Thursday, February 2, 2023

የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ሴት ጋዜጠኛ ወይዘሮ ሮማነወርቅ ካሣሁን

የታላላቅ ስራዎች ባለቤት ከሆኑ ሴቶች መካከል አንዷ የሆኑት የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ሴት ጋዜጠኛ ወይዘሮ ሮማነወርቅ ካሣሁን በጋዜጠኝነት፣ በደራሲነትና በጸሐፌ ተውኔትነት ልዩ ልዩ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ሴት ጋዜጠኛ ወይዘሮ ሮማነወርቅ ካሣሁን ከአባታቸው ከአቶ ካሣሁን እንግዳሸት እና ከእናታቸው ከወይዘሮ አለሙሽ ዓለም በ1914 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወለዱ፡፡ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም ቅድሥት ሥላሴ ቤተ-ክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብተው የቤተ-ክርስቲያን ትምህርት በመማር ዳዊት ደገሙ፡፡ ከዚያም ስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት በመግባት በጊዜው ይሰጥ የነበረውን ዘመናዊ ትምህርት ተማሩ፡፡ በትምህርት ቤት ቆይታቸውም የወቅቱን “ሴት ለትምህርት አልተፃፈችም” የሚለውን ልማድ በጥረታቸውና በትጋታቸው በመቋቋም በትምህርት ቤት ቆይታቸው የአንደኛነት ደረጃን በመያዝ በአውሮፓውያን አስተማሪዎቻቸው ይሸለሙ ነበር፡፡ በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ይማሩ በነበረበት ወቅትም ከአውሮፓውያን መምህራን ያገኙት ዘመናዊ ትምህርት ከተፈጥሮ ችሎታቸው ጋር ተደምሮ በጥናትና ንባብ ያዳበሩትን እውቀታቸውን ወደአደባባይ ማውጣት ስለፈለጉ በጥር ወር 1939 ዓ.ም በወቅቱ “የማስታወቂያና ፕሮፖጋንዳ ሚኒስቴር” ተብሎ ይጠራ በነበረው መስሪያ ቤት የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ በመሆን ተቀጠሩ፡፡
በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ባገለገሉባቸው ጊዜያት በሬዲዮ ዜና አጠናቃሪነት፣ በዜና አንባቢነት፣ በሴቶች ፕሮግራም አዘጋጅነት ሰርተዋል፡፡ በተለይ “ለወይዛዝርት” የተባለውና በሳምንት ሁለት ጊዜ በኢትዮጵያ ሬዲዮ የሚቀርበው ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ ነበሩ፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ በትያትርና በውይይት መልክ የሚያቀርቧቸው ትምህርታዊ መሰናዶዎች ስለ ቤት ባልትና፣ ስለ ልጅ አስተዳደግና ስለ መልካም ቤተሰብ ኑሮ ያወሱ ነበርና በአድማጮች ዘንድ “እውነትም ሮማነወርቅ” አሰኝቷቸዋል፡፡ በዚሁ መስሪያ ቤት ውስጥ አንድም ቀን “ሰለቸኝ” ሳይሉ በየጊዜው ለአድማጭ አዲስ ነገር ይዞ በመቅረብ ለ25 ዓመታት ያህል ለሙያቸው በመታመን ያገለገሉት ጋዜጠኛ ሮማነወርቅ፣ ለሴቶች ብቻ ሳይሆን ለወንዶችም (በተለይ ደግሞ ለጋዜጠኞች) አርዓያ መሆን ችለዋል፡፡ ይህም ከፍተኛ የሆነ ተወዳጅነትንና አድናቆትን አስገኝቶላቸዋል፡፡ ወ/ሮ ሮማነወርቅ ካሣሁን በህይወት ዘመናቸው ከሚወዱት የጋዜጠኝነት ሙያ በተጨማሪ ደራሲም ናቸው፡፡ ወይዘሮ ሮማንወርቅ ካሣሁን የመጀመሪያ መጽሐፋቸውን “ትዳር በዘዴ” በ1942 ዓ.