Thursday, September 10, 2015

እንቁጣጣሽ /አዲስ ዓመት/



     በንፋሱ ማየል እና ማነስ፣ መቀዝቀዝ እና መሞቅ፣ በተለያዩ አበቦች እና ቅጠሎች ማበብና መርገፍ፣ በዳመናው መጥቆር እና መንጣት፣ እንደየቦታው ሁኔታ ተፈጥሮአዊ በሆኑ ልዩ ልዩ ክስተቶች ጊዜ እንዳለፈ፣ ወቅት እንደተለወጠ፣ ዘመን እንደተቀየረ ማወቅ ይቻላል፡፡ በእነዚህ ወቅትና ሁኔታዎች ያሉ አውዳመቶችም በተለያየ ቦታ የተለያየ መልክ ይኑራቸው እንጂ የብዛም ይነስም ይከበራሉ፡፡ የተፈጥሮ ድምር አባል የሆነው የሰው ልጅም ከሁሉ ተለይቶ በተካነው የማሰብ እና የመፍጠር ችሎታው ቀናትን፣ ወራትን እና ዘመናትን ከፈፀማቸው ድርጊቶች እና ካጋጠሙት ሁኔታዎች ጋር ትዝ እንዲሉት ያደርጋል፡፡ በየዓመቱ የተወለደበትን ቀን እንደ ቤቱ አቅም እና ፍቃድ አክብሮ እና አስቦ የሚውል ሰው ጥቂት አይደለም፡፡ የጋብቻ ቀኑን፣ ስራ ጀመረበትን እለት፣ ምንም የሆነበትን ይሁን ያደረገበትን ቀን በተለያየ መንገድ ለማስታወስ ይሞክራል፡፡

    በተለይ በሃገራችን ወግና ልምድ አውዳመቶች በመጡ ቁጥር ለየት ያለ ከበሬታ ይደረግላቸዋል፡፡ የሚደረግላቸው የአከባበር አይነትም ሆነ ድምቀት እንደ አውዳመቶቹ የተለያየ ነው፡፡ ለገና እነደ ፋሲካ ፣ ለፋሲካ እንደ እንቁጣጣሽ፣ ለእንቁጣጣሽ እንደ አረፋ፣ ለአረፋ ደግሞ እንደ መወሊድ ላይደገስ እና ላይደምቅ ይችላል፡፡ በተለያየ ምክንያት ማለት ነው፡፡ አንዱ ቤት የአረፋ በዓል ሲደምቅ ሌላው ቤት የመወሊድ በዓል ከፍ ያለ ቦታ ይሰጠዋል፡፡     ለአንዱ ቤተሰብ ገና ትልቅ በዓል ሲሆን ለሌላው ደግሞ የደመራ በዓል የተለየ ይሆናል፡፡ እረ በዓል ማለት ፋሲካ ነው የሚልም አይጠፋም፡፡ የምን ፋሲካ ጥምቀት ነው እነጂ ዓመት በዓል “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” የሚባልበትም ቤት አለ፡፡በሌላ በኩል በሀገራችን ተፈጥሮ እንኳን ራሷ ለመስከረም ወር የምታደላለት በዓል ማለት “እንቁጣጣሽ” ነው የሚሉም አይታጡም፡፡ እንቁጣጣሽ /አዲስ ዓመት/ ለእኛ የተለየ ነው የሚሉት እነዚህ አካላት ሃሳባቸውን በስነ ቃል ያጠናክራሉ፡፡
ውብ መስከረም ለምለም
ውብ መስከረም ለምለም
ከወራቶች ሁሉ ውብ እንዳንቺ የለም፡፡ እያሉ አዲስ ዓመትን /እንቁጣጣሽን/ ከወርሃ መስከረም ጋር አያይዘው ያወድሳሉ፡፡


     በሁለት ወር ክረምት ቆሻሻው ተጠራርጎ፣ የደረቀው፣ የወረዛው እና የረገፈው ቅጠል ለምልሞ እና አቆጥቁጦ፣ ውብ አበባዎችም በየመስኩ ደምቀው ይታያሉ፡፡ የመስከረም ወር ለምለም የሚታይበት እና ምድር በአበባ የምትሸፈንበት ወቅት በመሆኑ ለእንቁጣጣሽ የሚዘጋጁ ዘፈኖች ልምላሜን በሚያጎሉ ቃላት ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ዘመን አልፎ ዘመን ሲለወጥ ፣ ዳመናው ተሸኝቶ ሰማዩ ሲገለጥ ምድር በአበቦች ልምላሜ ትንቆጠቆጣለች፡፡ በመስከረም የሚታዩት ወፎች እንኳን መስከረም ጠባ እንዲሉ የተላኩ ይመስላሉ፡፡ ፀሀይም ገና ብቅ ከማለቷ የአዲስ አመት ፀሀይ እንደሆነች ፈገግተዋ ያሳብቅባታል፡፡ እኛም ታዲያ እንደየሁኔታው በአዲስ መንፈስ ቤታችንን እና ግቢያችንን አፀዳድተን፣ ቤት ያፈራውን አዘጋጅተን ፣ ለበዓሉ የሚገባውን የየበኩላችንን አቅርበን ነው እንቁጣጣሽን የምንቀበለው፡፡


