ በመከተል አፄ
ነዖድም(1486 - 1500 ዓ.ም) ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ሁሉ ታቦተ ህጉን ወደ ጥምቀተ - ባህሩ
በሚወርድበት ጊዜ እና ከጥምቀተ - ባህሩ ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ አጅቦ መውረድ እና መመለስ እንዳለበት አዋጅ አስረግረው ነበር፡፡ በአዋጁ መሰረትም
ህዝቡ በየአመቱ ታቦተ ህጉን በማጀብ ወንዶች በጭፈራ እና በሆታ፣ ሴቶች ደግሞ በእልልታ ሲያከብሩ ኖረዋል ፤ አሁንም እያከበሩት
ይገኛል፡፡
በከተራው ዕለት ድንኳን ተተክሎ
፣ ዳሱ ተጥሎ እና ውኃው ተከትሮ ሁሉም ነገር ከተስተካከለ በኋላ፤ ታቦተ ህጉ የሚንቀሳቀስበት ሰዓት ሲደርስ የየቤተ መቅደሱ ታቦታት
በወርቅ እና በብር መጎናፀፊያ እየተሸፈኑ ፤ በተለያየ ህብር በተሸለሙ የክህነተ አልባሳት በደመቁ ካህናት እና የመፆር መስቀል በያዙ
ዲያቆናት ከብረው፣ ከቤተ መቅደስ ወደ አብሕርት/ መጥማቃት/ ለመሄድ ሲነሱ መላው አብያተ ክርስቲያናት የደውል ድምፅ ያሰማሉ፡፡
ምዕመናንም ከልጅ እስከ አዋቂ በአፀደ ቤተ ክርስቲያን እና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ እንደሚባለው
ያማረ ልብሳቸውን ለብሰው በዓሉን ያደምቃሉ፡፡
ታቦታት
ከቤተ መቅደሳቸው ወጥተው በህዘበ - ክርስቲያኑ ታጅበው ማደሪያ ቦታቸው ይደርሳሉ፡፡ በዚያን ጊዜ ዳቆናት እና
ቀሳውስት በባህረ ጥምቀቱ ዙሪያ ሆነው ከብር የተሰሩ መቋሚያ እና ፅናፅን እንዲሁም ከበሮ ይዘው በነጫጭ እና በወርቅ ቀለም
ባሸበረቁ እጥፍ ድርብ አልባሳት አምረው እና ተውበው፤የክርስቶስን የጥምቀት ታሪክ የሚያወሱ ወረብ እና መዝሙሮችን ጣዕም ባለው
ዜማ ያቀርባሉ፡፡ ሌሊቱን ስብሀተ - እግዚአብሔር ሲደርስ አድሮ ከዚያም ስርዓተ ቅዳሴው ይፈፀማል፡፡ በወንዙ /በግድቡ/ ዳር
ፀሎተ- አኩቴት ተደርሶ 4ቱ ወንጌላት ከተነበቡ በኋላ ባህረ
ጥምቀቱ በብፁዓን አባቶች ተባርኮ ለተሰበሰበው ህዝበ - ክርስቲያን ይረጫል፡፡ ለዚህ በዓል ህዝበ ክርስቲያኑ ልዩ ትኩረት
ይሰጠዋል፡፡ ምክንያቱም በዓሉ እየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ የተጠመቀበትን ተምሳሌት በማሰብ ስለሚከበር፡፡
የጥምቀት በዓል ሀይማኖታዊ ስርዓቱን ከባህላዊ ወግ እና
ስርዓት ጋር አጣምሮ የያዠ ነው፡፡ በዚህም በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ህብረ - ቀለማዊ የሆነ ጨዋታቸውን በልዩ ልዩ ቋንቋዎች
ያቀርባሉ፡፡ በዓሉን ለማክበር ወደ ጥምቀተ ባህር የሚሄዱ ሰዎች ከበዓሉ በፊት ተዋወቁም አልተዋወቁም በዚያን ዕለት በጋራ ሆነው
ጥዑም ዜማዎችን ያንቆረቁራሉ፡፡ ይህ ዕለት ማንም ሰው ሳያፍር እና ሳይሸማቀቅ የውስጡን የሚገልፅበት እና በጋራ የሚጫወትበት
ዕለት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም በጓደኝነት ለመተጫጨት ለሚፈልጉ ወጣቶች መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡ ህዝበ - ክርስቲያኑ
ይህንን በዓል ዘር እና ቀለም ሳይለዩ በአንድነት ያከብሩታል፡፡ በመሆኑም በዓሉ ህዝብን ያቀራርባል፤ የመረዳዳት ባህልንም
ያሳድጋል፡፡
የጥምቀት በዓልን ለማክበር የተለያዩ ሀገር ዜጎች ፣ ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮች እና ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም የቤተክርስቲያን አባቶች እና ምዕመናን ይታደማሉ፡፡ ይህ በዓል በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚከበር ቢሆንም በተለይ በአፄ ፋሲል መዋኛ ፣ በላልይበላ ፣ በመቀሌ ፣ በአክሱም እና በአዲስ አበባ ከተሞች በተዘጋጀላቸው የክብር ቦታ ህዝበ - ክርስቲያኑ ከውጪ ከሚመጡ ቱሪስቶች ጋር በዓሉን
በደመቀ ሁኔታ ያከብሩታል፡፡
ታዲያ በዚህ በዓል ላይ ያስገረማቸውን ነገር በማስታወሻነት ለማስቀመጥ የተለያዩ ሰዎች የፎቶ እና የቪዲዮ ካሜራዎቻቸውን ደግነው
እያነሱ እና እየቀረፁ ያስቀራሉ፡፡
በመጨረሻም በሀገራችን የሚከበሩ ሀይማኖታዊ በዓላት የመረዳዳት እና የመደጋገፍ ባህልን ያዳብራሉ፡፡
ከዚህም ባሻገር አገሪቱ ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው ተጠቃሚ እንድትሆን ያስችሏታል፡፡ ስለዚህ ተገቢውን ትኩረት ልንሰጣቸው ይገባል፡፡