Thursday, April 20, 2017

ታላቁ የስነ ስዕል ባለሟል ፣ የስነ ጥበብ ት/ቤት መስራች እና የመጀመሪያው መምህር .....


  አያታቸው ሰዓሊ አለቃ ህሩይ ልጃቸው ፈለገሰላም በጉጉስ ጨዋታ ወቅት በአደጋ ህይወታቸው በማለፉ በሀዘን ላይ ናቸው፡፡ ሀዘናቸው ይበልጥ መሪር የሆነው ደግሞ ልጃቸው ገና 40 ቀን ብቻ ያስቆጠረ ጨቅላ ህፃን እንደ ወለዱ በመሞቱ ነው፡፡ እናም አያቱ አለቃ ህሩይ ህፃኑን ትኩር ብለው ቢመለከቱት ሟች ልጃቸውን መስሏቸው ተፅናኑ፡፡ አልሞተም ልጄ አሉ፡፡ አለ ልጄም ሲሉ ተናገሩ፡፡ በዚህ ምክንያት የህፃኑ መጠሪያ ለአባቱ ማስታወሻ እንዲሆን “አለ” ተባለ፡፡ አለፈለገሰላም ህሩይ ይህ የሆነው የዛሬ 93 ዓመት ፣ ሀምሌ 24 1915ዓ.ም ነው፡፡
   

  አለቃ ህሩይ የነገስታት እና መንፈሳዊ(መለኮታዊ) ስዕሎችን በመስራት የተደነቁ ነበሩ፡፡ የልጅ ልጃቸው “አለ”ም የአያታቸውን ፈለግ በመከተል ከጥበብ እና ከስራ ሁሉ ስዕልን አስበልጠዋል፡፡ በአሜሪካ ቺካጎ የከፍተኛ ስነ ጥበብ ትምህርታቸውን ተከታትለው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በ1947ዓ.ም ከአሜሪካ የትምህርት ቆይታቸው በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የዘመናዊ ስዕል ት/ቤት እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡  የስነ ጥበብ እና ዲዛይን ት/ቤት መስራች ሲሆኑ በዳይሬክተርነትም  ከ1951 - 1966ዓ.ም አገልግለዋል፡፡


   ለዘመናዊ የኢትዮጵያ ስነ ስዕል ትምህርት መሰረት የጣሉት አለ ፈለገሰላም የስዕል ጅማሮአቸው መልክዓ ምስል (ፖርትሬት ኪነ ንድፍ) ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ እውነታዊ ፣ ባህላዊ እና ትውፊታዊ ስራዎች ላይ ያተኩራሉ፡፡ ብዙዎቹ ስራዎቻቸውም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በርካታ የቤተ ክርስቲያን ግድግዳዎች እና ጉልላቶች በእኚህ ስመ ጥር ሰዓሊ ቡርሾች የተዋቡ ናቸው፡፡ ሂልተን ሆቴልም የሚገኝ ስዕል አላቸው፡፡


   ከስነ ጥበባት እና ዲዛይን ት/ቤት ዳይሬክተርነታቸው ባሻገርም በቅርስ ጥናት እና ጥበቃ የቅርስ ጥበቃ ክፍል ሀላፊም ሆነው ሰርተዋል፡፡ በተደጋጋሚ ከልዩ ልዩ አደጋዎች በመትረፋቸው ከሞት የተፋጠጡ የአልሸነፍ ባይነት ተምሳሌት ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡



    በኢትዮጵያ ትውፊታዊውን ከዘመናዊ አሳሳል ጋር አዋህደው የሚሰሩት አለ ፈለገሰላም በሙያቸው ላበረከቱት አስተዋፅኦም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስነ ጥበባት እና ዲዛይን ት/ቤት በስማቸው እንዲጠራ ተደርጓል፡፡ “አለ የስነ ጥበባት እና ዲዛይን ት/ቤት” ተብሎም ተሰይሟል፡፡ በህይወት ዘመናቸው ለነበራቸው አበርክቶም ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ ልዩ ልዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ በ93 ዓመታቸው ይህቺን አለም የተሰናበቱት አለ ፈለገሰላም በደብረሊባኖስ ገዳም ሀምሌ 6፣ 2008 ዓ.ም የቀብር ስነ ስርዓታቸው ተፈፅሟል፡፡

No comments:

Post a Comment