Thursday, February 18, 2016

የጦር አርበኛ፣ ፀሐፊ- ተውኔት፣ ደራሲ፣ የመጀመሪያዋ ሴት የፓርላማ ተመራጭ እና ዲፕሎማት …… ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ


    ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ በሸዋ ክፍለ ሀገር በመናገሻ አውራጃ አዲስ ዓለም ከተማ ጥር 6 ቀን 1908 . ተወለዱ። አባታቸው ታዋቂው ዲፕሎማት፣ የመጀመሪያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዘደንት፤ ጣሊያኖች ከኢትዮጵያ ከወጡ በኋላ ደግሞ የምክር ቤቱ ፕሬዘደንት ፤በዳግማዊ ምኒልክ  ሹመትም የመጀመሪያው ጎንደር ከተማ አስተዳዳሪ የነበሩት ከንቲባ ገብሩ ደስታ ሲሆኑ ታናሽ እህታቸው ደግሞ የውብዳር ገብሩ (እማሆይ ጽጌ ማርያም) ናቸው።

 ዕድሜያቸው ለትምህርት በደረሰበት ወቅት እቤታቸው አስተማሪ ተቀጥሮላቸው አማርኛ ትምህረት ከፊደል መቁጠር እስከ ዳዊት መድገም በቤታቸው ተማሩ። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ሄደው ስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት በመግባት እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምረዋል። ከንቲባ ገብሩ ወጣቷን ስንዱ ገብሩን እያስከተሉ ወደ ቤተ መንግሥትም ሆነ ሌላ ሥፍራዎች ይወስዷቸው እንደነበረና ከጊዜው አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንንም ጋር እንዳስተዋዋቋቸው ተዘግቧል።


    አልጋ ወራሹም የወጣቷን ብልህነትና ትጋት በማድነቅ ወደ ፈረንጅ አገር ተልከው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ባዘዙት መሠረት ወይዘሮ ስንዱ 1921 . (ፊታውራሪ አመዴ 1919 . ይላሉ) ወደ ስዊስ ለትምህርት ቢሄዱም ኑሮው ስላልተመቻቸውና ትምህርት ይሰጥበት የነበረውን ጀርመንኛ ቋንቋ ስላልወደዱት ወደ ፈረንሳይ አቅንተው ትምህርታቸውን ቀጠሉ። በመጨረሻም ስዊስ እና ፈረንሳይ ሁለት ትምህርት ቤቶች በመዘዋወር በዲፕሎማ ተመረቁ። እዛው የሕግ ትምህርት ለመቀጠል ጀምረው የነበረ ቢሆንም፤ ፍላጎታቸው ወደ ሥነ-ጽሑፍ በማዘንበሉ በአጠቃላይ ለአምስት ዓመታት እዛው ተምረው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ። ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱም አዲስ አበባ በቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ውስጥ የፈረንሳይኛ ቋንቋን፣ ሀይጅን፣ ቁጥርንና የአማርኛ ድርሰት አጻጻፍን ማስተማር ጀመሩ።



     ፋሺስቶች ኢትዮጵያን በወረሩ ጊዜ ወይዘሮ ስንዱ   ሆለታ ውስጥ ከሚገኙ  የጦር መኮንኖች ጋር ተቀላቅለው ፋሺስቶችን ለመፋለም ወደ ቦሬ ሄዱ። እዚያም የመትረየስ አተኳኮስ ትምህርት ተማሩ። ወደ ነቀምት በመሄድም ሕዝቡን እየሰበሰቡ ስለ ነፃነት ማስተማሩን ተያያዙት። በዚህ ወቅት በባንዳዎች ጠቋሚነት በፋሽስት እጅ ከመውደቅ ለጥቂት አምልጠው ጎሬ ላይ ልዑል ራስ እምሩ ጦር ጋር ተቀላቀሉ። 

