Wednesday, July 1, 2015

ድምፃዊ ፀዳለ ገብረማሪያም ማን ናት ... ?


    ድምፃዊት ፀዳለ ከድምፃዊነቷ ባሻገር ጥሩ ተወዛዋዥ ናት፡፡ ቫልስ እና ታንጎ የመሳሰሉትን ስትጫወት ደግሞ ከአይን ያውጣሽ ታስብላለች ይላሉ በቅርብ የሚያውቋት፡፡ የሁለት ወንድ ልጆችም እናት ናት፡፡

  ከሀረር ወደ አዲስ አበባ መጥታ አክስቷ ጋር ያደገችው ፀዳለ በአክስቷ አማካኝነት ወ/ሮ አሰገደች አላመራው ሆቴል(ፓትሪስ ሉሙምባ ምሽት ክበብ) ገባች፡፡ በዚሁ ምሽት ክበብ ውዝዋዜ ትሰራ የነበረችው ፀዳለ የተለያዩ ድምፃውያን ስራቸውን ሲያቀርቡ በመስማት እሷም ለራሷ  ታንጎራጉር ጀመር፡፡ ከዚያም በጓደኞቿ አነሳሽነት ወደ ሙዚቃው አለም ገባች፡፡ በወቅቱም የብዙነሽ በቀለን “የሚያስለቅስ ፍቅር” በመጫወት ነው የተቀጠረችው፡፡

  በፓትሪስ ሉሙምባ ቆይታዋ በዳንስ ፣ ውዝዋዜ እና ድምፃዊነት እየሰራች 100ብርም ይከፈላት ነበር፡፡ በፓትሪስ ሉሙምባ ምሽት ክበብ ስትጫወት በተመለከቷት ሻምበል ወንድሙ ዘውዴ እና ድምፃዊ ታምራት ሞላ አማካኝነት ምድር ጦር ኦርኬስትራ በ1958ዓ.ም በሲቪል የዘመናዊ ሙዚቃ ድምፃዊነት ተቀጠረች፡፡ በምድር ጦርም የራሷን የመጀመሪያ ስራ “ካለህበት መጣሁ” የተሰኘ ሙዚቃን ተጫውታለች፡፡ ቀስ በቀስም በርከት ያሉ የአማርኛ እና የሀረር ኦሮምኛ/ቆቱኛ/ ሙዚቃዎችን በግል እና በጋራ አቀንቅናለች፡፡
 
  በግሏ ፡- ካለህበት መጣሁ ፣ ቀለበቴን እንካ ፣ ፍቅር ነው፣ መች ቀረሁ፣ ጨክኜ ፣ የሴቶች ህሊና ፣ አጀቢቱ ፣ ልጆቼን አደራ እና ሌሎችንም ሰርታለች፡፡ በተለይ “ልጆቼን አደራ” የተሰኘው ስራዋ ከራሷ ህይወት ጋር የተገናኘ ሲሆን የግጥሙ ደራሲ ደግሞ ሲራክ ታደሰ ነው፡፡ ከባሏ ጋር በተለያየችበት ወቅት የተጫወተችው ይህ ስራ በግጥሙ ውስጥ የእሷን ህይወት ስለሚያሳይ የተወሰኑትን የዘፈኑን ግጥሞች በጥቂቱ እነሆ፡-
             “መሰረት የሌለው ፍቅርና ቤት
             አይቀርም መፍረሱ ዛሬ አየሁት
             ትቀበለኝ እንደሆን ሀሳቤን
             አደራ እልሃለሁ ልጆቼን፡፡
             ሳምንህ የከዳኸኝ አንተ የጊዜ ሰው
             ትዳራችን ጠፋ ቤታችን ዘጋህው
             እኛም እንለያይ ይበተን ሀብታችን
             እስኪ ለማን ይቅሩ ህፃን ልጆቻችን……”
በጋራ(ከሃብታሙ ሽፈራው) ጋር ፡- ውይይት ፣ ሰመለሌ እና ሌሎች ኦሮሚኛ ዘፈኖችን ተጫውታለች፡፡

    በምድር ጦር ቆይታዋ ከእነ ታምራት ሞላ ፣ አባይ በለጠ ፣ ሀብታሙ ሽፈራው ፣ ጌታቸው አስፋው ፣ ጥላዬ ጨዋቃ እና ሌሎችም ጋር አብራ ሰርታለች፡፡ ከምድር ጦር ኦርኬስትራ ጋርም በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በመዘዋወርም ሙዚቃዎቿን አቅርባለች፡፡ ምድር ጦር 270 ብር ይከፈላት ነበር፡፡ በኋላም ዕድገት አግኝታ በ400 ብር ወደ ማዕከላዊ ዕዝ ተዛውራለች፡፡ በዚያ ቆይታዋም ከእነ ብዙነሽ በቀለ ፣ መንበረ ፣  ዘመነ መለሰ እና ሌሎችም ጋር ተጫውታለች፡፡

   ድምፃዊ ፀዳለ ገብረማሪያም ከ1958 - 81 ዓ.ም በምድር ጦር ፣ ከ1981 - 85 ዓ.ም በማዕከላዊ ዕዝ ፣ከ1985 - 2000 ደግሞ በራስ ትያትር በዘመናዊ ሙዚቃ ድምፃዊነት ሰርታለች፡፡ በዚሁ አመትም ጡረታ ወጥታለች፡፡ብዙ ስራዎቿን ግጥም እና ዜማ ይሰሩላት የነበሩት ምድር ጦር በነበረችበት ጊዜ - (ኮለኔል ለማ ደምሰው ፣ ተሾመ ሲሳይ እና ወንድሙ ዘውዴ) ሲሆኑ ማዕከላዊ ዕዝ - (አየለ ማሞ) ራስ ትያትር ደግሞ ሱራፌል አበበ ናቸው፡፡

  ነሀሴ 5,1938 ዓ.ም ሀረር የተወለደችው ድምፃዊት ፀዳለ ገብረማሪያም አሁን በህመም ምክንያት ቤት ውላለች፡፡ ሰርጋችንን ያሞቅንባቸው ፣ ብሶታችንን የረሳንባቸው ፣ ወደ ኋላ በምልሰት ትዝታዎቻችንን ያስታወስንባቸው ፣ አርቲስቶቻችን የህዝብ ሀብት በመሆናቸው ክብር ልንሰጣቸው ይገባል፡፡በችግራቸው ጊዜም ልናስታውሳቸው እና ልንደርስላቸው ያስፈልጋል፡፡

No comments:

Post a Comment