Thursday, March 17, 2016

"ዛሬ ማታ በሕልሜ ከብልቴ ፀሐይ ስትወጣ አየሁ …" - የአጤ ምኒልክ እናት


   በኢትዮጵያ የታሪክአፃፃፍ ሒደት ውስጥ የአጤ ምኒልክን ታሪክ በሚገባ የፃፈ ሰው ቢኖር ጳውሎስ ኞኞ ነው። ጳውሎስ አጤ ምኒልክን አብሯቸው የኖረ እና ከእጃቸው የበላ የጠጣ ይመስል እያንዳንዱን ጥቃቅን ታሪካቸውን ሁሉ ለትውልድ ያስተላለፈ ብርቅዬ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ታሪክ ፀሐፊ እና ዲስኩረኛ ነበር። በአጤ ምኒልክ ታሪክ ብቻ ሦስት ታላላቅ መፃሕፍትን ያበረከተ ጆቢራ ከያኒ ነበር።
 
  አንደኛው ቀደም ባሉት ዘመናት አዘጋጅቶት 1984 . ያሳተመው 509 ገጾች ያሉት አጤ ምኒልክ የሚለው መጽሐፉ ነው። ሁለተኛው እርሱ ከሞተ በኋላ አስቴር ነጋ አሳታሚ ድርጅት ከጳውሎስ አንድያ ልጅ ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር በመተባበር 2003 . ያሳተሙት አጤ ምኒልክ በሀገር ውስጥ የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች የሚለው 622 ገጾች ያሉት ግዙፍ መጽሐፍ ነው። 

   ሦስተኛው ደግሞ አሁንም አስቴር ነጋ አሳታሚ ድርጅትና ሀዋርያው ጳውሎስ በመተባበር ያሳተሙት አጤ ምኒልክ ከውጭ ሀገራት የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች ባለ 337 ገጾች የሆነው መጽሐፍ ነው። በእነዚህ ታላላቅ መፃሕፍቶቹ የአድዋውን ጀግና ጳውሎስ ኞኞ ከልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮች አንፃር ዘክሯቸዋል። የፊታችን ሰኞ የካቲት 23 ቀን የአድዋ በዓል ነውና እኔም ጳውሎስ ኞኞ ሰጥቶን ካለፋቸው ታሪኮች ውስጥ በጣም ያስገረመኝን የአጤ ምኒልክን አፈጣጠር የተመለከተውን ወግ ላጫውታችሁ ብዬ አሰብኩ። 

   ታሪኩ እንዲህ ነው፡የኋለኛውን የሀገራችንን ታሪክ ስንቃኝ ብዙ አስገራሚ ነገሮችን እናገኛለን። ለምሳሌ መነኩሴዎችና ትንቢት ተናጋሪዎች በሰፊው የሚታመንባቸው ወቅት ነበር። እነርሱ የተናገሩት መሬት ጠብ አይልም፤ እውነት ነው ተብሎ ይታመናል። የነገስታት ጋብቻ ሁሉ የሚወሰነው በኮከብ ቆጣሪዎች አማካይነት ነበር። እከሊትን ካገባህ የስልጣን ዘመንህ የተረጋጋ፣ እድሜህ የረዘመ፣ ሕይወትህ የለመለመእየተባለ ብዙዎች በዚህ መስመር ተጉዘውበታል። ለጦርነት ዘመቻ ሁሉ የሚወጣው እነዚህአዋቂዎችበሚያዙት መሠረት ነበር። ጉዳዩ እስከ ቅርብ ጊዜ ይሰራበት ነበር። 1950ዎቹ የተነሱት ማርክሲሰት ሌኒኒስት ፍልስፍናዎችና ትግሎች እያዳከሙት መጡ እንጂ፣ እንዲህ አይነቱእምነትበሀገራችን ትልቅ ቦታ ነበረው። ይህን ርዕሰ ጉዳይ አያሌ ምሳሌዎችን እየጠቃቀስን ወደፊት እንጨዋወትበታለን። ለዛሬ ግን ቀደም ብዬ ወደጀመርኩት ርዕሰ ጉዳይ ላምራ። አጤ ምኒልክ እጅግ ብልሕ መሪ እንደነበሩ ታሪካቸውን የፃፉ ሁሉ ይመሰክራሉ። ጳውሎስ ኞኞ ደግሞ ምኒልክ ወደዚህች ዓለም ሲመጡ፣ ሲፈጠሩ ጀምሮ የተለየ ታሪክ እንዳላቸው ጽፎልናል።

