Sunday, February 22, 2015

ኒውስዊክ የዛሬ 40 አመት ገደማ ተከታን ደብዳቤ ለደርግ ፅ/ቤት ፅፎ ነበር ……


    “ይህ ደብዳቤ ለቀድሞው የኢትዮጵያ ቱሪስት ድርጅት ሃላፊ አቶ ሀብተስላሴ ታፈሰ ምህረት ይደረግላቸው ዘንድ ለደርግ ወታደራዊ ፍርድ ቤት የተላከ ነው ፡፡ በፍርድ ቤቱ ችሎት ጣልቃ የመግባት ፍላጎት የለኝም፡፡ ይሁንና ሀብተስላሴ ታፈሰ በምርመራ ወንጀለኛ ሆነው እንኳን ቢገኙ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ለሀገራቸው ያደረጉትን አስተዋፅኦ ከግምት እንዲያስገባ እማፀናለሁ፡፡ የኒውስዊክ የአፍሪካ ቢሮ ሃላፊ እንደመሆኔ ሀብተስላሴ ታፈሰ የቱሪዝም ሚኒስትር ብቻ ናቸው አልልም፡፡ መንግስት ያልሾማቸው የኢትዮጵያ አምባሳደር ናቸው፡፡ ያልገባሁበት የአፍሪካ ሀገር የለም ሀብቴን የሚወዳደር አፍሪካዊ ሚኒስትር ግን አላየሁም፡፡ ሀብተስላሴ ሁሉ ነገር ቢሟላላቸው ኢትዮጵያን በቱሪዝም የአፍሪካ ቁንጮ እንደሚያደርጓት አልጠራጠርም፡፡ ቱሪዝም ያለ እሳቸው ትርጉም የለውም፡፡ ልማትን የምትሻ ኢትዮጵያ እኚህን ታላቅ ሰው ብታጣ እጅግ አሳፋሪ ይሆናል፡፡ ፍርድ ቤቱም ለምን ይህን ያህል እንደምወተውት ሳይረዳ ይቀራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ” 


   ብዙዎች እንደሚሉት ለሀብተስላሴ ታፈሰ ከእስር መፈታት የውጭ መገናኛ ብዙሃን የማይናቅ ሚና ነበራቸው፡፡ ቀደም ሲል መልካም ስራቸውን ያሞካሸው ኒውስዊክ መፅሄት በደለኛ እንኳን ቢሆኑ ለሀገራቸው ያደረጉት አስተዋፅኦ ታይቶላቸው ቅጣቱ እንዲቀል ከላይ ባነበባችሁት መልኩ ተማፅኖ ነበር ፡፡

Friday, February 20, 2015

ገንዘቤ ዲባባ በ5ሺህ ሜትር ክብረ ወሰን ሰበረች

  
   ገንዘቤ ዲባባ በስቶኮልም በተካሄደ የ5ሺህ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር 14፡18.86 በመግባት የርቀቱን ክብረ ወሰን የግሏ አድርጋለች፡፡ የ5ሺህ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ክብረ ወሰን 14፡24፡37 በሆነ ሰዓት በመሰረት ደፋር ተይዞ የነበረ ነው፡፡ ገንዘቤ ክብረ ወሰኑን የሰበረችው የመሰረትን ሰዓት በ5 ሰከንድ በማሻሻል ነው፡፡

  ብርቱካን ፈንቴ እና ብርቱካን አዳሙ15፡22፡56 እና 15፡34.15 በሆነ ሰዓት ገንዘቤን ተከትለው ገብተዋል፡፡ ገንዘቤ ባሳለፍነው የጎርጎሮሳውያኑ 2014 በ15 ቀናት ውስጥ ሶስት ክብረ ወሰኖችን መስበሯ ይታወሳል፡፡ገንዘቤ ዲባባ በቤት ውስጥ ውድድሮች ፈርጥ እየሆነች መምጣቷን ዘገባው አትቷል፡፡
                                                          ምንጭ፡-ራነርስ ወርልድ

