አርቲስት ካሳዬ ገበየሁ ኮረሪማ የኪነ ጥበብ ጅማሮው በአርሲ ባህል ኪነት ቡድን ነው፡፡ አርቲስቱ ከታዳጊነቱ ጀምሮ በባህል ውዝዋዜ ፣ በድምፃዊነት ፣ ተዋናይነት ፣ መድረክ ዝግጅት እና በድርሰት ሙያ ተሳትፏል፡፡ በራስ ትያትር ፣ ህፃናት እና ወጣቶች ፣ ሀገር ፍቅር እና ትያትር እና ባህል አዳራሽ (ማዘጋጃ ቤት) ከባለሙያነት እስከ አመራርነት ባሉት ኃላፊነቶች ሰርቷል፡፡
ከትውልድ ቅዬው በ1980ዎቹ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት
በጊዜው በነበሩ ኪነቶች ውስጥም ይሰራ ነበር፡፡ ከዚያም በአዲስ አበባ ትያትር እና ባህል አዳራሽ በባህል ተወዛዋዥነት ተቀጥሮ ስራን
አሀዱ ብሎ ጀመረ፡፡ ከዚያ በኋላ በራስ ትያትር - በድምፃዊነት እና በትወና፤ በራስ ትያትር - በድምፃዊነት እና ትወና ፤ በህፃናት
እና ወጣቶች - በስቴጅ ማኔጀርነት እንዲሁም በሀገር ፍቅር - ለ3
አመት ያህል በስራ አስኪያጅነት አገልግሏል፡፡
አርቲስት ካሳዬ ገበየሁ በተለያዩ የሬዲዮ እና የቴሌቭዥን ድራማዎች ላይ ተሳትፏል፡፡ በብዙዎች ዘንድ “የቀን ቅኝት” በተሰኘው የሬዲዮ ድራማ ላይ በሚጫወተው የ “ደምለው” ገፀ ባህሪ ተወዳጅነትን አትርፏል፡፡ ከገፀ ባህሪ ባለቤቱ “አንጓች” - አስቴር በዳኔ ጋር የነበራቸው መናበብ እና ብቃትም በአድማጭ ዘንድ እውቅናን እንዲያገኙ አድርጓቸዋል፡፡ ከሬዲዮ ድራማ በሻገርም “ማረፊያ ያጣች ወፍ”፣ “ኖላዊ” ፣ “መስኮት” እና ሌሎች የቴሌቭዥን ድራማዎች ላይ ሰርቷል፡፡ “ከዘራው” የተሰኘ ፊልም በመድረስም ለተመልካች አቅርቧል፡፡
በትያትር ረገድም “ጤና ያጣ
ፍቅር” ፣ “የምሽት ፍቅረኞች” ፣ “ሮሚዮ እና ጁሌት” ፣ “ደመና” እና የተለያዩ ሙዚቃዊ ተውኔቶች ላይ
በማዘጋጀት እና በመተወን ተሳትፏል፡፡ አሁን ደግሞ ስራን አሀዱ ወደአለበት ትያትር ቤት ተመልሶ የአዲስ አበባ ትያትር እና
ባህል አዳራሽ(ማዘጋጃ ቤት)ን በስራ አስኪያጅነት እያገለገለ ይገኛል፡፡ ስለ አርቲስት ካሳዬ ገበየሁ እኔ ከብዙ በጥቂቱ ይህንን አጋርቻችኋለሁ፤
በተረፈ እናንተ ጨምሩበት፡፡