ም ለእትመት አብቅተዋል። መጽሐፉ የገጠሩንና የከተማውን ትዳርና ኑሮ የሚያነፃፅር ሲሆን በውስጡም በገጠር ያለውን የሕይወት ውጣ ውረድ ዘርዝሮ ያቀረበ ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ በ1943 ዓ.ም ሁለተኛ መጽሐፋቸውን “ማህቶተ ጥበብ” መፅሐፍ በትያትር መልክ በማዘጋጀት ለህትመት አበቁ፡፡ መፅሃፉ በወቅቱ ሕይወታቸው ስላለፈው ስለ ልዕልት ፀሐይ ኃይለሥላሴ ሕይወት የሚያወሳ ነው፡፡ በ1948 ዓ.ም ሦስተኛ መጽሐፋቸውንም ለህትመት አብቅተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ወይዘሮ ሮማንወርቅ ጽሁፎቻቸውን በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ በማሳተም በሕትመት መገናኛ ብዙኃን ላይም የፋና ወጊነት ሚናን ተጫውተዋል፡፡ የ“መነን” መጽሔት አዘጋጅ ከመሆናቸውም በተጨማሪ የሴቶችን ሕይወት የሚመለከቱ ልዩ ልዩ ትምህርታዊ (የምክር) ጽሑፎችን በጋዜጦችና በመጽሔቶች ላይ በመፃፍም የታወቁና የተደነቁ ነበሩ፡፡
ወይዘሮ ሮማንወርቅ በሙያቸው ላበረከቱት አስተዋፅኦና ላሳዩት ከፍተኛ ስራ ብርታትና ትጋት የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ ከሽልማቶቹ መካከልም ከኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት መንግሥት የወርቅ ሜዳልያ እና በ1956 ዓ.ም የኢትዮጵያ ደራሲያን መታሰቢያ ሽልማት - የብር ሜዳሊያ ይጠቀሳሉ፡፡ ወይዘሮ ሮማነወርቅ የጤና እክል አጋጥሟቸው በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ጥር 23 ቀን 1964 ዓ.ም አረፉ፡፡ ስርዓተ ቀብራቸውም በማግስቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሹማምንትና ሰራተኞች እንዲሁም እጅግ በርካታ ሕዝብ በተገኘበት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተ-ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡ ሞት ቀደማቸው እንጂ “ሔዋን” ፣ “መልካም እመቤት” ፣ “የቤተሰብ አቋም” ፣ “የባልትና ትምህርት” ፣ “የሕፃናት ይዞታ” ፣ “ዘመናዊ ኑሮ” ፣ “የኑሮ መስታዎት” ፣ “ጋብቻና ወጣቶች” ፣ እንዲሁም “የባልና የሚስት ጠብ” በሚሉ ርዕሶች መጻሕፍትን አዘጋጅተው ለሕትመት ለማብቃት እየሰሩ እንደነበረም ይነገራል፡፡ ክብር ለሚገባው ክብር እንስጥ….

