የፊልም አዘጋጅ፣ ተዋናይ፣ ፀሃፊ እና መምህር ነው፡፡ ትምህርቱን በሀገር ውስጥ እና በውጪ ተምሯል፡፡ 12ኛ ክፍልን ጨርሶ የሙዚቃ ትምህርትን የተከታተለ ሲሆን በጊዜው ሜጀሩን “ባሱን” እና ማይነሩን ፒያኖ በማድረግ በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቋል፡፡ በተለይ “ባሱን” በተባለው የሙዚቃ መሳሪያ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው እንደሆነም ይነገርለታል፤ ሁለገብ የፊልም ባለሙያ ብርሃኑ ሽብሩ፡፡
በሙዚቃ ትምህርት በከፍተኛ ማዕረግ ከተመረቀ በኋላም ነፃ የትምህርት እድል አግኝቶ ወደ ቀድሞዋ ሶቬት ህብረት በማቅናት
ለአንድ አመት ቋንቋ እና ስነ ፅሁፍ ተምሯል፡፡ ከዚያም የሲኒማ፣ የትያትር እና የቴሌቭዥን ስራዎች ዩኒቨርስቲ ውስጥ ለአንድ
አመት ትያትር አመራር /ዳይሬክቲንግ/ እና ትወና አጥንቷል፡፡ በማስከተልም በፊልም ፋካሊቲ(ትምህርት ክፍል) የልብ ወለድ ፊልም
ትወና ጥበብን ለ5 አመት ተምሯል፡፡ በትምህርት ቆይታውም 9 ያህል ፊልሞችን እና 6 ያህል ተውኔቶችን ከተለያዩ ሀገራት
የትምህርት አጋሮቹ እና የፊልም ባለሙያዎች ጋር ሰርቷል፡፡ ለአብነትም የሰው ያለህ፣ የመጨረሻው ውይይት፣ ፀሀይ ስትጠልቅ፣
የትም ምንም አለ(Nothing is everywhere) ፣ የቀረ መንገደኛ እና ነፍሰ ገዳይ ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡
ትምህርቱን ጨርሶ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላም የኢትዮጵያ ፊልም ኮርፖሬሽንን በመቀላቀል የተለያዩ ስራዎችን ሰርቷል፡፡ በአጠቃላይ በግል እና በጋራ 70 የሚደርሱ ሰራዎችን ሰርቷል፡፡ በተለያየ መንገድ ከተሳተፈባቸው የፊልም ፣ ድራማ እና ቪዲዮ ስራዎቹ መካከል፡-
- በህይወት ዙሪያ - ኑረት - ግልፅ የመሆን ጊዜ
- ዋስትና - የሰላም ባዳነት - የሞት
ፍቅር - ማናት
- ኮንሶ ካራት - የጊዜያችን ሰዎች - ውስጠት
- ንቅዘት - ጎዳና - ሰባራ መስተዋት
- የሞት ሸለቆ - የወፍ ጎጆ - ሀድጊ የትግሪኛ የቴሌቭዥን ድራማ(ዳይሬክት በማድረግ)
- ገበና ቁጥር 1 (በትወና) የመሳሰሉትን ማነሳሳት ይቻላል፡፡ በተለይ ገበና ቁጥር 1 የፍሰሃ ገፀ ባህሪን ወክሎ ከጀማነሽ ሰለሞን (በድራማ ገፀ ባህሪዋ - ማርታ ጋር) ባሳየው የትወና ብቃት በብዙዎች ዘንድ ይታወቃል፡፡ በዚህ የቴሌቭዥን ድራማ ምክንያት በተለያየ ጊዜ ያገኙትን 12ሺ አድናቂዎቹን ስም የመዘገበ ሲሆን በግለሰቦቹ ስም በአንድ ሰዓሊና ቀራፂ እመቤት በለጠ አማካኝነት ስዕል ተሰርቶ ለኤግዚብሽን ቀርቦም ነበር፡፡ ከዳይሬክቲንግ ፣ ትወና እና መምህርነት ባሻገር የተለያየ አርቲክል እና ግጥሞችን በመፃፍም ይታወቃል፡፡ የጉማ ፊልም ሽልማት ላይም በማማከር እና በዳኝነት ሰርቷል፡፡
በአጠቃላይ በተማረው ትምህርት
እና ባገኘው ልምድ የሀገራችንን የፊልም ኢንዱስትሪ ለማሳደግ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ ስለ ሁለገቡ የፊልም ባለሙያ
ብርሃኑ ሽብሩ ከብዙ በጥቂቱ እኔ ይህንን አልኩ ፣ እናንተ ደግሞ
ያላችሁን ሀሳብ እና አስተያየት አጋሩኝ፡፡ ለእንግዳዬ ብርሃኑ ሽብሩ እድሜ ከጤናና ስራን ከስኬት ጋር እመኛለሁ!!!