    በህፃናት ዘፈንና ጭፈራ መስከረምን እንኳን ደህና መጣህ ብለን፣ ከዘመድ ተጠያይቀን፣ በልጆች አበባ ስጦታ እንኳን አደረሰህ/ሽ ተባብለን በተቻለን መጠን እንደየአቅማችን በዓሉን በጥሩ ሁኔታ ለማክበር እንጥራለን፡፡ እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ ብያለሁ፡፡ ከአያት ቅድመ አያቶቻችን ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው ምርቃት እኔም የአመት ሰው ይበለን ብዬ ተሰናበትኩ፡፡
           .…ከብረው ይቆዩን ከብረው ፣ ላመት ወንድ ልጅ ወልደው
               በመጋረጃ ውለው ፣ ሃምሳ ጥገቶች አስረው
              ከብረው ይቆዩን ከብረው ፣ ከብረው ይቆዩን ከብረው!!!

Saturday, August 22, 2015

“ከስጋ ቤት እስከ ታዋቂ ተዋናይነት......” አርቲስት ተዘራ ለማ

   
    ከስጋ ቤት እስከ ህብረት ሱቅ ሽያጭነት…… ከተወዛዋዥነት እና ጊታር ተጨዋችነት እስከ ታዋቂ ተዋናይነት ለመድረስ በቅቷል፡፡ በከፍተኛ18 ኪነት ቡድን ውስጥ አሁን ታዋቂ ከሆኑት ከእነ ፋሲካ ዲሜትሪ እና ዳዊት መለሰ ጋር ተጫውቷል፡፡ በጊዜውም በኪነት ቡድኑ ውስጥ በተወዛዋዥነት እና በጊታር ተጫዋች ነት ያገለግል ነበር፡፡ ከ1983 ዓ.ም በኋላ ኪነት ቡድኑ በመበተኑ እሱም ከጥበቡ አለም ርቆ ወደ ሹፍርና ሙያ ይገባል፡፡ በሹፍርናም ለ20 ዓመታት ያህል ሰርቷል፡፡ በሹፍርና በአገለገለበት ዘመንም የተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎችን የዞረ ሲሆን በርካታ ውጣ ውረዶችን እና ገጠመኞችን አስተናግዷል፡፡ (በመሳሪያ ከማስፈራራት እስከ መደብደብ ድረስ……) ይህ ሰው አርቲስት ተዘራ ለማ ነው፡፡

   ለ20 ዓመት የሰራበት የሹፍርና ሙያ ወደ ትወናው አለም እንዲገባ በር ከፍቶለታል፡፡ በቶም ቪዲዮ አማካኝነት ውሳኔ ፊልም ሲሰራ በሹፌርነት ሰርቶ ነበር፡፡ 500 ብር ቢነጋገርም ተባባሪነቱ እና ቅንነቱን ያየችው የቶም ቪዲዮ ባለቤት ገነት ተጨማሪ 500 ብር በማከል 1000ብር ተከፍሎታል፡፡ 

   እሱ ግን በክፍያው ደስተኛ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም የትወና ፍላጎቱ እና በካሜራ እይታ ውስጥ ለመግባት መሻቱ ስላልተሳካለት፡፡ ይሁንና በሁለተኛው ቀን ለዚሁ ለውሳኔ ፊልም ቀረፃ አለም ገና በሄደበት ጊዜ አለቃ ሆኖ የሚሰራበት አጭር ሲን (ትዕይንት) ይሰጠዋል፡፡ 

