Sunday, September 22, 2013

ኢትዮጵያዊቷ ብሩክታይት ደገፋ ለ12 ዓመታት የቆየውን የሲድኒን ማራቶን ሪከርድ በመስበር አሸነፈች

  ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ብሩክታይት ደገፋ በሲድኒ 12 ዓመታት ሳይሰበር የቆየውን የሴቶች የማራቶን ክብረወሰን በመስበር  አሸነፈች።

   በዛሬው እለት በሲድኒ የተካሄደው ይህ 42.2 ኪሎ ሜትር ውድድር ቀደም ሲል .. 2001 በአውስትራሊያዊቷ ክሪሻና ስታንቶን  2 ሰዓት 38 ደቂቃ 11 ሰከድ ተይዞ የነበረ ሲሆን ብሩክታይት 2 ሰዓት 32 ደቂቃ 45 ሰከንድ በሆነ ግዜ ነውየቦታውን ክብረወሰን  በማሻሻል ጭምር ማሸነፍ የቻለችው።
  በሌላ በኩል የሴቶች ግማሽ ማራቶኑን  ውድድር ላውራ ጀምስ የተባለችው አውስትራሊያዊት 1 ሰዓት 18 ደቂቃ 36 ሰከንድ በመግባት በአንደኛነት አጠናቃለች  በተመሳሳይ በተካሄደው  የወንዶች የማራቶን የሩጫ ውድድር ኬንያዊው ዊሊ ኪቦር ድል የቀናው ሲሆን ኪቦር 2 ሰዓት 13 ደቂቃ 48 ሰከንድ አንደኛ ሆኖ ጨርሷል።  
                                    ምንጭ:  9news

Friday, September 13, 2013

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ ተባለ

በአፍሪካ ፈጣን እድገት እያስመዘገበ ያለው የኢትዮጰያ አየር መንገድ ምርጥ የአፍሪካ አየር መንገድ በመባል የመንገደኞች ምርጫ ሽልማት አግኝቷል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሽልማቱን 3/13/2005 / በካሊፎርንያ የተቀበለ ሲሆን ሽልማቱም መቀመጫውን አሜሪካ ባደረገ አየርላየን ፓሰንጀር ኤክስፕሬንስ ማህበር የተዘጋጀ ነው፡፡የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወልደ ገ/ማሪያም እናዳሉት ሽልማቱ በመላው አለም ለሚገኙ ጠንካራ የፓን አፍሪካ አየር መንገድ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞችም ነው ብለዋል፡፡

Tuesday, September 10, 2013

ከኢትዮጵያ በማደጎ የወሰዷትን ልጅ ለሞት የዳረጉት አሜሪካውያን ቤተሰቦቿ ጥፋተኛ ተባሉ

        ኢትዮጵያዊቷን ሐና ዊሊያምስን በማደጎ ወደ አሜሪካ የወሰዳት ላሪ ዊሊያምስ በቀረበበት ሐናን የመግደል ክስ ጥፋተኛ ተባለ። በ2008 ከኢትዮጵያ በማደጎነት የተወሰደችው ሐና ከፍተኛ ቅዝቃዜ ቦታ ላይ ተቆልፎባት  የደረሰባት የጤና መታወክ ለሞት ሊዳርጋት እንደቻለ ፍርድ ቤቱ አረጋግጧል።

  ከጤና መታወክም ባለፈ ለቀናት ያለምግብ ከምድር በታች ባለ ቤት ውስጥ ተዘግቶባት  መቆየቷ ለሞቷ አንድ ምክንያት እንደሆነም ለፍርድ ቤቱ   አቃቤ ህግ ያቀረበው ማስረጃ ያመለክታል።በዚህም መነሻነት አቃቤ ህግ ለፍርድ ቤቱ የ13 ዓመቷ ሐና ዊሊያምስን ተከሳሾቹ  አባቷ ላሪና ዊሊያምስና እናቷ ካሪ ዊሊያምስ  ከኢትዮጵያ በማደጎ በ2008 ያመጧት መሆኑን በማስረዳት ሰው በመግደል ክስ መስርቶባቸው ነበር። ሐና በ2011 ግንቦት ወር ላይ  ቤተሰቦቿ መኖሪያ ጀርባ ባለ ምድር ቤት ለቀናት ተዘግቶባት መቆየቷና የቤቱ የቅዝቃዜ ምጣኔ 4 ዲግሪ ሴልሺየስ መሆኑ ለሞት ሊዳርጋት ችሏል።

ላሪ ዊልያምስና ካሪ ዊልያምስ ከሐና ሞት ከአራት ወራት በኋላ በቁጥጥር ስር ውለው ክሳቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ሲሆን ፥ ፍርድ ቤቱም ሰው በመግደል ወንጀል ጥፋተኛ ብሏቸዋል። በተጨማሪ ተከሳሾቹ  በማደጎ የወሰዱት የ10 ዓመቱ የሐና ወንድም በተመሳሳይ የመደብደብ ፣ የርሃብና በምድር ቤት ተቆልፎበት እንደነበረም መርማሪዎች ደርሰውበታል። ለዚህም ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹን ህጻናት ላይ ጥቃት በማድረስና በአግባቡ ባለመንከባከብ ጥፋተኛ ብሏቸዋል። በቀጣዩ ወር የጥፋተኝነት ቅጣት ውሳኔ ፍርድ ቤት እንደሚያሳልፍባቸው ቀጠሮ የያዘ ሲሆን ፥ በተከሰሱበት የዋሽንግተን ግዛት ህግ መሰረት እስከ እድሜ ልክ እስራት ድረስ ሊቀጡ ይችላሉ።