Friday, December 30, 2022

የብራዚሉ የእግር ኳስ ኮኮብ ፔሌ ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡

“የእግር ኳሱ ንጉስ” ተብሎ የሚጠራው ብራዚላዊው ኳስ ተጫዋች ፔሌ በ82 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ብሉን በርግ ዘግቧል፡፡ በእግር ኳሱ ዓለም ትልቅ ስም ያለው ብራዚላዊው የእግር ኳስ ተጫዋች ፔሌ ባጋጠመው የካንሰር ህመም ሆስፒታል ገብቶ ህክምና ሲከታተል የቆየ ቢሆንም ህይወቱን ማዳን አልተቻለም። በሙሉ ስሙ ኤድሰን አራንቴስ ዶ ናሲሜንቶ በመባል የሚታወቀው ፔሌ በአለም ዋንጫ ታሪክ ሶስት የዓለም ዋንጫዎችን፣ በ1958፣ 1962 እና በ1970 ከሀገሩ ጋር የውድድሩ አሸናፊ በመሆን ብቸኛ ባለታሪክ ነው፡፡ አለም በእግር ኳሱ ካየቻቸው የምንጊዜም ምርጦች መካከል ስሙ የሚጠቀሰው ኤድሰን አራንቴስ ዶ ናስሜንቶ ወይም በቅፅል ስሙ ፔሌ እ.አ.አ በ1940 በብራዚል ትሬስ ኮራኮስ መወለዱን ታሪኩ ያስረዳል። በልጅነቱ ግብ ጠባቂ ሆኖ ሲጫወት የሠፈሩ ልጆች በአካባቢው በሚታወቅ አንድ ተጫዋች ስም ‘ቢሌ’ ብለው እንደጠሩትና በግዜ ሂደት ስሙ ወደ ‘ፔሌ’ እንደተቀየረ ፔሌ ከዚህ በፊት በሰጣቸው ቃለ ምልልሶች ተናግሮ ነበር፡፡
በታችኛው የብራዚል ሊግ ሲጫወት ቆይቶ እ.አ.አ በ1956 በዋናው ሊግ የሚጫወተውን ሳንቶስ እግርኳስ ክለብን ተቀላቅሎ በአጥቂነት ተጫውቷል። ከሁለት አመት በኋላ ምትሀተኛው አጥቂ ፔሌ በ17 አመቱ ሃገሩ በአለም ዋንጫ እንድትደምቅ አደረጋት፤ በፍፃሜው ጨዋታም ተጋጣሚያቸው ስዊድን ላይ 2 ግቦችን አስቆጥሮ ዋንጫውን ከፍ እንዲያረጉ ምክንያት ሆኗል። ፔሌ በፍጥነት፣በሚዛን አጠበበቅ፣በኳስ ቁጥጥር፣በጥንካሬ እና ተጋጣሚን በሚያሸብሩ እንቅስቃሴዎቹ አለምን ያስደነቀ ነበር። ክለቡ ሳንቶስንም 3 ጊዜ ለሻምፒዎንነት አብቅቷል።
እ.አ.አ ኖቬምበር 19፣1969 18ሺህ ደጋፊዎች በተገኙበት የማራካኛ ስቴድየም ፔሌ 1000ኛ ጎሉን በፍፁም ቅጣት ምት ቫስኮ ደጋማ ላይ አስቆጠሮ ታሪኩን ጽፏል። ፔሌ በ1974 እግር ኳስ በቃኝ ብሎ ጫማውን ቢሰቅልም በ1975 በ7 ሚሊዮን ዶላር የአሜሪካውን ኒውዮርክ ኮስሞስን ተቀላቅሏል። ኮስሞስን ሻምፒዮን ያረገው ፔሌ እግር ኳስ በአሜሪካ እንዲለመድ ጥረት አድርጓል። በ1977 ጥቅምት 1 ፔሌ የመጨረሻውን ፕሮፌሽናል የእግርኳስ ጨዋታውን በጂያንትስ ስቴድየም ከቀድሞ ክለቡ ሳንቶስ ጋር አድርጎ ጫማውን ሰቅሏል። ፔሌ ረጅም አመታትን በተሻገረው ደማቅ የእግርኳስ ህይወቱ ከ1280 በላይ ግቦችን አስቆጥሯል። በ2000 ላይ ፊፋ የሚሊኒዬሙ መርጥ ተጫዋች ሲልም ሰይሞታል። ፔሌ ጫማውን ከሰቀለ በኋላ የስፖርት አምባሳደር ሆኖ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ከዩኒሴፍ ጋር በወዳጅነት ስፖርታዊ ውድድሮች በዓለም ላይ ሰላም እና እርቅ እንዲሰፍን ጥረቶችን አድርጓል። በተለየ ብቃቱና፣ በተወዳጅ ፈገግታው የሚታወቀው ፔሌ እግር ኳስ በዓለም ተወዳጅ እንዲሆን አድርጎ በ82 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡

Wednesday, October 12, 2022

የመስቀል ወፍ እና የአደይ አበባ ...