  በዚህ ጊዜ አርቲስት ተዘራ ደስታው ወደር አልነበረውም፡፡ ይህ ነበር እንግዲህ ፊልምን እና አርቲስት ተዘራን ያስተዋወቃቸው፡፡ የልጅነት ሀሳቡ እና ምኞቱ ሰመረ፡፡ “ወሳኔ ፊልም” የበኩር ስራው ሆነ ማለት ነው፡፡ ከዚያም ከኩርባው በስተጀርባ የተሰኘ ፊልም ላይ ተውኗል፡፡ አርቲስት ተዘራ ለማ እስካሁን ከ20 በላይ ፊልሞች ላይ የተለያዩ ገፀ ባህሪትን ተጫውቷል፡፡ እነርሱም ፡- 
         -  ውሳኔ   -  ከኩርባው በስተጀርባ  -  ፍቅር ባጋጣሚ  -  ታሰጨርሺኛለሽ
       -  ፍቅር በይሉኝታ  - አልወድሽም   - ወንድሜ ያቆብ  - ኢንጂነሩ
          - ጥቁር እና ነጭ   - ፍፃሜው       - ሀማርሻ         - ሰውዬው
          -  የፍቅር ቃል      - ቪዳ          - ባዶ ነበር        - ፀሀይ የወጣች ቀን
          -  ጣምራ           - የበኩር ልጅ   - እሷን ብዬ       - ጉደኛ ነች
      - ሰበበኛ       - ዘውድና ጎፈ ፤በመሰራት ላይ ያሉ እና በቅርብ የሚወጡ ፡- ታላቁ ሩጫ ፣ ሰንሰለት ፣ እስክትመጪ ልበድ እና ሌሎችም ይተቀሳሉ፡፡ በአለም ሲኒማ የታየ “የእኔ እውነት” የተሰኘ ትያትር ሰርቷል፡፡ ይህ ትያትር ሀገር ፍቅር ለመታየት ወረፋ እየጠበቀ ነው፡፡ የኩኩ ሰብስቤ ቻልኩበት ክሊፕ ላይም ተሳትፏል፡፡

   
    በ “በኩር ልጅ” ፊልምም ባሳየው የገፀ ባህሪ አጨዋወት በ9ኛው የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል ላይ “የአመቱ ምርጥ ተዋናይ” ተብሎ ተሸልሟል፡፡ በ”ፍቅር ቃል” ፊልም ላይም እንዲሁ ባሳየው ብቃት ከእነ ቤተሰቡ የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡ የከፍተኛ 18 ኪነት ቡድን ውስጥ ከተዋወቃት ባለቤቱ ተወዛዋዥ ፋንቱ አርጋው በ1977ዓ.ም ጋብቻውን የፈፀመው አርቲስት ተዘራ ለማ አራት ልጆችን አፍርቷል፡፡ ልጆቹም የእሱን ፈለግ የተከተሉ ሲሆን በተለይ ሰላም የተባለችው ልጁ ከ “ኩርባው በስተጀርባ” ፊልም ላይ አብረው ሰርተዋል፡፡


   በ1954ዓ.ም ፍቼ የተወለደው አርቲስት ተዘራ ለማ እድገቱ እዚሁ መዲናችን አዲስ አበባ ርቼ አካባቢ ነው፡፡ ይህ አርቲስት ወደ ጥበቡ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በፊልም ፣ በቴሌቭዥን ተከታታይ ድራማ ፣ በትያትር እና በልዩ ልዩ ማስታወቂያዎች ላይ ሰርቷል፡፡ በቀጣይም በአዳዲስ ስራዎቹ እንደምናየው ተስፋ አለኝ፡፡ ያሰብከው ይሳካ ፣ እድሜ ከጤና ጋር ይስጥህ ብያለሁ……

Wednesday, August 5, 2015

በትምህርት ቤት ስሟ እሌኒ አሁን ደግሞ ኩኩ .... ድምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ


   ለስለስ ባሉ ዜማዎቿ ትታወቃለች ፡፡ በልጅነቷ የወንድ የሴት ሳትል ከእሷ ድምፅ ጋር የሚሄዱትን ሙዚቃዎች ተጫውታለች፡፡ የእነ ሙሉቀን መለሰ ፣ ጌታቸው ካሳ ፣ ሽሽግ ቸኮል ፣ እታገኘሁ ሀይሌ እና ብዙነሽ በቀለን እና ሌሎችንም ሰርታለች፡፡ በጊዜው ቆየት ያሉትን የእንግሊዘኛ ሙዚቃዎች በማድመጥ እስከማንጎራጎርም ደርሳ ነበር፡፡ ተወዳጇ ድምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ፡፡

   ገና ከልጅነቷ ጀምሮ ት/ቤት ውስጥ በማንጎራጎር ነው ሙዚቃን የጀመረችው፡፡ በጊዜውም ሙሉቀንን ታደንቀው ስለነበረ ከአባቷ ከደጃዝማች ሰብስቤ ሽብሩ እየወሰደች (የእሳቸውን እና የሌሎችም) የግጥም ስራዎች ትሰጠው ነበር፡፡ ሙሉቀን መለሰም “ናኑ ናኑ ነይ” የተሰኘ አልበሙን ሲያወጣ በጊዜው የግጥም ደራሲዬ ኩኩ ሰብስቤ ናት እስከ ማለትም ደርሶ ነበር፡፡ 

   ድምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ የመጀመሪያ የመድረክ ስራዋን ያቀረበችው ከአይቤክስ እና ዋልያስ ባንድ ጋር በመሆን በሂልተን ሆቴል በተዘጋጀ የተማሪዎች ፓርቲ ላይ ነበር፡፡ በዚህ መድረክ ላይ የታጨችው ድምፃዊት ኩኩ ራስ ሆቴል በ300ብር ተቀጥራ ከመሀሙድ አህመድ ጋር በአይቤክስ ባንድ አጃቢነት በሳምንት ሁለት ቀን ትጫወት ነበር፡፡ በኋላ ላይም ወደ ሂልተን ሆቴል በመዛወር በ600ብር በየቀኑ ከዋልያስ ባንድ ጋር ትሰራ ነበር፡፡ በጊዮን ሆቴል ከሮሃ ባንድ ጋርም ትጫወት ነበር፡፡ በዚሁ ባንድ አጃቢነትም ከአለማየሁ እሸቴ ጋር “እንግዳዬ ነሽ” የተሰኘ የመጀመሪያ ስራዋን ለህዝብ አድርሳለች፡፡ ቀስ በቀስም ከሮሃ ባንድ ጋር ሶስት ያህል አልበሞችን አውጥታለች፡፡ 


    ከተለያዩ አንጋፋ ድምፃውያን ጋር በቅብብሎሽ የሰራቻቸውም በሮሃ ባንድ የተቀናበሩ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ከአይቤክስ ፣ ዋልያስ  ፣ ሮሃ ፣ ኢትዮ ስታር እና ኤክስፕረስ ባንዶች ጋር በተለያዩ ጊዜያት ሰርታለች፡፡ በተለይ በትዝታ ስራዎቿ የምትታወቀው ድምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ እስካሁን ስምንት ያህል አልበሞችን ሰርታለች፡፡ የመጨረሻ አልበሟ “ቻለኩበት” የተሰኘው ሲሆን በቀጣይም ሌላ አልበም ለመስራት እየተዘጋጀች ነው፡፡ በርከት ያሉ ነጠላ ዜማዎች ያሏት ሲሆን በቅርቡም “ሰበቤ” የተሰኘ ነጠላ ዜማዋን ለአድናቂዎቿ ጀባ ብላለች፡፡ እሳካሁን ባላት የካበተ ልምድ በሀገር ውስጥ እና በውጪ ኮንሰርቶቿን አቅርባለች፡፡ በጅቡቲ ጀምራ ሰነዓ፣ አቡዳቢ ፣ የመን ፣ ዱባይ ፣ አሜሪካ (በተለያዩ ከተሞች) እና በታላላቅ የአውሮፓ ከተሞች በመዘዋወር ሙዚቃዎቿን ለአድናቂዎቿ ተጫውታለች፡፡


     በ1980ዎቹ ወደ አሜሪካ የሄደችው ድምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ በዚያው ለ15 አመታት ያህል ቆይታለች፡፡ በዚያም አንድ ልጅ አፍርታለች፡፡ ልጇ ካሌብ የአሜካ ዜግነት ያለው ሲሆን በቅርቡም የከፍተኛ ትምህርቱን ለመከታተለ ወደ አሜሪካ ይጓዛል፡፡ ልጇ ከፍተኛ የኳስ ፍቅር እንዳለው የምትናገረው ኩኩ በአንድ ወቅትም እንግሊዝ ሀገር ወስዳ የማንቺስተር ስታዲየምን አስጎብኝታዋለች፡፡ድምፃዊት ኩኩ የትምህርት ቤት ስሟ እሌኒ ሲሆን 12ኛ ክፍልን ስትጨርስ እና ዘፋኝ ስትሆን ነው “ኩኩ” የሚል ስሟን በጋዜጣ ያሳወጀችው፡፡
  

    በሀገር ውስጥ እና በውጭ በርከት ያሉ የምሽት ክለቦች ውስጥ ሰርታለች፡፡ በሀገር ውስጥ ፍራንክ አዲስ ፣ እንዲጎ . ሀረር መሶብ ፣ ወረገኑ ፣ ሀርለም ጃዝ ፣ ጃዝ አምባ ፣ በአሜሪካ ደግሞ ከቴዲ ማክ ጋር በመስከረም ሬስቶራንት ስራዎቿን ታቀርብ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ “Club H2O” እና ማማስ ኪቺን ሙዚቃዎቿን ትጫወታለች፡፡ እኔ በዚሁ ላብቃ ቀሪውን እናንተ ጨምሩበት ……  እድሜ እና ጤና ለተወዳጇ እና አንጋፋዋ ድምፃዊ ኩኩ ስብስቤ ተመኘሁ፡፡

Sunday, July 19, 2015

ቀራፂ፣ አዝማሪ፣ ባለቅኔ ፣ ነጋዴ፣ የመኪና ጠጋኝና ሹፌር …. ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ



   የመጀመሪያው ሙዚቃን በሸክላ ያስቀረፁ እና ህጋዊ መንጃ ፍቃድ በመያዝ (ከጀርመን ሀገር) የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መኪና አሽከርካሪ /ሹፌር/ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ (Recording History) በሸክላ የተቀረፀ የመጀመሪያው ዜማ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ስራዋች ሲሆኑ ዘመኑም በአጤ ምኒልክ ዘመነ መንግስረት ነበር( እ.ኤ.አ 1910) ፡፡