                                                                                           ምንጭ: አሶሽየትድ ፕሬስ

Thursday, September 5, 2013

ከጅቡቲ ድሬዳዋ ያለው የባቡር መስመር አገልግሎት መስጠት ጀመረ

 
 የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር አካል የሆነው ከጅቡቲ እስከ ድሬዳዋ ያለው የባቡር መስመር እድሳቱ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።  ከ1890 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ይኼው የባቡር መስመር በደረሰበት ብልሽት ምክንያት መቋረጡ በድሬዳዋ ከተማ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉን ነው የከተማዋ ነዋሪዎች የሚናገሩት።

    የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ አየለ ወንደወሰንም በነዋሪዎቹ ሀሳብ ይስማማሉ ። ይህ የሆነውም ባለ አንድ ሜትር የሀዲድ ስፋት እና ከድሬዳዋ ጅቡቲ ድረሰ የ308 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የባቡር መስመር በማርጀቱ ምክናይት ጥገና እንዲደረግለት መቋረጡን በማንሳት። እሳቸው እንደሚሉት በኢትዮጵያ በኩል ካለው 208 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ውስጥ ፥ ጥገና የሚያስፈልገውን 100 ኪሎ ሜትር ለመጠገን ስራውን የወሰደው የጣሊያን ድርጅት 23 ኪሎ ሜትሩን ብቻ ጠግኖ ስራውን አቁሞ ነበር ። ይህ ሁኔታም በሶስት አመት ውስጥ እንዲጠናቀቅ የታቀደውን እድሳት በስድስት አመት ውስጥ እንዲጠናቀቅ ማድረጉንም ያስረዳሉ።

     መንግስት ጉዳዩን እያጣራው ቢሆንም የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት ግን በራሱ አቅም ቀሪውን የባቡር ሀዲድ በመጠገን አሁን ላይ ስራውን እንዲጀምር ማድረጉንም ተናግረዋል።አገልግሎቱም ሀምሌ ወር አጋማሽ ላይ በሙከራ ከተጀመረ በኋላ ከሀምሌ 23 2005 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሙሉ ስራው በመግባት ከድሬዳዋ እስከ ጅቡቲ በሳምንት ሶስት ግዜ መንገደኞችን የማጓጓዝ ስራው እየተካሄደ ይገኛል ። በተለይ ወቅቱ የጅቡቲ ነዋሪዎች በሙቀት ምክንያት ወደ ድሬዳዋ የሚመጡበት በመሆኑ የአገልግሎቱ መጀመር ለከተማዋ እንቅስቃሴ መነቃቃት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ነው የሚሉት ሃላፊው ። እስከ አሁንም በኢትዮጵያ በኩል ከ4 ሺህ 800 በላይ መንገደኞች ማጓጓዝ የተቻለ ሲሆን ፥ የድሬዳዋ ነዋሪዎችም ከጆሯቸው ርቆ የነበረውን የባቡር ጡሩምባ በመስማታቸውና በአገልግሎቱ መጀመር መደሰታቸውን ተናግረዋል።


      አቶ አየለ እንደሚሉት ድርጅቱ በቅርቡም የጭነት ትራንስፖርት ለመጀመር አስፈላጊው ዝግጅት አድርጓል ። አሁን ያለው ባቡር አራት ተሳቢዎችን የሚይዝ ሲሆን በሂደት ይህን ከፍ በማድረግ የሎጂስቲክ አገልግሎትን ለመጀመር ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ስምምነት መፈጸማቸውንም ነው የተናገሩት። ቀሪው ከድሬዳዋ አእስከ አዲስ አበባ ያለው መስመር ፥ በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አማካኝነት እየተካሄደ ባለው የባቡር መስመር ዝርጋታ የሚገናኝ ይሆናል ።

Monday, September 2, 2013

በሞሪሺየሱ ውድድር የኢትዮጵያ ታዳጊ አትሌቲክስ ቡድን 3ኛ በመሆን አጠናቀቀ


በሞሪሺየስ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው 11ኛው የአፍሪካ ታዳጊ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ትናንት ተጠናቀ። በውድድሩ 36 ሃገራት ሲካፈሉ ፥ ከእነዚህ ውስጥ 26 ሃገራት በሜዳልያ ሰንጠረዥ ውስጥ ገብተዋል። ውድድሩን ናይጀሪያ 9 የወርቅ ፣ 7 የብርና 8 የነሃስ በድምሩ 24 ሜዳልያዎችን በማግኘት በበላይነት ስታጠናቅቅ ፥ ደቡብ አፍሪካ ደግሞ 7 የወርቅ ፣ 9 የብርና 8 የነሃስ በድምሩ በ24 ሜዳልያዎች ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።


  ኢትዮጵያ 7 የወርቅ ፣ 7 የብርና 8 የነሃስ በድምሩ 22 ሜዳልያዎችን በማግኘት ውድድሩን 3ኛ በመሆን አጠናቃለች። ኢትዮጵያ በ2011 በተካሄደ ተመሳሳይ ውድድር  17 ሜዳልያዎችን ያስመዘገበች ሲሆን ፥ የዘንድሮው ውድድር የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት ነው። የናይጀሪያ እና የጋና መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ በመካከለኛ ርቀት ያስመዘገብችው ውጤት አበረታች መሆኑን ዘግበዋል።

                                                                                                             ምንጭ ፡-    ኤፍ ቢ ሲ