የመስቀል ወፍን ለአይን ያበቃት የመስከረም ውበት ነው፡፡ የመስከረም ውበት ምስጢር አበቦች ናቸው፡፡ መስከረም ምድር በአበቦች ቀለም አዲስ ልብስ የምትለብስበት ወር ነው፡፡ አደይም እንደመስቀል ወፍ የመስከረም ጌጥ ናት፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው የአደይ አበባ ዝርያ የዕድገት ጊዜውን ሲጨርስ የሚሞት ሲሆን ፍሬው ብቻ መሬት ውስጥ ተቀብሮ የሚቀር ነው፡፡ የሌሎች ግን ግንዳቸው ወይም ስራቸው ተርፎ ይቀራል ፡፡ ዋናው የአበባ ጊዜ በመስከረም ወቅት የሆነበት ምክንያት ግን የአበባ ማውጣት ዑደታቸው መስከረም ስለሆነ እና የዚህ የአደይ አበባ ዝርያ ፍሬ አፍርቶ ደርቆ ተክሉ ከሞተ በኋላ ፍሬው መሬት ተቀብሮ ከስድስት ወር እስከ ሁለት አመት ሊቆይ ስለሚችል ነው፡፡ ይህ ወቅትም የሽልብታ ጊዜ /የዶርማንሲ ፔሬድ/ ይባላል፡፡ በነዚህ ጊዜያት ውስጥ ምቹ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ብቻ ፍሬው እንደገና እንዲበቅል ያደርጋል ማለት ነው ፡፡ ይህም ማለት ለዕፅዋት ብቅለት አስፈላጊ የሆኑት እርጥበት፣ አየርና ሙቀት በበቂ ሁኔታ ሲስተካከል ማለት ነው፡፡ ለማበብ ደግሞ ክረምቱ መውጣት አለበት፡፡ ምንም እንኳን ሐምሌና ነሐሴ ቢበቅልም መስከረም ሳይጠባ አያብብም፡፡
እንደሚታወቀው የዝናብም ይሁን የመስኖ ውሃ ካገኙ በርካታ የሣርና የተክል ዓይነቶች ይበቅላሉ፣ ያብባሉ፣ ያፈራሉ፡፡ የአደይ አበባ አስገራሚው ነገር የቱንም ያክል በበጋ ዝናብ ቢያገኝ ወይም በየትኛውም የመስኖ እርሻ ባለበት አካባቢ አይበቅልም፡፡ ሐምሌ ከገባ ጀምሮ ግን በየእርሻውና በየዳገቱ በተለይ ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነፃ የሆኑ ቦታዎች ሁሉ መብቀል ይጀምራል፡፡ አበባው አንዴ ካበበ በኋላ እንደፈካ ምድርን አስውቦ የሚቆየው ለረጅም ጊዜ አይደለም ፡፡ ቢበዛ ለሶስት ወራት ብቻ ጋራና ሸንተረሩን፤ ሜዳና ተራራውን በተስፋ ሰጪው ቢጫማ ቀለም አስውቦ ይቆይና ይጠፋል ፡፡ ይህም ሌላው የአደይ አበቦች መለያ ባህሪ ነው ፡፡ የመስቀል ወፍ እና የአደይ አበባ ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ ማን ያውቃል...? ይላል ባለቅኔ መንግሥቱ ለማ
"የመስቀል ወፎች ለረጅም ጊዜ ሳይታዩ ቆይተው መስከረም ወር ላይ የሚከሰቱ ዓመታዊ እንግዶች ሳይሆኑ አብረውን ቆይተው በተፈጥሮ ሂደት የላባቸው ቀለም የሚቀየር ቤተኛ አእዋፋት እንደሆኑ በዘርፉ ጥናት እና ምርምር ያደረጉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ ፡፡ እንደ ባለሙያዎቹ ገለፃ የመስቀል ወፍ በተለይ በመስከረም ወር አጋማሽና ቀደም ብለው በጥቁር ፡ ቢጫ ፡ ነጭ እና ብሩህ ደማቅ ቀለም አሸብርቀው የሚገለጡ እንጂ ጠፍተው የሚከሰቱ አይደሉም።
እንደየቋንቋውና እንደየአካባቢው እነዚህ ወፎች የየራሳቸው ስያሜና መጠሪያም ሊኖራቸው ይችላል። የመስቀል ወፍ ተብለው የሚታወቁት እነዚህ አእዋፋት ከኢትዮጵያ ባሻገር በኬንያ፣ ሱዳን ፣ በኡጋንዳ ፣ በታንዛንያ ፣ ሴኔጋል ፣ ደቡብ አፍሪካና ሌሎች ሀገራትም ይገኛሉ።

Saturday, October 1, 2022

እንኳን ለኢሬቻ በዓል በሰላም አደረሳችሁ … !!!