  በ1900ዓ.ም ሙሴ ሆልስ የተባሉ ጀርመናዊ በኢትዮጵያ ለብዙ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ አፄ ምኒልክን በተሰናበቱበት ጊዜ ጀርመን ሀገር ወስደው የሚያስተምሯቸው ሶስት ወጣቶች እንዲሰጧቸው ስለ ጠየቋቸው እና ነጋድራስ ተሰማ እሸቴም በጥሩ ሰዓሊነታቸው በቤተ መንግስቱ ስለ ታወቁ “ያ ተሰማ እሸቴ እጁ ብልህ ነውና መኪና መንዳት እና መጠገን እንዲማር እሱ ይኺድ” ብለው አፄ ምኒልክ ስለ ወሰኑ ወደ ጀርመን አገር ሄደው ለሁለት አመት ተኩል ያህል የአውቶሞቢልን አሰራር ለመማር ችለዋል፡፡



  ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ መስንቆ መምታት እና ዜማ ካባታቸው ተምረው ስለነበር ወደ ጀርመን ሄደው በቆዩበት ጊዜ የተላኩበትን የሹፌርነት እና የመካኒክነት ትምህርት አጠናቀው አጥጋቢ ውጤት ከማምጣታቸውም በላይ የመጀመሪያውን የአማርኛ ዜማ በሸክላ ለማስቀረፅ በቅተዋል፡፡ በጀርመን ቆይታቸው ወቅት “ሂዝ ማስተርስ ቮይስ” የተባለው የጀርመን የሙዚቃ ድርጅት ጠይቋቸው የኢትዮጵያ መዲና እና ዘለሰኛ ዜማዎችን በ17 አይነት ስልት እየተጫወቱ ተቀርፀዋል፡፡ ኩባንያው የተሰማ እሸቴን ዜማዎች በ17 ሸክላዎች የቀረፀ ሲሆን ለዜማው ባለቤት የድካም ዋጋ እንዲሆን በወቅቱ 17ሺህ የጀርመን ማርክ ከፍሏቸዋል፡፡

   በዘመኑ ብቻ ሳይሆን በሀገራችን አሁንም እነዚህ የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ብርቅዬ ሸክላዎች በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ውስጥ ተሰብስበው ይገኛሉ፡፡ እነዚህ በተቋሙ እጅ ያሉት 16 ያህል ሸክላዎች እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ዜማዎችን የያዙ ሲሆን በአጠቃላይ 32 ዜማዎች ተቀርፀውባቸዋል፡፡ እያንዳንዱ የሸክላው ገፅ ላይ A ወይም B ተብሎ ተሰይሟል፡፡የዜማው ስምም ተፅፎበታል፡፡ የዜማው ባለቤት ተሰማ እሸቴ ስም አለ ፤ ሸክላው ጀርመን ሀገር መሰራቱ እንዲሁም የሸክላው ቁጥር ተጠቅሷል፡፡

  ሌሎች የአማርኛ ዲስኮች የተቀረፁት ጠላት ኢትዮጵያ ሊገባ ሁለት አመት ያህል ሲቀር ነው፤ የእነ ፈረደ ጎላ ፣ ንጋቷ ከልካይ እና ተሻለ መንግስቱ የዜማ ሸክላዎች ብቅ ያሉት፡፡ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን የነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ሸክላዎች ከ20 አመት በላይ አቅም ባላቸው ቤተሰቦች ዘንድ በብቸኝነት በግራማፎን ሲደመጡ ቆይተዋል፡፡ ነጋድራስ ተሰማ በዘፈኖቻቸው የአገርና የባንዲራ ፍቅርን ፣ የተቃራኒ ፆታን ፍቅር ፣ ስልጣንን ፣ ጀግንነትን አውድሰውበታል፡፡ ነጋድራስ ተሰማ፣ የመኪና ሹፍርናና የመካኒክነት ሙያን እንዲሰለጥኑ በአፄ ምኒልክ ተመርጠው ወደ ጀርመን አገር በተላኩ ጊዜ ከተላኩበት ሙያ ውጪ በስዕል ፣ በቅርፃ ቅርፅና በሙዚቃ ሙያ በርካታ ስራዎችን ሲሰሩ ቆይተው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡
  ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ከአባታቸው ከአቶ እሸቴ ጉቤ እና ከእናታቸው ከእማሆይ ወለተየስ ሀብቱ ሀምሌ 20 ቀን 1869ዓ.ም ምንጃር ቀርሾ አጥር በተባለው ስፍራ ነው የተወለዱት ፡፡ አባታቸው አቶ እሸቴ የራስ መኮንን ጭፍራ ስለ ነበሩና መስንቆም ስለሚጫወቱ ራስ መኮንንን ተከትለው ወደ ሐረር ሲሄዱ ነጋድራስንም በህፃንነታቸው ይዘዋቸው በመሄዳቸው ያደጉት እና አማርኛ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በሐረር ነው፡፡ አባታቸው አቶ እሸቴ ሐረር እንዳሉ በመሞታቸው ነጋድራስ ተሰማ በወጣትነት ዕድሜያቸው  ዳግማዊ አፄ ምንሊክን ተከትለው ወደ አዲስ አበባ መጡ፡፡ እኚህ ሰው የኢትዮጵያ ስፖርት ፈርጥ የሆኑት የአቶ ይድነቃቸው አባት ናቸው፡፡


     የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ቀራፂ፣ ፎቶግራፈር፣ አዝማሪ፣ ባለቅኔ ፣ ሰዓሊ ፣ የፖለቲካ ሰው ፣ ነጋዴና የመኪና ጠጋኝና ሹፌር የሆኑት ነጋድራስ ተሰማ ፣ በዘመናቸው በርካታ አዳዲስ ነገሮችን ለመጀመር ከፍተኛ ፍላጎትና ጉጉት የነበራቸው ሰው ነበሩ፡፡ ከዘፈን ችሎታቸው በተጨማሪ የተለያዩ ስዕሎችንና ቅርፃቅርፆችን በመስራት ለአዳዲስ ሙያዎች ፈር ቀዳጅ እንደሆኑም ይነገራል፡፡ ሃሳባቸውን በነፃነት ለመግለፅና ፊት ለፊት ለመጋፈጥ ደፋር ነበሩ የሚባሉት ነጋድራስ ተሰማ ፣ የቅርፃ ቅርፅ ስራዎች ፣ ስዕሎችና ዘፈን ሀጢያትና ክፉ ስራ እንደሆነ ይታመን በነበረበት በዚያ ዘመን ፣ የፍቅረኛቸውን ምስል በቅርፅ ሠርተውና የተለያዩ የፍቅር ዜማዎችን በማዜም ፣ ዘመናቸውን የቀደሙና ሃሳባቸውን በነፃነት ለመግለፅ የደፈሩ ሰው ናቸው፡፡

Wednesday, July 1, 2015

ድምፃዊ ፀዳለ ገብረማሪያም ማን ናት ... ?


    ድምፃዊት ፀዳለ ከድምፃዊነቷ ባሻገር ጥሩ ተወዛዋዥ ናት፡፡ ቫልስ እና ታንጎ የመሳሰሉትን ስትጫወት ደግሞ ከአይን ያውጣሽ ታስብላለች ይላሉ በቅርብ የሚያውቋት፡፡ የሁለት ወንድ ልጆችም እናት ናት፡፡

  ከሀረር ወደ አዲስ አበባ መጥታ አክስቷ ጋር ያደገችው ፀዳለ በአክስቷ አማካኝነት ወ/ሮ አሰገደች አላመራው ሆቴል(ፓትሪስ ሉሙምባ ምሽት ክበብ) ገባች፡፡ በዚሁ ምሽት ክበብ ውዝዋዜ ትሰራ የነበረችው ፀዳለ የተለያዩ ድምፃውያን ስራቸውን ሲያቀርቡ በመስማት እሷም ለራሷ  ታንጎራጉር ጀመር፡፡ ከዚያም በጓደኞቿ አነሳሽነት ወደ ሙዚቃው አለም ገባች፡፡ በወቅቱም የብዙነሽ በቀለን “የሚያስለቅስ ፍቅር” በመጫወት ነው የተቀጠረችው፡፡

  በፓትሪስ ሉሙምባ ቆይታዋ በዳንስ ፣ ውዝዋዜ እና ድምፃዊነት እየሰራች 100ብርም ይከፈላት ነበር፡፡ በፓትሪስ ሉሙምባ ምሽት ክበብ ስትጫወት በተመለከቷት ሻምበል ወንድሙ ዘውዴ እና ድምፃዊ ታምራት ሞላ አማካኝነት ምድር ጦር ኦርኬስትራ በ1958ዓ.ም በሲቪል የዘመናዊ ሙዚቃ ድምፃዊነት ተቀጠረች፡፡ በምድር ጦርም የራሷን የመጀመሪያ ስራ “ካለህበት መጣሁ” የተሰኘ ሙዚቃን ተጫውታለች፡፡ ቀስ በቀስም በርከት ያሉ የአማርኛ እና የሀረር ኦሮምኛ/ቆቱኛ/ ሙዚቃዎችን በግል እና በጋራ አቀንቅናለች፡፡
 