Thursday, February 19, 2015

የሰማዕታት ሀውልት /የካቲት 12/


    ሀውልቱ የወራሪው የጣሊያን ወታደሮች በግፍ የጨፈጨፏቸውን 30ሺ ያህል ሰዎች ለመዘከር የቆመ ነው፡፡ ግራዚያኒ ሰራዊቱን እና መኳንንቱን ጠርቶ ፣ ህዝቡን ሰብስቦ የአሁኑ አዲሰ አበባ ዩኒቨርስቲ ቀደም ሲል ገነተ ልዑል በሚል ይታወቅ በነበረው በአፄ ኃይለስላሴ ቤተ መንግስት ውስጥ የተለመደ የእብሪት ንግግሩን በማሰማት ላይ ነበር፡፡ ግራዚያኒን ለመግደል አመቺ ቦታ እና ጊዜ ሲጠባበቁ የነበሩት አብርሐም ደቦጭ እና ሞገስ አሰግዶም የያዙትን ቦምብ አከታትለው ወረወሩበት፤ ግራዚያኒም ቆሰለ፡፡ ከዚያች ቅፅበት በኋላ በማንኛውም ሁኔታ የተገኘ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በግፍ ተጨፈጨፈ፡፡ አዲሰ አበባም በንፁሀን የደም ጎርፍ ተጥለቀለቀች፡፡ በህፃናት ለቅሶ በእናቶች ዋይታ ተዋጠች፡፡ በወቅቱ የተፈጠረው ሁኔታም ኢትዮጵያውያን በድፍረት እና በወኔ ጠላትን እንዲፋለሙ ብርታት ሆናቸው፡፡ እነዚህን ያለርህራሄ የተጨፈጨፉ ንፁሀን ዜጎች ለማሰታወስም ዛሬ በየካቲት 12 ሆስፒታል ፣ በአዲሰ አበባ ዩኒቨርስቲ እና በአንበሳ ግቢ መካከል 6ኪሎ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ የሰማዕታቱ ሃውልት ቆሟል፡፡


         በዚህ ሀውልት ቀረፃ ላይ ኢትዮጳያውያን ባለሙያዎችም ተሳትፈዋል፡፡ ሀውልቱ 28 ሜትር ቁመት ያለው ሲሆን ባለ ሶስት ማዕዘንም ነው፡፡ ሀውልቱ የተሰራው በሁለት የዩጎዝላቪያ ዜግነት ያላቸው ባለሙያተኞች ሲሆን በሀውልቱ ላይ ኢትዮጵያውያን በጣሊያን ወታደሮች በግፍ ሲገደሉ የሚያሳዩ ቅርፃ ቅርፆችም ይስተዋላሉ፡፡ ሀውልቱ ከቅርፃ ቅርፆቹ ባሻገር የተለያዩ ፅሁፎችም አሉት፡፡
                                                                   ክብር ለተሰውት ሰማዕታት……..!!!

Thursday, February 5, 2015

ጥቂት ስለ ስቴፈን ዊሊያም ሆውኪንግ....


ዊልያም ሼክስፒር ፣ አይዛክ ኒውተን ፣ ቻርለስ ዳርዊን፣ አልበርት አንስታይን፣ እና መሰል ምሁራኖች በእያንዳንዱ የአለም ማህበረሰብ  ህይወት ላይ እጅግ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳረፍ የቻሉ የእውቀት አባቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ምድራችንን ከተሰናበቷት ዘመናትን ቢያስቆጥሩም ለአለም ህዝብ አበርክተው ያልፉት ስራቸው ግን ስማቸውን ለዘላለም እንድናስታውሳቸው ያደርግናል፡፡


     ስቴፈን ሆውኪንግ ደግሞ አንስታይን ካለፈ በኋላ የተገኘ ምጡቅ አእምሮ ያለው የአለማችን ቁንጮ ሳይንቲስት እየተባለ ይወደሳል፡፡ እ.ኤ.እ ጥር 8, 1642 ጋሊሊዮ ጋሊሊ ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡ ከ300 አመታት በኋላ ደግሞ ብሪታኒያው ስቴፈን ሆውኪንግ እውቁ የእንግሊዝ ዩንቨርሰቲ በሚገኝበት ከተማ ኦክስፎርድ እ.ኤ.አ ጥር 8, 1942 ተወለደ፡፡


