Wednesday, October 12, 2022
የመስቀል ወፍ እና የአደይ አበባ ...
የመስቀል ወፍን ለአይን ያበቃት የመስከረም ውበት ነው፡፡ የመስከረም ውበት ምስጢር አበቦች ናቸው፡፡ መስከረም ምድር በአበቦች ቀለም አዲስ ልብስ የምትለብስበት ወር ነው፡፡ አደይም እንደመስቀል ወፍ የመስከረም ጌጥ ናት፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው የአደይ አበባ ዝርያ የዕድገት ጊዜውን ሲጨርስ የሚሞት ሲሆን ፍሬው ብቻ መሬት ውስጥ ተቀብሮ የሚቀር ነው፡፡ የሌሎች ግን ግንዳቸው ወይም ስራቸው ተርፎ ይቀራል ፡፡
ዋናው የአበባ ጊዜ በመስከረም ወቅት የሆነበት ምክንያት ግን የአበባ ማውጣት ዑደታቸው መስከረም ስለሆነ እና የዚህ የአደይ አበባ ዝርያ ፍሬ አፍርቶ ደርቆ ተክሉ ከሞተ በኋላ ፍሬው መሬት ተቀብሮ ከስድስት ወር እስከ ሁለት አመት ሊቆይ ስለሚችል ነው፡፡ ይህ ወቅትም የሽልብታ ጊዜ /የዶርማንሲ ፔሬድ/ ይባላል፡፡ በነዚህ ጊዜያት ውስጥ ምቹ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ብቻ ፍሬው እንደገና እንዲበቅል ያደርጋል ማለት ነው ፡፡ ይህም ማለት ለዕፅዋት ብቅለት አስፈላጊ የሆኑት እርጥበት፣ አየርና ሙቀት በበቂ ሁኔታ ሲስተካከል ማለት ነው፡፡ ለማበብ ደግሞ ክረምቱ መውጣት አለበት፡፡ ምንም እንኳን ሐምሌና ነሐሴ ቢበቅልም መስከረም ሳይጠባ አያብብም፡፡
እንደሚታወቀው የዝናብም ይሁን የመስኖ ውሃ ካገኙ በርካታ የሣርና የተክል ዓይነቶች ይበቅላሉ፣ ያብባሉ፣ ያፈራሉ፡፡ የአደይ አበባ አስገራሚው ነገር የቱንም ያክል በበጋ ዝናብ ቢያገኝ ወይም በየትኛውም የመስኖ እርሻ ባለበት አካባቢ አይበቅልም፡፡ ሐምሌ ከገባ ጀምሮ ግን በየእርሻውና በየዳገቱ በተለይ ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነፃ የሆኑ ቦታዎች ሁሉ መብቀል ይጀምራል፡፡ አበባው አንዴ ካበበ በኋላ እንደፈካ ምድርን አስውቦ የሚቆየው ለረጅም ጊዜ አይደለም ፡፡ ቢበዛ ለሶስት ወራት ብቻ ጋራና ሸንተረሩን፤ ሜዳና ተራራውን በተስፋ ሰጪው ቢጫማ ቀለም አስውቦ ይቆይና ይጠፋል ፡፡ ይህም ሌላው የአደይ አበቦች መለያ ባህሪ ነው ፡፡
የመስቀል ወፍ እና የአደይ አበባ
ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ
ማን ያውቃል...? ይላል ባለቅኔ መንግሥቱ ለማ
"የመስቀል ወፎች ለረጅም ጊዜ ሳይታዩ ቆይተው መስከረም ወር ላይ የሚከሰቱ ዓመታዊ እንግዶች ሳይሆኑ አብረውን ቆይተው በተፈጥሮ ሂደት የላባቸው ቀለም የሚቀየር ቤተኛ አእዋፋት እንደሆኑ በዘርፉ ጥናት እና ምርምር ያደረጉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ ፡፡ እንደ ባለሙያዎቹ ገለፃ የመስቀል ወፍ በተለይ በመስከረም ወር አጋማሽና ቀደም ብለው በጥቁር ፡ ቢጫ ፡ ነጭ እና ብሩህ ደማቅ ቀለም አሸብርቀው የሚገለጡ እንጂ ጠፍተው የሚከሰቱ አይደሉም።
እንደየቋንቋውና እንደየአካባቢው እነዚህ ወፎች የየራሳቸው ስያሜና መጠሪያም ሊኖራቸው ይችላል። የመስቀል ወፍ ተብለው የሚታወቁት እነዚህ አእዋፋት ከኢትዮጵያ ባሻገር በኬንያ፣ ሱዳን ፣ በኡጋንዳ ፣ በታንዛንያ ፣ ሴኔጋል ፣ ደቡብ አፍሪካና ሌሎች ሀገራትም ይገኛሉ።
Saturday, October 1, 2022
እንኳን ለኢሬቻ በዓል በሰላም አደረሳችሁ … !!!
በየዓመቱ መስከረም ወር ላይ የኢሬቻ በዓል በደመቀ ስነ ስርዓት ይከበራል፡፡ ይህ ክብረ በዓል በኦሮሚያ ክልላዊ አስተዳደር ትኩረት ከተሰጣቸው ህዝባዊ በዓላት አንዱ ሲሆን በዓሉ የምስጋና፣ የሰላም፣ ፍቅርና አንድነት መገለጫ ነው። የኢሬቻ በዓል አንዱ የገዳ ስርዓት መገለጫ ሆኖም በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳደስ ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡
ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ በህብረት ወደ ተራራ እና መልካ ወይም በወንዝ ዳር ወርዶ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት ስርዓት/በዓል ነው፡፡ ይህ በዓል በተለያዩ ቦታዎች ቢካሄዱም ዋና ዋናዎ በሁለት ይከፈላሉ፡፡ እነርሱም “ኢሬቻ ቱሉ” እና “ኢሬቻ መልካ” በመባል ይታወቃሉ፡፡
የበጋ ወቅት አልፎ
በበልግ ወቅት ላይ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል “ኢሬቻ ቱሉ” ይባላል፡፡ ይህም በበጋ ወቅት ሰው እና እንሰሳት በድርቅ ሲጠቁ ወይም
ሲጎዱ ወደ ተራራ በመውጣት የበልግ ዝናብ እንዲዘንብላቸው ፈጣሪን የሚለማመኑበት ስርዓት ነው፡፡
ክረምት አልፎ በፀደይ
መግቢያ ወቅት ላይ በቢሾፍቱ ከተማ በድምቀት የሚከበረው ደግሞ “ኢሬቻ መልካ” በዓል ይባላል፡፡ ይህ በዓል ከክረምት ወደ በጋ በሰላም
ስላሸጋገራቸው እርጥብ ሳር እና አደይ አበባ በመያዝ ወንዝ ዳር ወጥተው ፈጣሪን የሚያመሰግኑበት ስርዓት ነው፡፡ በዚህ በዓል ላይም
ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ በርካታ ሰዎች ይታደማሉ፡፡
Subscribe to:
Posts (Atom)