  በግሏ ፡- ካለህበት መጣሁ ፣ ቀለበቴን እንካ ፣ ፍቅር ነው፣ መች ቀረሁ፣ ጨክኜ ፣ የሴቶች ህሊና ፣ አጀቢቱ ፣ ልጆቼን አደራ እና ሌሎችንም ሰርታለች፡፡ በተለይ “ልጆቼን አደራ” የተሰኘው ስራዋ ከራሷ ህይወት ጋር የተገናኘ ሲሆን የግጥሙ ደራሲ ደግሞ ሲራክ ታደሰ ነው፡፡ ከባሏ ጋር በተለያየችበት ወቅት የተጫወተችው ይህ ስራ በግጥሙ ውስጥ የእሷን ህይወት ስለሚያሳይ የተወሰኑትን የዘፈኑን ግጥሞች በጥቂቱ እነሆ፡-
             “መሰረት የሌለው ፍቅርና ቤት
             አይቀርም መፍረሱ ዛሬ አየሁት
             ትቀበለኝ እንደሆን ሀሳቤን
             አደራ እልሃለሁ ልጆቼን፡፡
             ሳምንህ የከዳኸኝ አንተ የጊዜ ሰው
             ትዳራችን ጠፋ ቤታችን ዘጋህው
             እኛም እንለያይ ይበተን ሀብታችን
             እስኪ ለማን ይቅሩ ህፃን ልጆቻችን……”
በጋራ(ከሃብታሙ ሽፈራው) ጋር ፡- ውይይት ፣ ሰመለሌ እና ሌሎች ኦሮሚኛ ዘፈኖችን ተጫውታለች፡፡

    በምድር ጦር ቆይታዋ ከእነ ታምራት ሞላ ፣ አባይ በለጠ ፣ ሀብታሙ ሽፈራው ፣ ጌታቸው አስፋው ፣ ጥላዬ ጨዋቃ እና ሌሎችም ጋር አብራ ሰርታለች፡፡ ከምድር ጦር ኦርኬስትራ ጋርም በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በመዘዋወርም ሙዚቃዎቿን አቅርባለች፡፡ ምድር ጦር 270 ብር ይከፈላት ነበር፡፡ በኋላም ዕድገት አግኝታ በ400 ብር ወደ ማዕከላዊ ዕዝ ተዛውራለች፡፡ በዚያ ቆይታዋም ከእነ ብዙነሽ በቀለ ፣ መንበረ ፣  ዘመነ መለሰ እና ሌሎችም ጋር ተጫውታለች፡፡

   ድምፃዊ ፀዳለ ገብረማሪያም ከ1958 - 81 ዓ.ም በምድር ጦር ፣ ከ1981 - 85 ዓ.ም በማዕከላዊ ዕዝ ፣ከ1985 - 2000 ደግሞ በራስ ትያትር በዘመናዊ ሙዚቃ ድምፃዊነት ሰርታለች፡፡ በዚሁ አመትም ጡረታ ወጥታለች፡፡ብዙ ስራዎቿን ግጥም እና ዜማ ይሰሩላት የነበሩት ምድር ጦር በነበረችበት ጊዜ - (ኮለኔል ለማ ደምሰው ፣ ተሾመ ሲሳይ እና ወንድሙ ዘውዴ) ሲሆኑ ማዕከላዊ ዕዝ - (አየለ ማሞ) ራስ ትያትር ደግሞ ሱራፌል አበበ ናቸው፡፡

  ነሀሴ 5,1938 ዓ.ም ሀረር የተወለደችው ድምፃዊት ፀዳለ ገብረማሪያም አሁን በህመም ምክንያት ቤት ውላለች፡፡ ሰርጋችንን ያሞቅንባቸው ፣ ብሶታችንን የረሳንባቸው ፣ ወደ ኋላ በምልሰት ትዝታዎቻችንን ያስታወስንባቸው ፣ አርቲስቶቻችን የህዝብ ሀብት በመሆናቸው ክብር ልንሰጣቸው ይገባል፡፡በችግራቸው ጊዜም ልናስታውሳቸው እና ልንደርስላቸው ያስፈልጋል፡፡

Monday, June 22, 2015

እነሆ ስጦታ……… ከሸዋንዳኝ ሀይሉ !!!



      በእነ ለንደን ቢት ፣ ቦብ ማርሌ እና አርኬሊ ሙዚቃን አሀዱ ያለው አርቲስት ሸዋንዳኝ የአማርኛ ሙዚቃ ዳዴው የእነ ግርማ በየነ ፣ ጌታቸው ካሳ እና ዳዊት መለሰ ስራዎች ነበሩ፡፡ ከዚያም በሳቂልኝ እና ስጦታሽ አልበሞቹ ከወዳጅ እና አድናቂዎቹ ጋር ተገኛኝቷል፡፡ እ.ኤ.አ 2004 በኮራ የሙዚቃ ሽልማት በወንዶች ከምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያን ወክሎ የ3ኝነት ደረጃን አግኝቷል፡፡

