በውበቷና ቁመናዋ ዓይነ ግቡ የሆነችው ይህች ጉብል፤ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት መድረክ በአካልም በሙያም አድጋ ታላቅ የጥበብ ሰው ለመሆን በቅታለች፡፡ አርቲስቷ ሁለገብ የጥበብ ሰው ስትሆን እጅግ በርካታ አጫጭርና ረጃጅም ቴአትሮችን በመድረክ ተጫውታለች። በግሏ እና ከሌሎች ጋር በማዜም በሸክላ ያስቀረፀቻቸው የሀገር እና የፍቅር እንዲሁም የትዝታ ዜማዎቿ ዘመን ተሻጋሪነታቸውን ያስመሰከሩ ናቸው። ዛሬም ቀልብ ይስባሉ፣ ልብ ያሸፍታሉ። የሀገር ፍቅሯ
ንግስት አርቲስት አሰለፈች አሽኔ፡፡
አሰለፈች ከጓደኛዋ
ጌጤነሽ ክብረት ጋር በ1968ዓ.ም አካባቢ “ሸገኔዎች” የተሰኘ የሙዚቃ ሸክላ አሳትማም ነበር ፡፡ “እየው ድማሙ” ፣ “መቼ ነው” ፣ “ዛሬ ነው” ፣ “ፍቅር እንደገና” ፣ “ሠላም ለምወድህ ” ፣ “እንዲህም እንዲህም” ፣ “የንብ አውራ መሳይ” ፣ “ሳብዬ” የሚሉ ዜማዎቿ ለአብነት ይጠቀሳሉ። “ማንጠግቦሽ” የተሰኘ ሙዚቃዊ ድራማም አላት፡፡ ከጥላሁን ገሠሠ፣ ከፍሬው ኃይሉ ከአሰፋ አባተ ፣ ከተማ መኮንን ፣ አሰፋ ሀይሌ ፣ ታጠቅ ገብረወልድ እና ከሌሎችም ታዋቂ ዘፋኞች ጋር በህብረት የዘፈነቻቸው በርካታ ስራዎች አሏት። በውዝዋዜ ረገድም ከነ ሙናዬ መንበሩ፣ ዘነበች ታደሰ እና ሌሎችም ጋር የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት መድረክን አድምቃለች። ታዳሚውን አስደስታለች። በሙያዋ ከሌሎች አርቲስቶች ጋር የተለያዩ አገራት በመሄድ ሙዚቃዎችን፣ ትርኢቶችንና ባህላዊ ውዝዋዜዎችን አሳይታለች። ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት(አፍሪካ ህብረትም) ቀደም ሲል ከጓደኞቿ ጋር ህብረ ዝማሬ
ሰርታለች፡፡ አሰለፈች ድምፃዊ ፣ ተወዛዋዥ
እና ተዋናይ ከመሆኗም ባሻገር ግጥም እና ዜማ ትደርሳለች፡፡
በሀገር ፍቅር ቆይታዋ በርካታ ስራዎችን የሰራችው አርቲስት አሰለፈች ለንጉሱ ፣ ለግርማዊት እቴጌ መነን እና ለውጪ መሪዎች በልዩ ልዩ በዓላት ወቅት አበባ እና ሌሎች ስጦታዎችን ታቀርብም ነበር፡፡ ንጉሱም በተለያዩ ጊዜያት ልዩ ልዩ ሽልማቶችን አበርክተውላታል፡፡ በ1937ዓ.ም ጅሩ ተወልዳ አዲስ አበባ ያደገችው አሰለፈች አሽኔ በተለያዩ የአለም ሀገራትም ስራዎቿን አቅርባለች፡፡ በአንድ ወቅትም በአሜሪካ ቆይታዋ ለፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ ደብዳቤ ፅፋ ከፕሬዚዳንቱም ለፃፈቻ ደብዳቤ ምላሽ ተሰጥቷታል፡፡ ከስፖርት እግር ኳስ እና ሩጫን ትወዳለች፡፡ ቀደም ባለው ጊዜም የቅድስ ጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊ ነበረች፡፡ በሩጫው አለም እነ አበበ ቢቂላ ፣ ሀይሌ ገ/ስላሴ ፣ ደራርቱ ቱሉ ፣ ጥሩነሽ እና ገንዘቤ ዲባባን እንደምታደንቅም ገልፃለች፡፡