  
  ምኒልክ በትዕዛዝ የተወለዱና ልዩ ፍጡር መሆናቸውን ጭምር የሚያስረዳው የጳውሎስ ገለፃ የሚከተለው ነው፡ምኒልክ 1836 . ነሐሴ 12 ቀን ቅዳሜ ዕለት ተወለዱ። አባታቸው ኃይለመለኮት ሳህለሥላሴ ሲሆኑ፤ እናታቸው / እጅጋየሁ ለማ አዲያሞ ይባላሉ። የምኒልክ እናት / እጅጋየሁ የንጉሥ ሣህለሥላሴ ሚስት የወ/ በዛብሽ ገረድና የልጆች ሞግዚት ነበሩ። እጅጋየሁ የግርድና ሥራ የጀመሩት በንጉሥ ሣህለሥላሴ ቤት አልነበረም። ንጉሥ ሣህለሥላሴ ቤት ከመቀጠራቸው በፊት የአንኮበር ቤተ-ከርስትያን አለቃ የነበሩት የመምህር ምላት ገረድ ነበሩ። በአለቃ ምላት ቤት ግርድና ተቀጥረው ሳለ አንድ ቀን ጧት ለጓደኞቻቸው “… ዛሬ ማታ በሕልሜ ከብልቴ ፀሐይ ስትወጣ አየሁ…” ብለው ተናገሩ።
  “ሥራ ቤቶች የሰሙት ወሬ መዛመቱ አይቀርምና ወሬው ከጌትዮው ከአለቃ ምላት ዘንድ ደረሠ። አለቃ ምላትምእንግዲያው ይህ ከሆነ ወደላይ ቤት ትሂድአሉ። የላይ ቤት የሚባለው የአንኮበሩ የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ቤተ-መንግሥት ከኮረብታ ላይ በመሆኑ አገሬው በተለምዶላይ ቤትይለዋል።

   “እጅጋየሁ እንደተመከሩት ከንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ቤት ሔደው ተቀጠሩ። የእጅጋየሁ የሕልም ወሬ ተዛምቶ ንጉሥ ሣህለ ሥላሴም ቤት ገብቶ ስለነበር የንጉሥ ሣህለሥላሴ ባለቤት / በዛብሽ ከልጃቸው ሁሉ አብልጠው ሰይፉ ሣህለሥላሴን ይወዱታል። ስለዚህ ሰይፉ ከእጅጋየሁ ልጅ እንዲወልድ ማታ እጅጋየሁን ወደ ሰይፉ መኘታ ቤት ልከው ያን ጐረምሳ እንድትጠብቅ አደረጉ።
   “የልጅ ሰይፉ አሽከሮች የእጅጋየሁን መላክ እንዳወቁ ለጌታቸው ለልጅ ሰይፉ ተናገሩ። ሰይፉ የሚወዳት ሌላ ሴት አለችው። የአዲሲቱን የእጅጋየሁን መምጣት እንደሰማ ተናዶ እንዳያባርራትም እናቱን ፈርቶ ከወንድሙ ከኃይለመለኮት ዘንድ ሄዶእባክህ ሌላ ሴት ከሌለህ እሜቴ የላኳትን ያቺን ገረድ ውሰድልኝአለ። ኃይለመለኮትም እሺ ብሎ ከእጅጋየሁ ጋር ባደረጉት ግንኙነት ልጅ ተፀነሰ።
  “እናትየዋ / በዛብሽ የእጅጋየሁን መፀነስ እንዳዩ ከሰይፉ ያረገዘች መስሏቸው ተደሰቱ። በኋላ ግን ከሌላው ልጃቸው ከኃይለመለኮት ማርገዝዋን ሲሰሙ ተናደው እጅጋየሁን በእግር ብረት አሰሩዋት። ቆይቶም በአማላጆች ተፈታች። ንጉሥ ሣህለሥላሴ ይህን ወሬ ሰሙ። ልጃቸው የንጉሥ ልጅ ሆኖ ገረድ በማፀነሱ ተናደው ወሬው እንዳይሰማ እጅጋየሁን ከርስታቸው ከአንጐለላ ሄዳ እንድትቀመጥ አደረጉ።
   “እጅጋየሁ የመውለጃ ጊዜዋ ሲደርስ ወንድ ልጅ ወለደች። የእጅጋየሁን መውለድ ንጉሥ ሣህለሥላሴ ሲሰሙ የልጁን ሥምምን ይልህ ሸዋ በሉትብለው ስም አወጡ።ምን ይልህ ሸዋያሉበት ምክንያት የእኔ ልጅ ከገረድ በመውለዱ ሸዋ ምን ይል ይሆን? ለማለት ፈልገው ነው። በኋላ ግን በሕልማቸው ከምን ይልህ ሸዋ ጋር አብረው ቆመው ከእሳቸው ጥላ የልጁ ጥላ በልጦ፣ በእግር የረገጡትን መሬት ሲያለካኩ እርሳቸው ከረገጡት ልጁ የረገጠው ረዝሞ አዩ። ይህን ሕልም ካዩ በኋላምኒልክ የእኔ ስም አይደለም። የእሱ ነው። ስሙን ምኒልክ በሉትብለው አዘዙ።