      ሆውኪንግ እጅግ ምጡቅ አእምሮውን በመጠቀም አብረውት የሚማሩትን  ተማሪዎች ከመብለጥም አልፎ  የፊዚክስ ትምህርትን ለበርካታ አመታት ላስተማሩ መምህራንም ፈተና ሆኖ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1962 ከኦክስፎርድ ዩንቨርሰቲ የከፍተኛ ማዕረግ ተሸላሚ በመሆን የመጀመሪያ ድግሪውን አገኝቷል፡፡ ከተወሰኑ አመታት በኋላም በ1966 ከካምብሪጅ ዩንቨርስቲ የዶክትሬት ድግሪውን ተቀብሏል፡፡


  ስቴፈን ዊሊያም ሆውኪንግ  በሲንጉላሪቲ /ነጥብነት/ ፣ ቢግ ባንግ /ታላቁ ፍንዳታ/ ፣ ብላክ ሆልስ / ፅልመታዊ ጉድጓዶች/ ፣ የሆውኪንግ ራዴሽን /ጨረራ/ የሚሉ ንድፈ - ሀሳቦች ላይ ሰፊ ትንታኔ ሰጥቷል፡፡  “A Brief History of Time, The Grand Design”  እነዚህን እና ሌሎች መፅሀፍትን አሳትሟል፡፡ በተለይ “A Brief History of Time” የተሰኘ መፅሀፉ በብዙ ሚሊዮን ቅጅዎች የተሸጠ ሲሆን በተለያዩ ቋንቋዎችም ተተርጉሟል፡፡ በ1979 በሂሳብ የሉካዥያን ፕሮፌሰርነትን አግኝቷል፡፡ በርካታ ሽልማቶችንም በተለያዩ ጊዜያት ተጎናፅፏል፡፡


 የአስትሮ - ፊዚክሱን ሊቅ ገና በወጣትነቱ ያጋጠመው የሞተር ኒውሮን በሽታ ለሞት ባይዳርገውም የእድሜ ልክ አካል ጉዳተኛ እና የተሸከርካሪ ወንበር ቁራኛ አድርጎታል፡፡ በሽታው ልዩ ልዩ የነርብ ህዋሳትን የሚያቀጭጭና የሚያዳክም በመሆኑ ሆውኪንግንም መናገር እንዳይችል አድርጎታል፡፡


    ለዘመኑ ቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና በሰው ሰራሽ ንግግር ማቅረቢያ መሳሪያ /Speech Generating Device / በመጠቀም መግባባት ይችላል፡፡ በጉንጮቹ አካባቢ የተገጠሙት እነዚህ ሴንሰሮች ሀሳቡን በመረዳት ወደ ፅሁፍ እና ድምፅ ይቀይሯቸዋል፡፡

                                                                   እንዲህም ይቻላል!!!

Wednesday, February 4, 2015

የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት እና ተመራማሪነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ሶስት መምህራን የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ፡፡

 

   የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶከተር ዮሴፍ ማሞ እንዳስታወቁት የፕሮፌሰርነት ማዕረጉ ለመምህራኑ የተሰጠው የዩኒቨርስቲው ሴኔት በወሰነው መሰረት ነው፡፡ በዚህም ለዩኒቨርስቲው ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ይፍሩ ብርሃን ፣ ለእንሰሳት ህክምና ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ኢታና ደበላ እና ለስነ ህይወት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ፍቅሬ ደሳለኝ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ከ

መምህራኑ ከረዳት ፕሮፌሰር እስከ ተባባሪ ፕሮፌሰር በቆዩባቸው ጊዜ ያከናወኗቸው የምርምር ስራዎች በአለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ባላቸው የምርምር ስራ በሚያትሙ የህትመት ውጤቶች ታትመው የወጡት በዩኒቨርስቲው ተገምግሞ ለፕሮፌሰርነት ብቁ የሚያደርጋቸው መሆኑ ታምኖበታል ብለዋል፡፡ እንደ ኢ.ዜ.አ የምርምር ስራዎች ለአካባቢው ማህበረሰብ እና ለአገር ጥቅም እንዲሰጡ ለማድረግ ዩኒቨርስቲው የምርምር ጥናት ኢንስቲትዩት አቋቁሞ  ወደ ስራ መግባቱን አመልክቷል፡፡