  ከዚያም በጦርነቱ የሚጎዱ አርበኞችን ለማከም የሚሆን ቀይ መስቀል ለማቋቋም መፈለጋቸውን ለራስ እምሩ አማክረው በተሰጣቸው አምስት መቶ ብር አቋቁመው አርበኞችን መርዳት ጀመሩ። ወዲያው ግን እርሳቸው ተቀላቅለውት የነበረው የጥቁር አንበሳ ጦር ሲመታ ጣልያን  ሠራዊት እጅ ተማርከው በእስር ወደ አዲስ አበባ አመጧቸውና የቁም እስረኛ ሆኑ።
የካቲት 12 ቀን 1929. ግራዚያኒ ለመግደል በተደረገው ሙከራ ወንድማቸው መሸሻ ገብሩ አሉበት በመባል ይታሰሱ ስለነበር ወንድማቸውን ከአደጋ ለማዳን ሲሞክሩ በድጋሚ በፋሺስቶች እጅ ወደቁ። በወቅቱ ግራዚያኒ ይኖርበት የነበረው ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ውስጥ ታሰሩ። ቀጥሎም ወደ አስመራ ከዚያ ወደ ምጽዋ ተወሰዱ። ከምጽዋ ወደብ ሦስት መቶ ወንዶችና ስምንት ሴቶች (እማሆይ ጽጌ ማርያምን ጭምር) ሆነው በመርከብአዚናራወደተባለች የኢጣሊያኖች እስር ቤት ተወስደው ዘጠኝ ወራት ታሰሩ። ከእስር በኋላም ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ በእንደዚህ ያለ ተግባር ላይ እንዳይሰማሩ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም፤ ማስፈራሪያው ሳይበግራቸው አርበኞችን በግጥም፣ በወኔ ቀስቃሽ ጽሑፎች በማበረታታት፣ መረጃ በማቀበል፣ መሣሪያ በማዳረስ የጀግንነት ተግባር ፈጽመዋል።

   ወ/ ስንዱ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት በሀገር ፍቅር ስሜት በመነሣሣት በርካታ ስሜት ቀስቃሽ ግጥሞችን ጽፈዋል፡፡  የኢትዮጵያ ትግል፣ አድዋ፣ አፄ ቴዎድሮስ፣ የታጋዮች ስሜት ከግራዚያኒ ንግግር በኋላ፣ ኮከብህ ያውና ያበራል ገና፣ የየካቲት ቀኞች፣ ከማይጨው መልስ፣ የኑሮ ስህተት፣ የልቤ መጽሐፍየታደለች ሕልም፣ ርዕስ የሌለው ትዳር፣ ፊታውራሪ ረታ አዳሙየሚሉት ሥራዎቻቸው የገጣሚዋን የሀገር ፍቅር ስሜትና የሥነ ጽሑፍ ችሎታ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ 
  ከድል በኋላ ወይዘሮ ስንዱ  ለሁለት ዓመታት ደሴ ከተማ የሚገኘው ወይዘሮ ስሂን ትምህርት ቤት አስተዳዳሪ በመሆን፣ በኋላም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው እቴጌ መነን ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህርነት፣ ከዚያም የመጀመሪያዋ ሴት ርዕሰ መምህር ሆነው አገልግለዋል። 1948 . እስከ 1952. ድረስ የመጀመሪያዋ የሴት የሕግ መምሪያ ምክር ቤት  አባልና  የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ሊቀ መንበር ሆነውም አገልግለዋል። በዚህ ምክር ቤት አባል በነበሩበት ጊዜ ብቸኛዋ ሴት ከመሆናቸውም ባሻገር የሴቶች እኩልነት በማይከበርበት ጊዜ እናየወንድ ዓለምበገነነበት የታሪክ ምዕራፍ የሴቶችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበርና እኩልነትን በሕግ ለማስተማመን ብዙ የታገሉ ሴት ነበሩ።



    የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበር ፕሬዝዳንት፣ የሕዝባዊ ኑሮ እድገት ዋና ፀሐፊነትና አስተዳዳሪነት፣ በምዕራብ ጀርመን ለሦስት ዓመት የትምህርት አታሼ በመሆን አገልግለዋል። ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ ላበረከቷቸው አስተዋጽዖዎች የወርቅ ሜዳሊያ፣ የንግሥት ሣባ የወርቅ ኒሻን፣ የቀይ መስቀል የወርቅ ሜዳሊያ እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷቸዋል።



   የመጀመሪያዋ የሴት ፓርላማ አባል፣ የሴት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ ጀግናና ፀረ-ፋሺስት አርበኛ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣ የመጽሐፍ ደራሲ፣ እና የመጀመሪያዋ የሴት ዲፕሎማት ስንዱ ገብሩ(የክቡርት ዶክተር) ሰኞ ሚያዝያ 12 ቀን 2001 . በተወለዱ በ93 ዓመታቸው ሕይወታቸው አልፎ መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተቀብረዋል።

No comments:

Post a Comment