የዓመቱ መስከረም ወር ላይ የኢሬቻ በዓል በደመቀ ስነ ስርዓት ይከበራል፡፡ ይህ ክብረ በዓል በኦሮሚያ ክልላዊ አስተዳደር ትኩረት ከተሰጣቸው ህዝባዊ በዓላት አንዱ ሲሆን በዓሉ የምስጋና፣ የሰላም፣ ፍቅርና አንድነት መገለጫ ነው። የኢሬቻ በዓል አንዱ የገዳ ስርዓት መገለጫ ሆኖም በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳደስ ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡

ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ በህብረት ወደ ተራራ እና መልካ ወይም በወንዝ ዳር ወርዶ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት ስርዓት/በዓል ነው፡፡ ይህ በዓል በተለያዩ ቦታዎች ቢካሄዱም ዋና ዋናዎ በሁለት ይከፈላሉ፡፡ እነርሱም “ኢሬቻ ቱሉ” እና “ኢሬቻ መልካ” በመባል ይታወቃሉ፡፡ 

የበጋ ወቅት አልፎ በበልግ ወቅት ላይ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል “ኢሬቻ ቱሉ” ይባላል፡፡ ይህም በበጋ ወቅት ሰው እና እንሰሳት በድርቅ ሲጠቁ ወይም ሲጎዱ ወደ ተራራ በመውጣት የበልግ ዝናብ እንዲዘንብላቸው ፈጣሪን የሚለማመኑበት ስርዓት ነው፡፡

ክረምት አልፎ በፀደይ መግቢያ ወቅት ላይ በቢሾፍቱ ከተማ በድምቀት የሚከበረው ደግሞ “ኢሬቻ መልካ” በዓል ይባላል፡፡ ይህ በዓል ከክረምት ወደ በጋ በሰላም ስላሸጋገራቸው እርጥብ ሳር እና አደይ አበባ በመያዝ ወንዝ ዳር ወጥተው ፈጣሪን የሚያመሰግኑበት ስርዓት ነው፡፡ በዚህ በዓል ላይም ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ በርካታ ሰዎች ይታደማሉ፡፡

Saturday, September 24, 2022

ከ1ኛ ክፍል እስከ ዶክተርነት ሕልማቸውን ያሳኩ 16 አብሮ አደጎች….


የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዘንድሮ በመጀመሪያ ዲግሪ ከሚያስመርቃቸው 250 ከሚበልጡ የህክምና ተማሪዎች ውስጥ 16 ከልጅነት ጀምሮ የሚተዋወቁ ወላይታ ሊቃ ከተባለ ትምህርት ቤት አብረው የመጡ ወጣቶች ናቸው፡፡

አብሮ አደገቹ ከለጋ እድሜያቸው አንስቶ ሀኪም የመሆን ልዩ ፍላጎት የነበራቸው ሲሆን ህልማቸውን እውን ለማድረግም አብሮ በማጥናት እና በመደጋገፍ ሲተጉ መቆየታቸውን ይገልጻሉ፡፡ የዚህ ትልማቸው መነሻ የጀመረውም ወላይታ ሊቃ በወላይታ ልማት ማህበር (ወልማ) በተቋቋመው ትምህርት ቤት ነው።

 16 ጓደኛማቾች መሃል አብዛኛዎቹ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ አብረው የተጓዙና ጠቂቶቹ ደግሞ ከአምሰተኛ ክፍል ተቀላቅለዋቸው እስከ 12 ክፍል ድረስ በትምህረፍት ቤቱ ቆይታ አድርገዋል። የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት መምህራን ዛሬ ለደረስንበት ደረጃ የማይተካ ሚና ነበራቸው የሚሉት ሀኪሞቹ ግንኙነታቸው የተማሪ እና የአስተማሪ አይነት ሳይሆን የወላጅ እና የልጅ እንደነበረ ያስታውሳሉ። 

 


ወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት አቅም በፈቀደ በእውቀት የዳበረ እና ራዕይ ያለው የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር፣ ተማሪዎችን በመልካም ስብዕና ለማነፅ የነበረው ቁርጠኝነት ለዛሬ የተሟላ ስብዕናቸው መሠረት እንደነበርም አውስተዋል። 

 አብሮ አደገቹ ሐኪሞች ዩኒቨርስቲ ከገቡም በኋላ ግንኙነታቸው ይበልጥ ተጠናክሮ ያለፉትን 7 ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በብርቱ ወንድማማችነት ያሳለፉ ሲሆን፣ በግቢ ቆይታቸውም የሕክምና ትምህርት የሚጠይቀውን ትዕግሥት እና ትጋት ማዳበራቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።