Wednesday, August 5, 2015

በትምህርት ቤት ስሟ እሌኒ አሁን ደግሞ ኩኩ .... ድምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ


   ለስለስ ባሉ ዜማዎቿ ትታወቃለች ፡፡ በልጅነቷ የወንድ የሴት ሳትል ከእሷ ድምፅ ጋር የሚሄዱትን ሙዚቃዎች ተጫውታለች፡፡ የእነ ሙሉቀን መለሰ ፣ ጌታቸው ካሳ ፣ ሽሽግ ቸኮል ፣ እታገኘሁ ሀይሌ እና ብዙነሽ በቀለን እና ሌሎችንም ሰርታለች፡፡ በጊዜው ቆየት ያሉትን የእንግሊዘኛ ሙዚቃዎች በማድመጥ እስከማንጎራጎርም ደርሳ ነበር፡፡ ተወዳጇ ድምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ፡፡

   ገና ከልጅነቷ ጀምሮ ት/ቤት ውስጥ በማንጎራጎር ነው ሙዚቃን የጀመረችው፡፡ በጊዜውም ሙሉቀንን ታደንቀው ስለነበረ ከአባቷ ከደጃዝማች ሰብስቤ ሽብሩ እየወሰደች (የእሳቸውን እና የሌሎችም) የግጥም ስራዎች ትሰጠው ነበር፡፡ ሙሉቀን መለሰም “ናኑ ናኑ ነይ” የተሰኘ አልበሙን ሲያወጣ በጊዜው የግጥም ደራሲዬ ኩኩ ሰብስቤ ናት እስከ ማለትም ደርሶ ነበር፡፡ 

   ድምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ የመጀመሪያ የመድረክ ስራዋን ያቀረበችው ከአይቤክስ እና ዋልያስ ባንድ ጋር በመሆን በሂልተን ሆቴል በተዘጋጀ የተማሪዎች ፓርቲ ላይ ነበር፡፡ በዚህ መድረክ ላይ የታጨችው ድምፃዊት ኩኩ ራስ ሆቴል በ300ብር ተቀጥራ ከመሀሙድ አህመድ ጋር በአይቤክስ ባንድ አጃቢነት በሳምንት ሁለት ቀን ትጫወት ነበር፡፡ በኋላ ላይም ወደ ሂልተን ሆቴል በመዛወር በ600ብር በየቀኑ ከዋልያስ ባንድ ጋር ትሰራ ነበር፡፡ በጊዮን ሆቴል ከሮሃ ባንድ ጋርም ትጫወት ነበር፡፡ በዚሁ ባንድ አጃቢነትም ከአለማየሁ እሸቴ ጋር “እንግዳዬ ነሽ” የተሰኘ የመጀመሪያ ስራዋን ለህዝብ አድርሳለች፡፡ ቀስ በቀስም ከሮሃ ባንድ ጋር ሶስት ያህል አልበሞችን አውጥታለች፡፡ 


    ከተለያዩ አንጋፋ ድምፃውያን ጋር በቅብብሎሽ የሰራቻቸውም በሮሃ ባንድ የተቀናበሩ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ከአይቤክስ ፣ ዋልያስ  ፣ ሮሃ ፣ ኢትዮ ስታር እና ኤክስፕረስ ባንዶች ጋር በተለያዩ ጊዜያት ሰርታለች፡፡ በተለይ በትዝታ ስራዎቿ የምትታወቀው ድምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ እስካሁን ስምንት ያህል አልበሞችን ሰርታለች፡፡ የመጨረሻ አልበሟ “ቻለኩበት” የተሰኘው ሲሆን በቀጣይም ሌላ አልበም ለመስራት እየተዘጋጀች ነው፡፡ በርከት ያሉ ነጠላ ዜማዎች ያሏት ሲሆን በቅርቡም “ሰበቤ” የተሰኘ ነጠላ ዜማዋን ለአድናቂዎቿ ጀባ ብላለች፡፡ እሳካሁን ባላት የካበተ ልምድ በሀገር ውስጥ እና በውጪ ኮንሰርቶቿን አቅርባለች፡፡ በጅቡቲ ጀምራ ሰነዓ፣ አቡዳቢ ፣ የመን ፣ ዱባይ ፣ አሜሪካ (በተለያዩ ከተሞች) እና በታላላቅ የአውሮፓ ከተሞች በመዘዋወር ሙዚቃዎቿን ለአድናቂዎቿ ተጫውታለች፡፡


     በ1980ዎቹ ወደ አሜሪካ የሄደችው ድምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ በዚያው ለ15 አመታት ያህል ቆይታለች፡፡ በዚያም አንድ ልጅ አፍርታለች፡፡ ልጇ ካሌብ የአሜካ ዜግነት ያለው ሲሆን በቅርቡም የከፍተኛ ትምህርቱን ለመከታተለ ወደ አሜሪካ ይጓዛል፡፡ ልጇ ከፍተኛ የኳስ ፍቅር እንዳለው የምትናገረው ኩኩ በአንድ ወቅትም እንግሊዝ ሀገር ወስዳ የማንቺስተር ስታዲየምን አስጎብኝታዋለች፡፡ድምፃዊት ኩኩ የትምህርት ቤት ስሟ እሌኒ ሲሆን 12ኛ ክፍልን ስትጨርስ እና ዘፋኝ ስትሆን ነው “ኩኩ” የሚል ስሟን በጋዜጣ ያሳወጀችው፡፡
  

    በሀገር ውስጥ እና በውጭ በርከት ያሉ የምሽት ክለቦች ውስጥ ሰርታለች፡፡ በሀገር ውስጥ ፍራንክ አዲስ ፣ እንዲጎ . ሀረር መሶብ ፣ ወረገኑ ፣ ሀርለም ጃዝ ፣ ጃዝ አምባ ፣ በአሜሪካ ደግሞ ከቴዲ ማክ ጋር በመስከረም ሬስቶራንት ስራዎቿን ታቀርብ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ “Club H2O እና ማማስ ኪቺን ሙዚቃዎቿን ትጫወታለች፡፡ እኔ በዚሁ ላብቃ ቀሪውን እናንተ ጨምሩበት ……  እድሜ እና ጤና ለተወዳጇ እና አንጋፋዋ ድምፃዊ ኩኩ ስብስቤ ተመኘሁ፡፡

No comments:

Post a Comment