   “እዚህ ላይ ንጉሥ ሣህለሥላሴ “… ምኒልክ የእኔ ስም አይደለም የእሱ ነው…” ያሉት በጥንት ጊዜምኒልክ በሚል ስም የሚነግሥ ንጉሥ ኢትዮጵያን ታላቅ ያደርጋታልየሚል ትንቢት ስለነበረ ሣህለሥላሴ ሲነግሱስሜ ምኒልክ ይሁንብለው ነበር። ምኒልክ በሚለው ስም ሣህለሥላሴ ለምን እንዳልነገሱ ክብረ-ነገሥት በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ብንመለከት “… የሸዋው ንጉሥ ሣህለሥላሴ፣ ምኒልክ በሚባል ሥም ሊነግሱ ሲሉ አንድ መነኩሴ በዚህ ስም አትንገስ። መጥፎ አጋጣሚ ያመጣብሃል። ይህ ስም የሚስማማው ከመጀመሪያው ወንድ ልጅህ ከኃይለመለኮት ለሚወለደው ነው። ይህም ስም የሚወጣለት የልጅ ልጅህ ኢትዮጵያን አንድ የሚያደርግ ትልቅ ንጉሥ ይሆናል አላቸው…” ይላል። ስለዚህ ነው የልጁን ስም ምኒልክ ያሉት።

   “ይሔው ከድሃ መወለድ በዘመኑ እንደ ነውር ተቆጥሮ፣ ምኒልክ በሣህለ ሥላሴ ቤተ-መንግሥት ውስጥ እንዳያድጉ ተደርጓል። ፀሐፌ ትዕዛዝ ገብረሥላሴ እየፈሩ ከፃፉት ብጠቅስ፤ “… ስለ ሕዝብ ዕረፍትና ጤና፣ የተወለደው ምኒልክ በአንጐለላ መቅደላ ኪዳነ ምህረት ክርስትና ተነስቶ ጠምቄ በሚባል ሀገር በሞግዚት አኖሩት….” ብለዋል። አንጐላላ ከደብረብርሃን ከተማ አጠገብ ያለ መንደር ነው። መንዝ ውስጥ ባለው ጠምቄ በሚባለው አምባም ከእናታቸው ጋር ሰባት ዓመት ተቀመጡ።
 
  “ፈረንሣዊው ሄነሪ አውደን 1872 . ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ነበር። ስለ ምኒልክ ትውልድ ሲተርክ “… ምኒልክ በተወለዱ ጊዜ መስፍኑ (ኃይለመለኮት) ልጁን አልቀበልም ብለው ካዱ። በነገሩ መሐል / በዛብሽ ገብተው ሌሎቹንም ዘመዶቹን ሰብስበው ልጁ ኃየለመለኮት መሆኑን አምነው ተቀበሉ።…” ይላል።  “ብዙ ታሪክ ፀሐፊዎች እንደሚሉት / እጅጋየሁ ውብና ከደህና ቤተሰብ መወለዳቸውን ይገልፃሉ። የአባታቸውንም ስም ግን የሚገልፅ የለም። ለማ አዲያሞ ይባላሉ። ይህን ሲተነትኑም አንዳንዶቹ ከጉራጌ አገር የተማረኩ ባርያ ናቸው ይሏቸዋል። 
  ባርያ ማለት በገንዘብ የሚሸጥ ብቻ ሳይሆን በጦርነት የሚማረክ ሁሉ ባርያ ይባላል። ይህ ሁሉ ይቅርና ዋናው ቁም ነገር ታሪክ መስራት እንጂ ትውለድ አይደለም።ታላቁ ናፖሊዮን እንደዘመኑ አፃፃፍ ወደ ላይ የሚቆጠር አልነበረውምና ታሪኩን የሚፅፈው ፀሐፊ ቀርቦየትውልድ ታሪክዎን ከየት ልጀምር?” ቢለውያለፈውን ትተህ ከእኔ ጀምርአለ እንደሚባለው ነው። ዛሬ በአጤ ምኒልክ ዙሪያ እንድታነቡልኝ የጋበዝኳችሁ ጽሁፍ ምክንያቱ ደግሞ የአድዋ ድል መባቻ ሳምንት በመሆኑ ነው። እኚህ በጥቁር ዓለም ውስጥ እጅግ ገናን ስም እና ዝና ያላቸው ንጉስ፣ ኢትዮጵያ በነጮች የቅኝ አገዛዝ ስር እንዳትወድቅ ተአምራዊ በሚባል የጀግንነት ውሎ ሀገራቸውን ነፃ ያወጡ መሪ ናቸው።
ምኒልክ ተወልዶ ባያነሣ ጋሻ፣
ግብሩ ዕንቁላል ነበር ይሄን ጊዜ አበሻ።” ተብሎ የተገጠመላቸው ናቸው። መልካም የአድዋ ድል ሣምንት እመኝላችኋለሁ፡፡
                                          ምንጭ ፡- ተፃፈ  በጥበቡ በለጠ

No comments:

Post a Comment