   ሙዚቃን ገና የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ በሴንት ጆሴፍ ት/ቤት ነበር የጀመረው፡፡ በዚህ ት/ቤትም የተለያዩ የእንግሊዘኛ ዘፈኖችን በመጫወት ለሁለት አመታት ያህል ሰርቷል፡፡ ከትምህርቱ ጎን ለጎን ሙዚቃን ይጫወት የነበረው ሸዋንዳኝ ሀይሉ ከአባቱ ጠንካራ ተቃውሞ ገጥሞት እስከ መኳረፍ ደርሶ ነበር፡፡ በዚህም ከቴዲ አፍሮ ጋር ቤት ተከራይተው ለሶስት አመት ያህል አብረው ኖረዋል፡፡ ለዚህም ይመስላል ሸዋንዳኝ “ስቅ አለኝ” እና “ስጦታሽ” የተሰኙትን አልበሞቹን ሲያወጣ ቴዲ አፍሮ በርከት ያሉ ግጥም እና ዜማዎችን ሰጥቶታል፡፡
  

  “ስቅ አለኝ” አልበሙ ከአባቱ ጋር ያስታረቀው ሲሆን እሳቸውም ደውለው አበረታተውታል፡፡ ከዚህ አልበም በኋላም ግብፅ ፣ ደቡብ አፍሪካ ፣ ዱባይ ፣ አቡዳቢ ፣ ባህሬን ፣ እስራኤል ፣ አውሮፓ እና አሜሪካ ኮንሰርቶችን አቅርቧል፡፡ ቡፌ ድላጋር ፣ የቀድሞው ላየን ክለብ ፣ ኮፊ ሀውስ ፣ ሂልተን ፣ ሽራተን ፣ ኢሉዥን እና ሚሞ ክለቦች ሰርቷል፡፡ በኋላ ላይም እሱ እና ቴዲ አፍሮ ላየን ክለብ ይዘው በጋራ ይሰሩበት ነበር፡፡ በተጨማሪም በ1999ዓ.ም “ፋራናይት” የተሰኘ ክለብ ከጓደኞቹ ጋር ከፍቶ ነበር፡፡ በዚህም እዮብ መኮንን ፣ ፀደኒያ ገ/ማርቆስ ፣ ጆኒ ራጋ እና ሌሎችም ስራቸውን ያቀርቡበት ነበር ምንም እንኳን አሁን አገልግሎት ላይ ባይሆንም፡፡
  

  በሀገራችን ታዋቂ ከሆኑት አይቤክስ ፣ ኢትዮ ስታር ፣ ኤክስፕረስ ፣ መዲና ፣ አዲሰ ፣ ሌቫንስ እና አፍሮ ሳውንድ ባንዶች ጋርም ሰርቷል፡፡ “አፍሮ ሳውንድ” ቴዲ አፍሮ ፣ ግሩም መዝሙር እና ሸዋንዳኝ ሀይሉ በጋራ የመሰረቱት ባንድ ነው፡፡ ስያሜውን ያወጣው ሸዋንዳኝ ሀይሉ ሲሆን ባንዱ ለ10 ዓመት ያህል በጥሩ ሁኔታ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በጊዜውም እነ ኤልያስ መልካ ፣ ዳግማዊ አሊ ፣ ዳንኤል ክንደያ ፣ አሸናፊ አሊ እና ሁንአንተን የመሳሰሉ ታዋቂ የሙዚቃ ሰዎችን አፍርቷል፡፡ 


  አርቲስት ሸዋንዳኝ ሀይሉ “ስቅ አለኝ” የተሰኘ አልበሙን ከሰራ ከ8 ዓመት በኋላ “ስጦታሽ” የተሰኘ ሁለተኛ አልበሙን ለአድናቂዎቹ  ጀባ ብሏል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ስራ ገና ሳይጀመር ቅድመ ክፍያ (ቀብድ) የኤሌክትራ ባለቤት አቶ ተሾመ በራሳቸው ፍላጎት ሰጥተውት የተሰራ አልበም ነው፡፡ አልበሙም 6 ዓመታትን ወስዷል፡፡


   እዚሁ አዲስ አበባ መስቀል ፍላወር የተወለደው አርቲስት ሸዋንዳኝ ሀይሉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ምስክያዞና ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሴንት ጆሴፍ እንዲሁም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተከታትሏል፡፡ በዩኒቨርስቲ ቆይታ የመጀመሪያ አመት ኬሚስትሪን ቢመርጥም ከአንድ አመት በኋላ ወደ ማኔጅመት በመቀየር ለሶስት አመት ተምሮ ሳይጨርስ “ዊዝድሮዋል” አድርጓል፡፡ አሁን ሙሉ ጊዜውን ለሙዚቃ ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ከሙዚቃው ውጪም ፊልም እና ግራውንድ ቴንስ ይወዳል፡፡ እግር ኳስ ከሀገር ውስጥ የቅድስ ጊዮርጊስ ፤ ከውጪ ደግሞ የብራዚል ብሄራዊ ቡድን ደጋፊ ነው፡፡ እኔ ይህን አልኩ እናንተ ደግሞ ቀሪውን ጨምሩበት…….